ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ በከተማዋ ሁለት የዳቦ ማምረቻ ፋብሪካ ያስገነቡ ሲሆን አንደኛው በማራኪ ክፍለ ከተማ ለሴተኛ አዳሪዎችና አቅም ለሌላቸው ሴቶች ታስቦ የተገነባ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አይራ አካባቢ በቅርቡ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም የተመረቀው ነው፡፡
በጎንደር ከተማ አይራ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ መጋቢት ወር 2014 ዓ.ም በቀዳማዊት እመቤት በፅህፈት ቤት ግንባታው የተጀመረው የዳቦ ፋብሪካው ባለፈው የካቲት 15 መመረቁ ይታወሳል። የዳቦ ፋብሪካው በዋናነት በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ቢጠበቅም ስራውን ማቋረጡ ነው የተነገረው፡፡
ፋብሪካው በቀን እስከ 400 ሺህ ዳቦ የማምረት አቅም ሲኖረው 100 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደተደረገበትና ለ160 ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥር በምርቃቱ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ መናገራቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ከተመረቀበት ጊዜ ጀምሮ አዲስ ዘይቤ ወደ ቦታው ሂዳ እስካየችበት መጋቢት 6 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ፋብሪካው ከስራ ውጭ ነው፡፡
የጎንደር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አለምነው ፋብሪካው የካቲት 15 በሚመረቅበት እለት በትራንስፎርመር ላይ ደረሰ ባሉት የፊውዝ መቃጠል ያጋጠመ ችግር እንጅ ብልሽት እንዳላጋጠመ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል፡፡
ከሌላ ፋብሪካ ባመጡት ተቀያሪ ፊውዝ ዳቦ አምርተው ለአረጋዊያን ማዕከል መስጠታቸውን የተናገሩት ስራ አስኪያጁ ችግሩን በማስተካከል በሁለት ሳምንታት ውስጥ ወደ አገልግሎቱ እንደሚመለስ ነው የገለፁት።
የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የዳቦ ፋብሪካው መጠናቀቁ ቢያስደስታቸውም ተሰርቷል ከማለት ውጭ አገልግሎት ባለመስጠቱ ቅሬታ እንደተሰማቸው ይገልጻሉ፡፡
ነዋሪዎቹ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በጎንደር እና አካባቢዋ የዳቦ ግብዓትና የቅባት እህሎች በስፋት የሚመረትባት ብትሆንም ህዝቡ የዳቦ እና የስኳር እንዲሁም የምግብ ዘይትን ማግኘት አዳጋች ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱ እና የውሃ እጥረት ከፍተኛ ችግር ለሆነባት የመናገሻ ከተማ ለሆነችው ጎንደር እስካሁን በከንቲባነት የሚመራ ሰው ሳይመደብ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
አዲስ ዘይቤ በከተማዋ ውስጥ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ዳቦና ዘይት ፋብሪካዎችን "ለምን ስራ ሳይጀምሩ ስራ አቆሙ" ስትል የሚመለከተውን ጠይቃ https://am.addiszeybe.com/featured/gonder/lifestyle-am/business-am/cooking-oil-issue-in-gondar መዘገቧ ይታወሳል።