መጋቢት 28 ፣ 2014

በኤሌክትሪክ መስመር ዘረፋ ምክንያት አሰላ እና አካባቢዋ ለፈረቃ አገልግሎት ተዳርገዋል

City: Adamaዜና

የዝርፊያው አጠቃላይ ኪሳራ እየተሰላ እንደሆነ ገልጸው ሁለት የብረት ምሰሶዎች መውደቃቸውንና ሦስተኛው ምሰሶ በሁለቱ መውደቅ ምክንያት መጣመሙን ነግረውናል።

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅ

ተስፋልደት ብዙወርቅ በአዳማ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በኤሌክትሪክ መስመር ዘረፋ ምክንያት አሰላ እና አካባቢዋ ለፈረቃ አገልግሎት ተዳርገዋል
Camera Icon

ፎቶ፡ELPA

በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ አቅራቢያ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ በተፈጸመ የኤሌክትሪክ መስመር ስርቆት የአሰላ እና አካባቢዋ የኃይል አቅርቦት መስተጓጎሉ ተገለፀ። 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት ለአዲስ ዘይቤ እንዳሳወቀው የስርቆት ወንጀሉ የተፈጸመው መጋቢት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ነው። በዕለቱ አርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ ዴራ ከተማ አቅራቢያ ሁለት ባለ 132 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት ተፈጽሟል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ጥገና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሃብታሙ ውቤ የዝርፊያው አጠቃላይ ኪሳራ እየተሰላ እንደሆነ ገልጸው ሁለት የብረት ምሰሶዎች መውደቃቸውንና ሦስተኛው ምሰሶ በሁለቱ መውደቅ ምክንያት  መጣመሙን ነግረውናል።

“ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ ቦታ አንድ ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ላይ በተፈጸመ ስርቆት አሰላ እና አካባቢዋ ወደ ፈረቃ አገልግሎት ገብተው ነበር” የሚሉት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት የኃይል ስርጭት ኃላፊ አቶ ተመስገን ነሪ፣ ስፍራው ተደጋጋሚ ስርቆት የሚስተዋልበት እንደሆነ ይናገራሉ።

እንደ ኃላፊው ገለፃ አሰላ ሰብስቴሽን የኃይል አቅርቦት የሚያገኘው ከ‘አዋሽ 2’ እና ‘ከመልካ ዋከና’ የኃይል ማመንጫዎች ሲሆን ዋነኛ የኃይል ምንጩ 32 ሜጋዋት የሚያመነጨው አዋሽ 2 ነው። ከመልካ ዋከና የሚገኘው 153 ሜጋ ዋት ኃይል የከተሞቹን ፍላጎት ስለማያሟላ አገልግሎቱን በፈረቃ ለማድረግ መገደዳቸውንም ነግረውናል።

ከዝርፊያው በኋላ ለአሰላ ከተማና አካባቢዋ አገልግሎት የሚሰጡ 9 ወጪ መስመሮችን ከአዳሚ ቱሉ ማሰራጫ በፈረቃ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። በዚህ ጣቢያ ያሉት 5 ባለ 15 ሺህ ቮልት እና 4 ባለ 33 ሺህ ቮልት ወጪ መስመሮች በየ3  ሰዓቱ በመፈራረቅ አገልግሎቱን በማስተናገድ ላይ ይገኛሉ። 

በስፍራው ከዓመት በፊት ተመሳሳይ ስርቆት እንደገጠማቸውና መሰረተ ልማትን መጠበቅ የኅብረተሰቡ ኃላፊነት እንደሆነም  አቶ ሃብታሙ አሳስበዋል። በአካባቢው ከሚገኙ የመንግስት እና የጸጥታ አካላት ጋር ወንጀለኞችን ለሕግ ለማቅረብ እየሰሩ ስለመሆኑም ኃላፊው ተናግረዋል።

የመስመር ጥገናው አንድ ሳምንት ሊወስድ ስለሚችል በሻሸመኔ በኩል ያለውን የኃይል አማራጭ ተጠቅሞ ለከተሞቹ የፈረቃ የኃይል አቅርቦት እየተሰጠ ይገኛል። አገልግሎቱን በፈረቃ ለመስጠት ጥረት ቢደረግም ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በሚኖርባቸው “ፒክ ሀወር” ጊዜያት መብራት የመቆራረጥ ችግር አጋጥሟል።

ተቋሙ የተዘረፉበትን ሐገር ውስጥ የሌሉ እቃዎች በውጭ ምንዛሪ ገዝቶ መጠገን ስለማይችል ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ድጋፍ መጠየቁንና በሌሎች መተካት የሚችሉትን እየተካ ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ ለመመለስ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዳማ ዲስትሪክት የሕግ ከፍል ኃላፊ አቶ ታምራት ረፌራ ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመሩ ስርቆት በሕግ ተይዞ በመጣራት ላይ እንደሚገኝ ነግረውናል። በዲስትሪክቱ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታዩ የሕገ-ወጥ ቆጣሪ ነቀላ፣ የከተማ ውስጥ መስመር ስርቆት እንዲሁም ሕገ-ወጥ መስመር ዝርጋታ ላይ 16 መዝገቦች እንደተከፈተ አንስተው ሁለቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።