በምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን ተገቢውን የአመጋገብ ስርአት ባለመከተል የሚከሰተው መቀንጨር በአማራ ክልል ከነበረበት 41.3 በመቶ ከፍ ሊል እንደሚችል ተነገረ። ክስተቱ የሚፈጠረው መቀንጨርን ለመከላከል በሚሰራው “የሰቆጣ ቃል-ኪዳን” ፕሮጀክት የታቀፉት አብዛኛዎቹ ወረዳዎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ ስለነበሩ ነው ተብሏል።
በሰቆጣ ቃል-ኪዳን የሙከራ ትግበራ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በዋግ-ህምራ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር የሚገኙ 27 ወረዳዎች ተካተዋል።
የሰቆጣ ቃልኪዳን የ6 ወር ሪፖርት ዕንደሚያሳየው ከ2011 – 2013 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ዓመታት በአንድ ቢሊዮን ብር በጀት ከ140 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ የማስጨበጥን ጨምሮ የአመጋገብ ስርአትን የሚያስተካክሉ ግብአቶች እንዲያመርቱ የማገዝ ሥራ ተሰርቷል። ይሁን እንጂ ከመላው ኢትዮጵያ ቀዳሚውን ደረጃ በያዘው አማራ ክልል መቀንጨር በስፋት የታየባቸው አካባቢዎቹ በጦርነት ምክንያት ወድመዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና መረጃ ዕንደሚያሳየው በክልሉ 11 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ 400 ሺህ የሚጠጉት ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በታች ነው። ይህም በክልሉ ያለውን የመቀንጨር ተጠቂዎች ቁጥር ይበልጥ ከፍ ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ከሃያ ሰባቱ ወረዳዎች ግማሽ ያህሉ በጦርነት ቀጣና ውስጥ በመቆየታቸው መቀንጨርን በ2022 ወደ ዜሮ ለማውረድ የተያዘው እቅድ እንዳይሳካ እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ የዘርፉ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል።
መቀንጨርን የመቀነስ ፕሮጀክት በዋናነት ከግብርና፣ ከሴቶች፣ ህፃናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ ከውሃና ማዕድን ኢነርጂ፣ ከትምህርት እና ጤና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት የሚተገበር በመሆኑ ጦርነቱ በተቋማቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት ትልቅ እንቅፋት እንደፈጠረበት ተነግሯል።
የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ፕሮጀክት የባህሪ ለውጥ እና የለውጥ ተግባቦት አማካሪ አቶ ጋሻው አዳነ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ችግሩ በስፋት በሚታይባቸው 27 ወረዳዎች መቀንጨርን የመቀነስ ስራው እየተሰራ እንደነበር አንስተዋል። ፕሮጀክቱ የሚሸፍናቸው በተከዜ ተፋሰስ ስር የሚገኙ ወረዳዎች ወደ 62 ከፍ ያሉት በ2014 ዓ.ም. ነበር።
ከግንዛቤ ፈጠራው በተጨማሪ ዶሮዎች፣ ፍየሎች፣ የተሻሻሉ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች፣ የውሃ እና የአነስተኛ መስኖ ተቋማት ጥሩ ፍሬ በማፍራት ላይ የነበሩ ቢሆንም በጦርነቱ ምክንያት ወድመው አገልግሎት እየሰጡ አለመሆናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።
በጦርነቱ የተከሰተው ውድመት፣ እርሱን ተከትሎ የመጣው የምግብ እጥረት፣ ችግሩን በቅንጅታዊ አሰራር ለመፍታት አለመሞከር እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ናቸው በሚል ተዘርዝረዋል።
“በወረዳዎቹ የተሰሩ ስራዎች በመውደማቸው ስራው መሉ በመሉ ተቋርጦ ቆይቷል። አሁን አንደገና ከዜሮ ለመጀመር ተገደናል" የሚሉት አቶ ጋሻው በአጠቃላይ ተሰርቶ የወደመውን ሀብት በተመለከተ በጀት ተመድቦ በመጠናት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ እና ጤና ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው 45 በመቶ ለህጻናት ሞት ምክንያት የሆነው መቀንጨር በየዓመቱ ከሀገሪቱ ጥቅል ምርት 16.5 በመቶ የሚሆነውን ያሳጣል።