ባለፈዉ አንድ ወር ውስጥ ከአዲስ አበባ ተሰርቀዉ ወደ ሐዋሳ ከተማ የገቡ 15 የተለያየ ሞዴል ያላቸዉ መኪናዎች ከ14 ተጠርጣሪዎች ጋር መያዛቸውን የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ መምሪያ አስታዉቋል።
የከተማዋ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት አቶ መኩሪያ ማኒሳ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት በተለያዩ ጊዜያቶች ከአዲስ አበባ ከተማ ተሰርቀዉ ወደ ሐዋሳ ከተማ የገቡ መኪናዎችና የወንጀሉ ፈፃሚ ተጠርጣሪዎች ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እና ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ሊያዙ ችለዋል።
በሐዋሳ ከተማ አንድ ግለሰብ አዲስ መኪና ሲገዛ መረጃዉ እንደሚደርሳቸው የሚናገሩት አቶ መኩሪያ “ስርቆቱን የሚፈጽሙት ግለሰቦች የመኪናውን ታርጋ በመቀየር ፣ የተለየ ቀለም በመቀባት እና ህገወጥ ሰነዶችን በማዘጋጀት” በአዲስ መልክ እንደሚሸጡ ተናግረዋል። መረጃዉ ለከተማው ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሚደርሰው መኪኖቹ አዲስ ቀለም ከተቀቡ በኋላ ታርጋቸውን ለማስቀየር በከተማው መንገድ እና ትራንስፖርት ቢሮ ምዝገባ ሲካሄድ ነው። ህገወጥ ሰነዶችን በማዘጋጀት መኪኖቹን ለማስመዝገብ ሲሞክሩ ብዙ ጊዜ ይያዛሉ። አንዳንዶቹም ገና ጋራዥ ዉስጥ ታርጋና ቀለም ሲቀያይሩ የተያዙ ናቸዉ ።
እንደ ኃላፊው ገለፃ 5 መኪኖች በሐዋሳ ከተማ ሲያዙ የተቀሩት መኪኖች ደግሞ በሲዳማ ክልል በሚገኙ ጩኮ እና አለታ ወንዶ ተብለው በሚጠሩ የወረዳ ከተሞች ላይ ሊያዙ ችለዋል። 14ቱ ተጠርጣሪዎች ለአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ተላልፈዉ መሰጠታቸውንም ኃላፊዉ ጨምረዉ ተናግረዋል።
አሁን አሁን ከአዲስ አበባ ተሰርቀው ለሚመጡ መኪኖች መዳረሻ የሆነችው ሐዋሳ የተለየዩ የስርቆት ወንጀሎችም እየተበራከቱባት ነው። የሐዋሳ ነዋሪዎችም ለከፍተኛ ስጋት መጋለጣቸዉን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
አቶ እንዳልካቸው ሰለሞን ከመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ የሞተር ሳይክላቸዉ የተወሰደባቸዉ የከተማው ነዋሪ ናቸው። “ከቀኑ 7:00 ሰዓት ላይ የሞተር ሳይክል ቤቴ በር ላይ አቁሜ ወደ ዉስጥ ገባሁ ፤ ከአስር ደቂቃ በኋላ ስመለስ ባኖርኩበት ቦታ ላይ ላገኘው አልቻልኩም፡ በአቅራቢያ ወዳለዉ ፖሊስ ጣቢያ አመልክቻለሁ ነገር ግን ከጠፋ አሁን አንድ ወር አልፎታል” ብለዋል።
በዚህ የስርቆት ወንጀል ሌላው ሰለባ የሆነዉ ማርቆስ ከፍያለው ደግሞ ምሽት ላይ 05 ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ ከሚገኘዉ የመኖሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ዉስጥ የሞተር ሳይክሉ እንደተወሰደበት ተናግሯል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በሐዋሳ ከተማ ቱላ ክ/ከተማ ነዋሪ የሆኑ እናት ለአዲስ ዘይቤ ሲናገሩ “በተደጋጋሚ የስርቆት ወንጀል በምኖርበት አካባቢ ይስተዋላል፤ እኔ ራሴ ሁለት ጊዜ ተዘርፌአለሁ” ያሉ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መልኩን እየቀያየረ በመጣዉ የወንጀል ድርጊት በፍርሃት መዉጣት እና መግባት እንኳን እንደተቸገሩ ያስረዳሉ።
የሞባይል ስልክ እንዲሁም የእጅ ቦርሳ የተወሰደባት ሌላኛዋ ነዋሪ አስቴር ዳምጠዉ “ከአንድ ሳምንት በፊት ከስራ አምሽቼ ወደ ቤት በመሄድ ላይ ሳለሁ ሁለት ወጣቶች በስለት አስፈራርተዉ የያዝኩትን ንብረት ተቀብለዉኛል” ብላለች። የሚያሳዝነው ግን ትላለች ወጣት አስቴር “ድርጊቱ ሲፈፀም በአቅራቢያዬ ያሉ ሰዎች እየተመለከቱ በዝምታ ማለፋቸዉ ነዉ” በማለት የስርቆቱ ወንጀል በማህበረሰቡ ላይ ምን ያህል ስጋት ሊፈጥር እንደቻለ ተናግራለች ።
“ከንጥቂያ እና ከስርቆት ወንጀል ጋር በተያያዘ 67 ተጠርጣሪዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በከተማዋ የፀጥታ ኃይል ሊያዙ ችለዋል” የሚሉት የሐዋሳ ከተማ የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ማኒሳ ከህብረተሰቡ እየተነሱ የሚገኙት ጥያቄዎች ስህተት የለባቸውም ብለዋል። እንደ አቶ መኩሪያ ገለፃ አምስት ተጠርጣሪዎች ከሞተር ሳይክል ስርቆት ጋር በተገናኘ ተይዘዉ የፍርድ ሂደታቸዉን እየተከታተሉ ይገኛሉ።
ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ የስርቆት ወንጀል ተፈፀመብን የሚል ሪፖርት ከነዋሪዉ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደርሳቸዉ የሚናገሩት ኃላፊው ይህንን ለማስተካከል እየተሰራ እንደሆነ ገልጸዋል። “በቅርቡ ባደረግነው ግምገማ፣ በዚህ አመት በተለይ ደግሞ ያለፉት ስድስት ወራት ከፍተኛ የዘረፋ ቁጥር ሪፖርት የተደረገበት ነው” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።