መጋቢት 27 ፣ 2014

በጎንደር ከተማ የመንገድ ዳር መብራቶች እና የኤሌትሪክ ገመዶች ስርቆት መበራከቱ ተነገረ

City: Gonderዜና

በያዝነው ዓመት ብቻ ከ3ሺህ ሜትር በላይ የኤሌትሪክ ገመድ በቁጥጥር ስር ውሏል።

Avatar: Getahun Asnake
ጌታሁን አስናቀ

ጌታሁን አስናቀ በጎንደር የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በጎንደር ከተማ የመንገድ ዳር መብራቶች እና የኤሌትሪክ ገመዶች ስርቆት መበራከቱ ተነገረ
Camera Icon

ፎቶ፡ ማህበራዊ ሚዲያ

የመንገድ ዳር መብራቶች እና ገመዶች ስርቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሻቀቡ ተነገረ። የጎንደር ከተማ ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሰረተ-ልማት ቡድን መሪ አቶ የኛነው አዲሱ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በከፍተኛ ወጪ የተዘረጉት የመንገድ ዳር መብራቶችና ገመዶች ተገቢውን አገልግሎት ሳይሰጡ መዘረፋቸው የምሽት ወንጀሎች እንዲበራከቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።  

እንደ አቶ የኛነው ማብራሪያ ከአዘዞ እስከ ኤርፖርት፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ እስከ ገንፎ ቁጭ፣ ከአራዳ እስከ አዲስ ዓለም፣ ከብልኮ እስከ ወለቃ ፈላሻ መንደር ያሉት የመንገድ ዳር የመብራቶች እና የኤሌትሪክ ገመዶች ሙሉ በሙሉ ተዘርፈዋል።

ከአዘዞ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ900 ሜትር በላይ የኤሌትሪክ ገመድ እና ከ50 በላይ ኤልኢዲ መብራት ዘርፈው ለማምለጥ የሞከሩ ከ7 በላይ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው የክስ ሂደት ላይ ይገኛሉ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር ስማቸው አደመ “በያዝነው ዓመት ብቻ ከ3ሺህ ሜትር በላይ የኤሌትሪክ ገመድ በዘራፊዎች ሲወሰድ በቁጥጥር ስር ውሏል” ብለዋል። በተጨማሪም ከወንጀሉ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት 14 ተጠርጣሪዎች የምርመራ መዝገባቸው ተጣርቶ ለአቃቤ ሕግ እንደተላከ ነግረውናል።  

የጎንደር ከተማ ማራኪ ክ/ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ውዱ አዱኛ የምሽት ዘረፋ እና ሕገ-ወጥ የጥይት ተኩስ እንዲባባስ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራቶች ዝርፊያ እንደሚገኝበት ይናገራሉ። አክለውም ከመንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን ከመኖርያ ቤቶችም የኤሌትሪክ ገመዶች መሰረቃቸውን እንደታዘቡ ነግረውናል።
 

የአዘዞ ክ/ከተማ ኤርፖርት አካባቢ ነዋሪዋ ወ/ሮ እማዋይ ፋሲሎ በበኩላቸው “ድርጊቱ ከዓመት ዓመት እየተባባሰ ነው” ብለዋል።

የኤሌትሪክ ማስተላለፊያ ገመዶችን በኤሌትሪክ ምሰሶ ላይ ከማስተላለፍ ይልቅ በመሬት ስር እንዲጓዙ ማድረግ እንደ ጊዜያዊ መፍትሄ መወሰዱን የጎንደር ከተማ ኮንስትራክሽን መምሪያ የመሰረተ-ልማት ቡድን መሪ አቶ የኛነው አዲሱ ተናግረዋል።

“ወንጀል እና ወንጀለኛን ከመከላከል አንጻር ሰፊ ስራ እየሰራን ነው” ያሉት ማኅበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር ስማቸው ከመከላከል በተጨማሪ በጥፋቱ ላይ ተሳታፎ ያላቸው ተጠርጣሪዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እያደረጉ ስለመሆናቸው ነግረውናል። ኃላፊው የከተማዋ ነዋሪዎች የተሰረቀ ንብረት ባለመግዛት ዘራፊዎችን እንዲከላከሉ ጥሪ አቅርበዋል።