መጋቢት 29 ፣ 2014

በጎንደር ገቢዎች መስተንግዶ የተማረሩ 537 ተቋማት ለፌደራል መገበር ጀምረዋል

City: Gonderዜና

የግብር ከፋዮች ሂሳብ በወቅቱ አለመመርመሩ፣ የሂሳብ መዝገቡ በግለሰቦች ግምት የተዘጋጀ መሆኑ እና መሰል አስተዳደራዊ እና የሥራ ቅልጥፍና ጉዳዮች ግብር ከፋዮቹ በአብዛኛው የሚማረሩባቸው ናቸው

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በጎንደር ገቢዎች መስተንግዶ የተማረሩ 537 ተቋማት ለፌደራል መገበር ጀምረዋል
Camera Icon

ፎቶ፡Fineartamerica

ዓመታዊ የገቢ ግብር ክፍያቸውን በጎንደር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች መምሪያ የሚፈጽሙ 537 ተቋማት የክፍያ ጣቢያቸውን ከክልል ወደ ፌደራል ማዘዋወራቸው ተነገረ። ድርጅቶቹ ይህንን የሚያደርጉት ካፒታላቸውን ጨምረው ተቋማቸውን ወደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (PLC) ወይም ‘ሼር ካምፓኒ’ በማሳደግ ነው። በከተማዋ ከተመዘገቡት 1ሺህ 650 ተቋማት መካከል 537 ያህሉ የሥራ ፈቃዳቸውን እና ተቋማዊ አደረጃጀታቸውን አሻሽለው በፌደራል ግብር ከፋይነት ተመዝግበዋል። 

ከ500ሺህ ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡት የግል ድርጅቶቹ የግብር ሂሳባቸውን ወደ ፌደራል ያዘዋወሩት የክልሉ ገቢዎች የውስጥ አሰራር ፈጣን እና ቀልጣፋ አለመሆኑ ስላማረራቸው እንደሆነ ተናግረዋል። 

“‘ሼር ካምፓኒ’ እና ‘PLC’ ተቋማት የሚገብሩት ፌደራል ነው። በአንድ ሰው ባለቤትነት የሚተዳደሩት ግን ያንን ማድረግ አይችሉም” የሚሉት አቶ ጥላሁን ጀምበሮ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት ባለሙያ ናቸው። ነጋዴዎቹ ራሳቸውን ለፌደራል ግብር ከፋይነት የሚያደራጁበት አንዱ ምክንያት ወረፋን ለመቀነስ እንደሆነ ነግረውናል። “የፌደራሉ ገቢዎች ቢሮ በየክልሎች ቅርንጫፍ ቢሮ ስላለው የግብር ከፋይ ደንበኞቹ ቁጥር ከክልሎች አንጻር አነስተኛ ነው። ይህ ሁኔታ መስተንግዶው ፈጣን እንዲሆን ያግዛል” ያሉ ሲሆን የፌደራል ገቢዎች ፋይል በዓመት አንድ ጊዜ መሰራቱ፣ የክልሎች እስከ 5 ዓመት መቆየቱ ነጋዴዎቹ ፌደራልን እንዲመርጡ ሊያደርግ እንደሚችል እንደሚገምቱ ነግረውናል።    

የጎንደር ከተማ ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ሙሉቀን ብርሃኑ በበኩላቸው ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት ክፍያቸውን አዲስ አበባ በሚገኘው የፌደራሉ ቅርንጫፍ ቢሮ መፈጸም የጀመሩት ተቋማት ወደ ፌደራል የመዘዋወር ሀሳብ ያሳደሩት በልዩ ልዩ ምክንያቶች ነው። እንደ ኃላፊዋ ማብራሪያ “የግብር ከፋዮች ሂሳብ በወቅቱ አለመመርመሩ፣ የሂሳብ መዝገቡ በግለሰቦች ግምት የተዘጋጀ መሆኑ እና መሰል አስተዳደራዊ እና የሥራ ቅልጥፍና ጉዳዮች ግብር ከፋዮቹ በአብዛኛው የሚማረሩባቸው ናቸው” ብለዋል።

ነጋዴዎቹ በበኩላቸው በቅጣት ስም እስከ 50ሺህ ብር ያለአግባብ መክፈላቸውን፣ ለአስቸኳይ የባንክ ብድር ሂሳባቸው እንዲመረመር ሲጠይቁ አላስፈላጊ መዘግየት መኖሩ፣ በሂሳብ ምርመራ መዘግየት ምክንያት የግብር እዳ እየተጠራቀመባቸው መሆኑን የአሰራር ግድፈት ነው ሲሉ አንስተዋል።  

ስሙን መጥቀስ ያልፈለገው ከፍተኛ ግብር ከፋይ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ነው። ከ500ሺህ ብር በላይ ካፒታል አስመዝግቦ በካፌና ሬስቶራንት ሥራ ተሰማርቷል። ከአንድ ሚልዮን ብር በላይ ዓመታዊ የገቢ ግብር ይከፍላል። በስሩ 5 ቋሚና 2 ጊዜያዊ ሰራተኞችን ቀጥሯል። “የምንጠየቀው ግብር ከምንሰራው ጋር በፍጹም አይመጣጠንም” በማለት ሐሳቡን ይጀምራል። “በከተማዋ ሕገ-ወጥ ንግድ በመበራከቱ ሕጋዊ ነጋዴዎች ተጎድተዋል። የዶላር እጥረት፣ ኮቪድ እንዲሁም ጦርነቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን ጎድተውታል። ነጋዴው ግብር ለመክፈል የሚመጣው በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ ነው” ብሏል። የግብር ክፍያውን ወደ ፌደራል እንዲያዛውር ያስገደደውም የአገልግሎት አሰጣጡ የተጓተተ እና ኋላ ቀር መሆን፣ ጉቦ የሚጠይቁ ሰራተኞች መበራከት እና መሰል ሁኔታዎች እንደሆኑ ነግሮናል።

“ለነጋዴ ጊዜ ገንዘብ ነው። መስተዳድሩ ይህንን አልተረዳም። ማህደር አያያዝ ላይ ትልቅ ክፍተት አለ። የግብር ከፋዮች ፋይል ይጠፋል። ተቀዶ ይወጣል። የት እንዳለ አይታወቅም። ግብር ከፋዮች በአግባቡ ተስተናግደው አይሄዱም” ሲል ችግሮች ያላቸውን ዘርዝሯል።

የከተማዋ ገቢዎች በያዝነው ዓመት ከአንድ ቢልዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ቢያቅድም እስከ መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የእቅዱን 47.56 በመቶ ማለትም 890 ሚልዮን ብር እንደሰበሰበ ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። እንደ ኃላፊዋ ገለጻ ከደሞዝ የሚሰበሰበው ግብር ከፍተኛውን መጠን የሚይዘው የከተማዋ የገቢ ግብር ነው።

የገቢዎች መምሪያ ኃላፊዋ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ "ጎንደር እንድታድግ እየሰሩ ያሉ ነጋዴዎች ለከተማዋ ግብር መክፈል አለባቸው የሚል አቋም አለን። ማስገደድ እንደማንችል ይታወቃል። ነገር ግን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግራችንን በቴክኖሎጂ በማዘመን ግብር ከፋዮቻችንን ወደ ነበሩበት ለመመለስ እንጥራለን” ብለዋል።

አስተያየት