መጋቢት 27 ፣ 2014

በሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበር ላይ በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ

City: Hawassaዜና

የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆነችው ጪሪ ወረዳ የተነሳው ግጭት ወደ ዳኤላ እና ሌሎች አጎራባች ወረዳዎች በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበር ላይ በተከሰተ ግጭት የሰው ህይወት አለፈ
Camera Icon

ፎቶ፡ Google Maps

በሲዳማ እና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ በምትገኘው ጪሪ ወረዳ ሀሌላ ቀበሌ በተከሰተ ግጭት የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰማ። ማንነታቸው ባልታወቀ የታጠቁ ሰዎች እንደተቀሰቀሰ በተነገረው ግጭት ህይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ ከ10 በላይ ሰዎች ከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በሆነችው ጪሪ ወረዳ የተነሳው ግጭት ወደ ዳኤላ እና ሌሎች አጎራባች ወረዳዎች በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

የ“ጪሪ” እና የ“ዳኤላ” ወረዳ ነዋሪዎች እንደሚሉት ግጭቱ አሁንም አልቆመም። የአከባቢው ነዋሪ አቶ ዘርፉ አወቀ "አሁንም የተኩስ ልውውጥ ድምጽ አለ። እንቅስቃሴያችን በስጋት የተሞላ ነው" ሲሉ የሚገኙበትን ሁኔታ አስረድተዋል። 

የግጭቱ መንስኤ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቁ የሐገር ሽማግሌ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸው መሆኑ ተነግሯል። ባሳለፍነው እሁድ መጋቢት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ከምሽቱ አራት ሰዓት የሐገር ሽማግሌው አቶ አዴ ሎኬ ዮኔ በጥይት ተደብድበው መገደላቸውን ተከትሎ የተስፋፋው ግጭት ሰዎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት ዳርጓል።   

የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ጢሞቴዎስ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ ግጭቱ ሆን ተብሎ እንደተፈጸመ ተናግረዋል። 

ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች ወደ ቦና አጠቃላይ ሆስፒታል ተወስደው የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ከክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያሳያል። 

የሲዳማ ክልል ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለማየሁ ግጭቱን አሁን ላይ መቆጣጠር እንደተቻለ እንዲሁም ለጦርነቱ ምክንያት ናቸው የተባሉ አካላት ላይ የማጥራት ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል። አቶ ዓለማየሁ አክለውም በግጭቱ ምክንያት የደረሰው አጠቃላይ ጉዳት የማጣራት ሥራው ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚደረግ ነግረውናል።

አስተያየት