መጋቢት 21 ፣ 2014

በኦሞ ወንዝ መገደብ ምክንያት የዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ

City: Hawassaዜና

በኦሞ ወንዝ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ዙሪያ ያሉ ቀበሌዎች ለከፍተኛ የምግብ እና የንፁሕ መጠጥ ውሃ ችግር ሰለባ እንደሆነ ሰምተናል።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በኦሞ ወንዝ መገደብ ምክንያት የዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን ተናገሩ
Camera Icon

ፎቶ፡ Britannicia

በኦሞ ወንዝ መገደብ ምክንያት በተፈጠረው ሰው ሰራሽ ሐይቅ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥና በአከባቢው ለረዥም ጊዜ የተከሰተው የዝናብ እጥረት በዳውሮ ዞን ዛባ ጋዞ ወረዳና በለሎች አከባቢዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለከፋ ችግር እንዲጋለጡ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል።

በዳውሮ ዞን የዛባ ጋዞ እና የሎማ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ 19 ቀበሌዎች ማለትም ጋራዳ ባጭራ፣ ጋራዳ ኢንታላ፣ ዳሻ አጃ፣ ሳማራ ሚናጣ፣ ደቼ ደነባ፣ ዛባ ዲልባ፣ ሀልዓኒ፣ ሴሪ፣ ደልባንታ፣ ዋሩማ እና አንጋላ አከባቢዎችን ጨምሮ በኦሞ ወንዝ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ዙሪያ ያሉ ቀበሌዎች ለከፍተኛ የምግብ እና የንፁሕ መጠጥ ውሃ ችግር ሰለባ እንደሆነ ሰምተናል።

አቶ ጌዲዮን ገዜ የተባሉ የአከባቢው ነዋሪ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "ቀደም ሲል ለመጠጥ ውሃ እንዲሁም ለእንስሳት አልፎም ተርፎ ለተለያየ አገልግሎት ሲጠቀሙ፣ ሲገለገሉ የቆዩ ምንጮች ዛሬ ላይ የሉም። ሲያማቸው የሚታከሙበት፣ ባህላዊ የህክምና መፍትሔ የነበሩ ከ8 በላይ ፍል ውሃዎች በኦሞ ወንዝ መገደብ ምክንያት እንዲሁም ለረጅም ወራቶች በነበረው የዝናብ እጥረት ችግሩ ስር ሊሰድ ችሏል" ብለዋል።

ከስድስት ዓመታት በፊት ይህ ችግር ቀስ በቀስ እያየለ የመጣ እንደሆነ እና በግምት ከ30 ሺህ በላይ የሚገጡ ነዋሪዎች አሁን ላይ በተከሰተው የተፈጥሮ እና የሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት መሞታቸው እንዲሁም በርካታ ህፃናትና እናቶች ለከፋ የምግብ እጥረት ችግር መጋለጣቸውን ሰምተናል።

የዳውሮ የዞን የአደጋ ስጋት አመራር ጽ/ቤት ከዞን አስተዳደርና ከለሎች የባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አብይና ንዑሳን ኮሚቴ በማቋቋም ለአደጋው ምላሽ ለመሰጠት ወደ ትግበራ መግባቱን እና "በአከባቢው ለተከሰተው የምግብ እጥረት እንዲሁም ለእንስሳት ሞት ችግር በኦሞ ወንዝ በተገነባው የኃይል ማመንጫ ግድብ አማካኝነት በተፈጠረው ሀይቅ ምክንያት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና በአከባቢው ለረዥም ጊዜ የተፈጠረ የዝናብ እጥረት ዋነኛ ችግር ነው" ሲሉ የዳውሮ ዞን አደጋ ስጋት አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዋሰሁን አባተ ተናግረዋል።

ኃላፊው አክለውም "በአከባቢው ከዚህ በፊት በነባሩ የደቡብ ክልል በልማታዊ ሴፍቲኔት ለቋሚ ቀጥተኛ ተጠቃሚዎች በማኅበራዊ አገለግሎት የሚደረግ ድጋፍና ለህፃናት የሚደረግ የትምህርት ቤት ምገባ አገለግሎት ለ3 ወራት መቋረጡንም" ገልፀዋል።

ከአምስት ቀናት በፊት ድርቁ ወደ ተከሰተበት አከባቢ ያቀኑት የዳውሮ ዞን ም/ዋና አስተዳዳሪ ምትኩ መኩሪያ (ዶ/ር)፣ የዞኑ ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሐይ ገሉ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ከማህበረሰብ ጋር ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን የተፈጠረውን ችግር በረጅም እና በአጭር ጊዜ እቅድ  ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

ምርቶቻቸውን ለመሸጥ  እንዲሁም በኦሞ ወንዝ ግድብ ምክንያት ከጥንት ጀምሮ የነበረውን የአጆራ መንገድ እንደተዘጋባቸውና መንግስት የውሃ መሰረተ ልማት ሲያስገባላቸው መንገዱ በሁለቱም በኩል ክፍት እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ በዚሪያችን ቢሆንም እስካሁን መብራት ማግኘት እልቻልንም ያሉት ነዋሪዎቹ ለችግሩ መንግስት ዘላቂ መፍትሔ መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።

በዞኑ ለአደጋው ምላሽ ለመስጠት በተቋቋመው ግብረ-ኃይል አማካኝነት የተለያዩ የእህል ዓይነቶች፣ የእንስሳት መድኃኒትና ለህፃናት የሚሆኑ አልሚ ምግቦች ተገዝተው ወደ አከባቢው የማጓጓዝ ስራ እየተሰራ ቢሆንም በቂ እንዳልሆነ ነው የዞኑ የአደጋ ስጋት አመራር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዋሰሁን የገለፁት።

ችግሩን ለክልልና ለፌደራል የባለድርሻ አካላት ቀደም ብለን አሳውቀናል ያሉት አቶ ዋሰሁን በተለይ አሁን በአከባቢው ያለው ችግር ከፍተኛ ስለሆነ ሁሉም የባለድርሻ አካላት ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥ  ጠይቀዋል።