በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ40 ሺህ በላይ የዩኒቨርስቲ መምህራን በአንድ ላይ በመሆን አውጥተውታል በተባለው መግለጫ ላይ ለሰኞ ህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጠራው የስራ ማቆም አድማ እዉቅና የለውም ሲል የኢትዮጵያ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ማህበር ገለፀ።
የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ማህበርና ቴክኒካል ረዳቶች በአንድ ላይ በመሆን ከሰሞኑ ባወጡት መግለጫ ከህዳር 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም ዩኒቨርስቲዎች መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደት እንደማይኖር ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እስከሚመለሱ ድረስ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ መዘጋጀታቸው መሆኑ ተመላክቷል።
ለደህንነታቸዉ ሲባል ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ እና ከ40 ሺህ መምህራኖች መካከል አንዱና አስተባባሪ የሆኑት መምህር ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት "መምህራን እያነሱት የሚገኙት ጥያቄ የህልዉና ነዉ፤ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነዉ። ጥያቄያችን እየተከፈለን የሚገኘዉ ደመወዝ በደረጃችን ታሳቢ ይደረግ እንጂ የፖለቲካ ወይም የስልጣን ፍላጎት አይደለም የመኖር ጥያቄ ነዉ ተቸግረን መኖር አልቻልንም" ሲሉ ተናግረዋል።
የዩኒቨርስቲ የመምህራን ማህበር ወኪሎች ከ2013 እስከ 2015 ዓ.ም. ድረስ በህጋዊነት መንገድ መንግስት ጋር በመሄድ ጥያቄዎችን ሲያሰማ የነበረ ቢሆንም በቂ ምላሽ ሊገኝ አልቻለም የሚሉት አስተባባሪዉ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የስራ ምዝና ክብደት (JEG) ጥናት በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ጥናት ሲደረግ የዩኒቨርስቲ መምህራን እንዲሁም ቴክኒካል ረዳቶችን ሳያካትት ቀርቷል ሲሉ የስራ ማቆም አድማው አስተባባሪ መምህር ተናግረዋል። “በዚህም ለሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ወርሃዊ ደመወዛቸዉ ሲጨምር የዩኒቨስቲ መምህራን ግን ባለበት እንዲሆን ተደርጓል” ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
በህጋዊነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ይደረጋል ስለተባለው የስራ ማቆም አድማዉ መረጃዉን በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ከመስማት ዉጪ የሚያዉቀዉቁት ነገር እንደሌለ እና እርሳቸው በሚመሩበት መዋቅር ዉስጥ እንደሌለ በተለይ ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
በ2004 የተቋቋመዉ እና በስራዉ ላይ 10 ዓመታትን ያስቆጠረዉ በክልል ደረጃ የተዋቀረ የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶ/ር በፍቃዱ ዘለቀ በበኩላቸው "የተጠራዉ አድማ በማህበሩ ስም የሚነግዱ እንጂ ህጋዊ የሆነዉ የመምህራን ማህበር ጥሪ አላደረገም ፤ ዉሸት ነዉ" በማለት ተናግረዋል።
ከደመወዝ እና ከጥቅማጥቅም እንዲሁም ከደረጃ እድገት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ጥያቄዎችን ሲያነሱ የቆዩት የዩኒቨርስቲዎች መምህራን ላልተወሰነ ጊዜ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ እና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መገደዳቸውን አንስተዋል።
ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ ሌላ መምህር እንደሚናገሩት “በመምህርነት ለ13 ዓመታት ብቆይም ክፍያዬ 8 ሺህ ብር ነዉ ይህ ደግሞ ከአገልግሎት አንፃር እጅግ ያነሰ ነዉ፤ ቤተሰብ ማስተዳደር እና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን ለሟሟላት አልቻልኩም " በማለት ተናግሯል።
ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የዩኒቨርስቲ መምህራን ማህበር ተወካዮች ለስድስት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በደብዳቤ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን ከጥያቄዎቹም የስራ ምዝና ክብደት ጥናት እንዲለቀቅ፣ አገልግሎት ያለዉ የዩኒቨርስቲ መምህር ከአዲስ ተቀጣሪዎች ጋር እኩል መከፈል እንደሌለበት እና በደረጃ እርከን እንዲከፈል፣ የአገልግሎት ክፍያ እና ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲኖር፣ ከአንድ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሌላ ዝዉዉር እንዲፈቀድላቸው፣ ህጋዊዉ የመምህራን ማህበር በአግባቡ እየሰራ ስላልሆነ የዩኒቨርስቲ መምህራን የራሳቸው ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚሉና በአጠቃላይ ባለ14 ነጥብ ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር።
በ2013 ዓ.ም. ቀርቦ ያልተመለሰው ጥያቄያቸዉ የቀድሞ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር መምህራን ያገለለዉ የሰራተኞች የስራ ምዘና ክብደት ጥናት ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ቢያስደርግም በተለያዩ ምክንያትቶች ምላሽ ሳያገኙ መቅረታቸዉን ለአዲስ ዘይቤ ገልፀዋል።
ዶክተር በፍቃዱ አክለዉም “መምህራን የሚያነሱት ጥያቄ ትክክል ቢሆንም ሀገሪቷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ዉስጥ ጦርነት ዉስጥ በመሆኗ እና በሌሎች ምክንያቶች ጥያቄዎች ሊዘገዩ ቢችሉም አሁን ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ክትትል እየተረገ እንደሚገኝ እና በረጅምና በአጭር ጊዜያት ይመለሳሉ መታገስ ያስፈልጋል” ብለዋል።