ነሐሴ 19 ፣ 2014

በጉራጌ የስራ ማቆም አድማ እና እስር እንደቀጠለ ነው

City: Hawassaዜናወቅታዊ ጉዳዮች

የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት ክልሉን በፍትሀዊነት ማስተዳደር የተሳነው በመሆኑ በህዝቦች ትግል እና የአደረጃጀት ጥያቄዎች እየፈረሰ ያለ አስተዳደር ነው ሲል ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር ገልጿል።

Avatar: Ilyas Kifle
ኤልያስ ክፍሌ

ኢልያስ ክፍሌ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ምሩቅ ሲሆን ዘገባዎችን እና ዜናዎችን የመፃፍ ልምድ አለው። በአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ነው።

ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በጉራጌ የስራ ማቆም አድማ እና እስር እንደቀጠለ ነው

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ዛሬ ነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. የስራ ማቆም እና ቤት ዉስጥ የመቀመጥ አድማ  እየተደረገ እንደሚገኝ አዲስ ዘይቤ ከዞኑ ነዋሪዎች አረጋግጣለች።

ከነሐሴ 12 ቀን ጀምሮ በደቡብ ክልል ኮማንድ ፖስት ዉስጥ የምትገኘዉ የጉራጌ ዞን በዛሬዉ ዕለት በወልቂጤ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አዋሳኝ አከባቢዎች የስራ ማቆም እና በቤት ዉስጥ የመቀመጥ አድማ እያደረጉ እንደሚገኙ ተሰምቷል። ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ዉሳኔ በኃላ በአካባቢው ሰዎች እየታሰሩ እና እየተንገላቱ ነዉ ብለዋል"። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለነሐሴ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ስብሰባ መጥራቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር ባወጣው መግለጫ የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ የክልሉ ምክር ቤት እና የጉራጌ ዞን የምክር ቤት አባላትን ለመክሰስ እና ለማሰር እንዲያመቸው ያለመከሰስ መብታቸውን ለማንሳት ነው ሲል ወቅሷል።

ማህበሩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ “ያለመከሠስ መብታቸው እንዲነሳ የሚደረጉ የክልልና የዞን ም/ቤት አባላት በዳግም ጥሪው እንዳይገኙ ማሰር፤ ያልታሰሩና የፓርቲው ሃሳብ ውድቅ ያደረጉ የምክር ቤት አባላትን በማሸበር እና እንደሚታሰሩ በማስፈራራት በስብሰባው ላይ እንዳይገኙ ማድረግ፤ ሕዝቡንና በተለይም ደግሞ የክልልነት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ፓርቲውንና መንግስትን የሚሞግቱ አካላትን ተስፋ ማስቆረጥ ነው” ሲል ቅሬታውን ገልጿል።

ማህበሩ እንደሚለው በደቡብ ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች እየተነሱ ያሉት “የክልሉ መንግስት ክልሉን በፍትሃዊነት መምራት ተስኖት በህዝቦች ትግል እየፈረሰ በመሆኑ ለህዝቦች የሚጠቅም ልዕልና ያለው ሀሳብ ማቅረብ አይችልም፤ የከሰሩ ፖለቲከኞች ስብስብ በመሆኑ አብሮ የመጥፋት ሴራ እያሴሩ” በመሆኑ ነው ብሏል።

ነሐሴ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. በአሜሪካ ሜሪላንድ መቀመጫውን ያደረገው ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር ባወጣው “የጉራጌ ማሕበረሰብን ማሰር፣ ማዋከብ እና እንግልት እንዲቆም የቀረበ የአቋም መግለጫ” በሚል ባወጣው መግለጫ የተዋቀረው ኮማንድ ፖስት የክልልነት ጥያቄውን የሚያነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዋከብ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ብሏል።

ከነሐሴ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በጉራጌ ዞን የታወጀው ኮማድ ፖስት ካስቀመጣቸው ክልከላዎች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እንዲሁም የስብሰባ እና የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ እንደሚገድብ ተገልጾ ነበር። በተጨማሪም ምንም አይነት መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆነ ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል፣ የንግድ ሱቆችና ተቋማትን ያለምክንያት መዝጋት እንደማይቻል እና የመንግስት ሰራተኞችም ከስራ መቅረት እንደማይችሉ፣ ሰልፍና መሰል እንቅስቃሴዎች መከልከላቸው እንዲሁም የሞተር ሳይክል እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት እና የባጃጅ ተሽከርካሪዎች እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ብቻ እንደሚሰሩ ተወስኗል።

በዚያው እለት የኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ጉራጌ ዞንን ጨምሮ አራት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ በነበሩበት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እንደሚቀጥሉ አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበርም በአቋም መግለጫው “ሐሳቡ ውድቅ የሆነበት የብልጽግና ፓርቲ እና እሱ የሚመራው መንግስት የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ትቶ ጉራጌ ዞን ላይ ባሰፈረው የደህንነትና ጸጥታ መዋቅር እና የኮማንድ ፖስት አማካይነት ሕዝቡን በጅምላ እያሰረ ይገኛል። ይህ እስር አፈናና እንግልት በበላይነት የሚያስፈጽመው በጉራጌ ሕዝብ ላይ እንደ መዥገር በተጣበቀውና እና ደቡብን እመራለሁ በሚለው አቶ ርስቱ ይርዳው እና እሱ በሚመራቸው ጭፍራዎች አማካይነት ነው” ሲል ገልጿል።

በተጨማሪም ከህብረተሰቡ ጥያቄ ጎን የቆሙ እና “ሰላማዊ ትግሉን” የሚመሩ ወጣቶችን ጨምሮ የዞኑ ጤና ቢሮ ኃላፊ፣ የዞኑ የፖለቲካና የርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር በመግለጫው አስታውቆ ነበር።

ዛሬ እየተደረገ የሚገኘው አድማ በዋናነት "ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተገናኘ ድጋፋችሁን ሰጥታችኋል የተባሉ ዜጎች እየታሰሩ እንደሚገኙና እነርሱም ድምፃቸውን እያሰሙ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የስራ ማቆም አድማዉ ለሁለት ቀናት ሊቆይ እንደሚችል የሚናገሩት ምንጮቻችን የአድማው ዋነኛ ምክንያት ደግሞ "በዞኑ ምክር ቤት የፀደቀው በክልል የመደራጀት ጥያቄ እንዲመለስ፣ የታሰሩት ዜጎች እንዲለቀቁ እንዲሁም ኮማንድ ፖስቱ እንዲነሳ" የሚል እንደሆነ ማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ቀደም ነሐሴ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመሳሳይ የጉራጌ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ወልቂጤ ከተማ እና በሌሎች የዞኑ አካባቢዎች “የክልልነት ጥያቄያችን ይመለስ?” በሚል የስራ ማቆም አድማ እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን የስራ ማቆም አድማው ለሁለት ቀናት መቆየቱንም አዲስ ዘይቤ ከዞኑ ነዋሪዎች አረጋግጣ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ባደረጉት የስራ ማቆም እና በቤት የመቀመጥ አድማ "መንግስት ለ30 ዓመታት በተደጋጋሚ ያቀረብነውን ህገመንግስታዊ መብታችን የሆነዉ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄያችንን እንዲመለስ" ሲሉ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን የአደረጃጀት ጥያቄን በተመለከተ ከዚህ በፊት በ2011 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት ፀድቆ ለፌዴራል መንግስቱ ከቀረበ በኋላ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ዘንድሮ በተለይም በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል የሚነሱ መሰል ጥያቄዎችን በክላስተር ለመፍታት የውሳኔ ሐሳብ መቅረቡን ተከትሎ ከነሐሴ ወር መጀመሪያ አንስቶ ጥያቄው ተጠናክሮ ተነስቷል።

ይህን ተከትሎም ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. የጉራጌ ዞን ምክር ቤት የአደረጃጀት ጥያቄውን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ጉባኤ ያካሄደ ሲሆን ክልል የመሆን ውሳኔው በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በስብሰባዉ ላይ በቀረቡት 'የጉራጌ ዞን ከሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር በክላስተር ይደራጅ' አልያም 'ራሱን ችሎ በክልልነት ይደራጅ' የሚሉት ሁለት አማራጮች  ላይ በተደረገው የምክር ቤት አባላት ድምፅ አሰጣጥ፤ 40 የምክር ቤቱ አባላት በክላስተር መደራጀትን ሲደግፉ 52 አባላት ደግሞ ጉራጌ ዞን ክልል መሆን አለበት በማለት በአብላጫ ድምፅ አፅድቀውታል። እዚህ ውሳኔ በኋላ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች የደስታ መግለጫ ሁነቶች ነበሩ።

ዓለም አቀፍ የጉራጌ ማህበር በአቋም መግለጫው ማዋከቡ እንዲቆም፣ የታሰሩ ዜጎች እንዲፈቱ እንዲሁም “የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚ/ር ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድም ፓርቲያቸው እና መንግስታቸው በጉራጌ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለው እስር እንግልት እና አፈና እንዲያቆም እና ለሕዝቡ ሕጋዊ ጥያቄ ሕጋዊ ምላሽ እንዲሰጥ አበክረን እንጠይቃለን” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ማህበሩ የዜጎች እስር እና እንግልት ቀጥሏል በሚል በድጋሜ ነሐሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “ይህ ሁሉ የሚሆነው በህገ መንግስቱ በጥቁር እና ነጭ የተቀመጠውን 'የህዝቦች መብት ይከበር' የሚሉ ግለሰቦች ላይ ነው። "ወንጀላቸው" ለምን ክላስተሩን ውድቅ አደረጋችሁ የሚል ነው። መንግስት ለህዝብ የገባው የለውጥ ቃል የመጠበቅ ወኔ ካለው ይህን የለየለት የማፍያ ስራ በአስቸኳይ ሊያስቆም ይገባል እንላለን” ብሏል።

ማህበሩ ጨምሮም “አፋኙ ስርአት የኃይል የበላይነቱ ወዳረጋገጠበት የጉልበት መንገድ ሊያስገባን ስሜትን የሚፈታተኑ ትንኮሳዎች ሲፈፅም ቆይቷል። በሀገር ሽማግሌዎቻችን፣ በምክር ቤት አባሎቻችን እና በወጣቶቻችን ላይ መረን የለቀቁ ትንኮሳዎች ፈፅሟል። የህዝብ ለህዝብ ግጭት እንዲነሳ ወረቀቶች በትኗል፣ ቤቶችንም አቃጥሏል። እነዛን ሁሉ ትንኮሳዎች ከዘላቂ ጥቅማችን አንፃር በትዕግስት እያለፍን መጥተናል። አሁንም በዚሁ ፅናታችን በመቀጠል ወደ ድሉ ደጃፍ እንጓዛለን” ሲል በመግለጫው አሳስቧል።

አስተያየት