መጋቢት 29 ፣ 2014

በአቃቂ ቃሊቲ በአማኞች መካከል የተከሰተው ፀብ እና ውዝግብ

City: Addis Ababaዜናማህበራዊ ጉዳዮች

በአካባቢው በተፈጠረው ግጭት አንድ ወጣት በጥይት ተመትቶ ህይወቱ ማለፉ ታውቋል

Avatar: Nigist Berta
ንግስት በርታ

ንግስት የአዲስ ዘይቤ ከፍተኛ ዘጋቢ እና የይዘት ፈጣሪ ስትሆን ፅሁፎችን የማጠናቀር ልምዷን በመጠቀም ተነባቢ ይዘት ያላቸውን ጽሁፎች ታሰናዳለች

በአቃቂ ቃሊቲ በአማኞች መካከል የተከሰተው ፀብ እና ውዝግብ

እሁድ መጋቢት 25 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ባቡር ጣቢያ አካባቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ አዋሳኝ ቦታ ላይ በሚገኘው መካነ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስትያን አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት በቦታው የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉንና ይህን ተከትሎም በቁጣ የተሞሉ ወጣቶች ግጭቱ ከተነሳበት ቦታ ራቅ ብሎ ወደ ሚገኘው አቃቂ በሰቃ መካነ ኢየሱስ ወንጌላውያን ቤተ-ክርስትያን በመዝለቅ ባደረሱት በተባለው ጥቃት ስምንት ሰዎች መጎዳታቸው እንደተገለፀ ይታወሳል።

የፀቡ መነሻ እንደሆነ ሲነገር የቆየው ባቡር ጣቢያ አካባቢ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና ለኢትዮጵያ ወንጌላዊያን እምነት ተከታዮች በቅርብ ርቀት ቤተ-እምነት መገንቢያ ቦታ ከመስጠቱ ጋር ተያይዘው የመጡ አለመግባባቶች መሆኑ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘም የነበሩት ሁነቶች ላይ አዲስ ዘይቤ የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግራለች።

ለሀይማኖት ተቋማቱ መገንቢያ እንዲሆን በከተማው አስተዳደር ተሰጥቷል ስለተባለው ቦታ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች ቦታው ለእምነት ተቋማቱ የተላለፈው በዚሁ አመት ሲሆን መካነ ስብሐት ቅድስት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን ቦታው ላይ ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ መገልገል መጀመሯን ተናግረዋል። 

በሥላሴ ቤተ-ክርስትያን የሚገለገሉ የአካባቢው ወጣቶች ቦታው ላይ በቅርብ ርቀት ልዩነት ለሁለት የተለያዩ የእምነት ተቋማት ግንባታ መሬት መሰጠቱን ያወቁት የደብረ ዘይት በዓል እለት የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በቦታው ላይ ዳስ ጥለው ፕሮግራም ሲያሰናዱ መሆኑን መረዳት ተችሏል። በዕለቱ የሥላሴ ቤ/ክ ወጣቶች “አካባቢው ላይ ለሁለቱ እምነት ተቋማት በቅርብ ርቀት ቦታ መሰጠቱ አግባብ አይደለም” የሚል ተቃውሞ ሲያሰሙ በተፈጠረ ግርግር የክፍለ ከተማው አስተዳደር አካላት በቦታው ተገኝተው ወጣቶቹን ማረጋጋታቸውን እና የሀይማኖት አባቶችም መጥተው ወጣቶችን አረጋግተው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙት የወንጌላውያን እምነት ተከታዮች በበኩላቸው አንደሚናገሩት ቦታው ላይ የአምልኮ ስፍራውን ለመገንባት የውጪ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንና “መጋቢት 18 ቀን ዳስ አትጥሉም ባሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወጣቶች የተፈጠረው ግርግር ላይ አስተዳደሮች እና የኦርቶዶክስ ሀይማኖት አባቶች ደርሰው አረጋግተው ሲሄዱ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ግምት ነበራቸው። “ነገር ግን መጋቢት 26 ቀን ድጋሚ ለአገልግሎት ወደ ቦታው ስንሄድ የተፈጠረው ግርግር አለመግባባቱ እንዳልተፈታ እና ሌላ እቅድ እንደነበር ያመለክታል” ሲሉ ይናገራሉ።

በዕለቱ በተፈጠረው ግርግር ላይ የአንድ ወጣት ህይወት ማለፉን ተከትሎ የተቆጡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ወጣቶች ውዝግቡ ከተነሳበት አካባቢ ራቅ ብሎ በሚገኘው አቃቂ በሰቃ መካነ ኢየሱስ ወንጌላውያን ቤተ-ክርስትያን በመዝለቅ በምዕመኑ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በተመለከተ ያነጋገርናቸው የአጥቢያው መጋቢ የሆኑት አገልጋይ ሳሙኤል ታደሰ ሁኔታውን ሲያስረዱ፣ “እሁድ ወደ ረፋድ አራት ሰዓት ገደማ ከምእመናን ጋር ጉባኤያችንን በማገባደድ ላይ ሳለን ቁጥራቸው በርከት ያሉ ወጣቶች ወደ ቤተክርስትያኑ በመዝለቅ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ማድረስ፣ እቃ መሰባበር እና የቤተክርስትያኑን ንብረት ይዘው መውጣት ጀመሩ” ያሉ ሲሆን በዚህ ሁኔታ ስምንት ሰዎች ተጎድተው ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ መደረጋቸውን፣ በርካታ የቤተክርስትያኗ ቁሳቁሶች መዘረፋቸውንና መውደማቸውንም ገልፀዋል። አያይዘውም ፖሊስ ዘግይቶ መድረሱን አንስተዋል።

በሌላ በኩል በመጀመሪያ የቦታ ግጭቱ በተቀሰቀሰበት ባቡር ጣቢያ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው በአቃቂ ቃሊቲ መካነ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ህይወቱ ያለፈውን ዘመድኩን አማረ ስለተባለው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የቅርብ ቤተሰቡ ሲናገሩ፣ “ዘመድኩን የሞተው በግርግሩ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ አባል በተኮሰው ጥይት እንደሆነ በአይናችን አይተናል። ነገር ግን ሲውል ሲያድር በድንጋይ ውርወራ ነው የሞተው የሚሉ ፍትህን ለማድበስበስ የታለሙ ልክ ያልሆኑ መረጃዎች ከዚህም ከዛም መውጣት ጀመሩ” ይላሉ።

የቤተሰብ አባሉ ሲያስረዱ የኦሮሚያ ፖሊሶች ተከታታይ ተኩስ እያሰሙ ወደላይ ሲሮጡ መታየታቸውን እና ህዝቡ በድንጋጤ ለባሰ ግርግር መጋለጡን በማንሳት፣ “ወጣቶች የዘመድኩንን አስክሬን ወደ ቤተ-ክርስትያኑ ቅጥር ግቢ ካስገቡት በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ደርሰው ተተኩሶበት ህይወቱ አንዳለፈ ከአይን እማኞች ቃል ወስደው ነበር። እኛም ይሄ ሁሉ ምስክር ባለበት የአስክሬን ምርመራ አያስፈልግም ብለን ነበር ቀብሩ የተፈጸመው። ነገር ግን ዛሬ የሚወራው ሌላ ነው፤ ስለዚህ አሁንም ፍትህ ይከበር የሚል አካል ምርመራ አድርጎ ለዘመድኩን ፍትህ ያሰጠው” ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተገናኘ ሃሳባቸውን የገለፁልን በአካባቢው የነበሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ወጣቶች በበኩላቸው ግርግሩ በፕሮቴስታንት አማኞች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሲባል ታቅዶ የተከናወነ እንደሚመስል ያምናሉ። በተለይም ግጭቱ ሌላ ቦታ ላይ ተፈፅሞ ከግጭቱ ጋር ምንም ግንኙነት ወደሌለው ወደ አቃቂ መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ፈጥነው ደርሰው ጥቃት ማድረሳቸው ቀድሞ ዝግጅት ተደርጎበት የነበረ ስለመሆኑ አመላካች ሊሆን ይችላል በማለት፣ ፖሊስም ዘግይቶ በመድረሱ ጥፋቶቹ የከፉ እንዲሆኑ አድርጓል በማለት ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን በኩል ያነጋገርናቸው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት አባ ወልደ ኢየሱስ ሰይፉ አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ የአቃቂ ቃሊቲ መካነ ስብሃት ስላሴ ቤተ-ክርስትያን በእርሳቸው አመራር ስር የሚገኝ አጥቢያ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ የተፈፀመው ድርጊት ግን ፍፁም ሊወገዝ የሚገባው እና የትኛውንም እምነት ተከታይ ምዕመናንን የማምለክ መብት የሚጋፋ መሆኑን ገልፀዋል። አያይዘውም የሟች ቤተሰቦችን ማፅናናታቸውንና ማበረታታቸውን የነገሩን ሲሆን፣ ይህንን ድርጊት የፈፀሙ አካላት በሕግ እንዲጠየቁ መደረግ አለበት በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መምህር አባ ገብረ መድኅን በበኩላቸው፣ የተፈጠሩት ውዥንብሮች የጠራ መረጃ ለመስጠት አመቺ አለመሆኑን በመጥቀስ ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ መረጃ እንደሚያደርሱን አሳውቀውናል።

ቀድሞ ግጭት በተከሰተበት በመካነ ስብሐት ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያንም ሆነ ኋላ በተዛመተበት በበሰቃ መካነ ኢየሱስ የወንጌላውያን ቤተ-ክርስትያን የተፈጠረውን ጉዳይ በተመለከተ በፖሊስ በኩል በይፋ የተባለ ነገር የሌለ ሲሆን ህይወቱ ያለፈው ወጣት ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መሞቱን በተመለከተ ስለተነገሩት መረጃዎች ለማወቅ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ይህን ጉዳይ የሚከታተለው የኦሮሚያ ፖሊስ መሆኑን ነግረውናል። ይሁን እንጂ አዲስ ዘይቤ የኦሮሚያ ፖሊስን ለማግኘት በተደጋጋሚ በተለያዩ መንገዶች ሙከራ አድርጋ ሳይሳካ ቀርቷል።

አስተያየት