ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጉራጌ ዞን በክልል እንዲደራጅ በቤት ውስጥ በመቀመጥ፣ በስራ የማቆም አድማ እና በሰላማዊ ሰልፎች ሲጠይቁ የነበሩት የዞኑ ነዋሪዎች ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ የዞኑ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ገለፁ።
በዞኑ ከሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በተጨማሪ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል በተባለዉ የንፁህ ዉሃ አቅርቦት ችግር እንዲቀረፍ በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ቢወጡም የደቡብ ክልል ፀጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስና ጥይት በመተኮሳቸው ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ ቁጥራቸዉ ከ40 በላይ የሚሆኑ ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ ከተደረገበት ረቡዕ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ግን የክልል እንሁን ጥያቄዎችን ያስተባበሩ እና ተሳትፎ አላቸዉ ተብለዉ የተጠረጠሩ የብሔሩ ተወላጆችን በፀጥታ ኃይሎች እየታሰሩ ይገኛሉ። የምክር ቤት አባላት፣ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ዞኑ በክልል እንዲደራጅ ሀሳብ የሰጡ፣ የህግ ባለሙያና ጠበቃዎች እና የማህበረሰብ አንቂዎች በአጠቃላይ ወደ 60 የሚጠጉ ሰዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አዲስ ዘይቤ ሰምታለች።
ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እየተጠየቀ የሚገኘው የጉራጌ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄ በዞኑ ምክር ቤቱ ዉሳኔም ሆነ በህገ መንግስቱ መሰረት አለመፈፀሙ እንዲሁም እስካሁን ሳይመለስ መቆየቱ በተደጋጋሚ ለተደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች እና አድማዎች መነሻ እንደሆነም ይታወቃል።
በጥቅሉ የሚነሱት ጥያቄዎች “በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር መቀጠል አንፈልግም፣ ባህልና ቋንቋችንን ማሳደግ እንፈልጋለን፣ በመሰረተ ልማት የጎለበተ አከባቢ ያስፈልገናል" የሚሉት ዋነኞቹ ሲሆኑ ይህም ህገ መንግስታዊ መብት ሆኖ ሳለ አለመከበሩ ተቃውሞ እንዲያሰሙ አድርጓቸዋል።
በወልቂጤ ከተማ ታስረዉ የነበሩ እስረኞችም ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ቡታጅራ መወሰዳቸዉ ተነግሯል። በእስር ላይ የሚገኙት ሰዎችም በፀጥታ ኃይሎችና በጠባቂዎች ድብደባ እንደሚደርስባቸው ወጣት መስፍን ደነቀ ይናገራል። አቶ መስፍን ደነቀ የሰባት ወር ነፍሰጡር የሆነችውና ያለመከሰስ መብቷ ሳይነሳ በእስር ላይ የምትገኘዉን የቀድሞ የዞኑ ምክር ቤት አስተባባሪ እና የክልሉ ምክር ቤት አባል ወ/ሮ ጠጄ ደነቀ ወንድም ነዉ።
አቶ መስፍን ደነቀ ሁኔታዉን ለአዲስ ዘይቤ ሲያስረዳ "ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ከለሊቱ 9 ሰዓት ላይ ወደ 42 የሚጠጉ ልዩ ኃይሎች” አጥር ዘለዉ ገብተዉ የክልልነት ጥያቄን ደግፈሻል በሚል እህቱን እንደወሰዷት ይገልፃል። “አሳሪዉ አይታወቅም” የሚለዉ መስፍን ደነቀ "አንዴ ጉራጌ ዞን ፓሊስ ጣቢያ፣ ቀጥሎም አይሪሽ አሁን ደግሞ ቡታጅራ ተወስዳ ትገኛለች" ያለ ሲሆን በቡታጅራ ታስረዉ የሚገኙት የብሔሩ ተወላጆች ከፍተኛ ድብደባ እየደረሰባቸው ይገኛል" ሲል የጉዳዩን አሳሳቢነት ያስረዳል።
"እስሩ ህገ ወጥ ነዉ" በማለት የታሳሪዎችን መብት በተመለከት ከአዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረገው የህግ ባለሞያ እና ጠበቃ አቶ ቶፊቅ በድሩ፣ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 19 ላይ "የተያዙ ሰዎች በ48 ሰዓታት ዉስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት አላቸዉ" ቢልም ይህ ድንጋጌ ተጥሶ እስካሁን ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከ20 ቀናት በላይ የሆናቸው ታሳሪዎች መኖራቸውን ገልጿል።
የህግ ባለሞያዉ እንደሚለው ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረዉ የዞኑ ምክር ቤት ስብሰባ በገዢው መንግስት የቀረበውን የክላስተር አደረጃጀት ምክረ ሀሳብ ዉድቅ ያደረጉት አባላት ተለይተው እንዲታሰሩ እየተደረጉ ሲሆን "አብዛኞች የምክር ቤት አባላት የሰሩት ወንጀል ሳይኖር ያለፍርድ በእስር ላይ ይገኛሉ" ብሏል።
የጉራጌ ዞን የህዝብ ተወካይና የክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ታረቀኝ ደግፌ ከአዲስ ዘይቤ ጋር ባደረጉት ቆይታ "በየጊዜው በሚቀያየረዉ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ምክንያት ወጣ ገባ የነበረ ጥያቄዉ በህዳር ወር 2011 ዓ.ም. በዞኑ ምክር ቤት አባላት በሙሉ ድምፅ በክልል መደራጀት እንፈልጋለን” በሚል ከፀደቀ በኃላ የመዋቀር ጥያቄ በድጋሚ መነሳሳቱን ተናግረዋል።
በጉራጌ ዞን ህዝብ እስካሁን ድረስ እያነሳ በሚገኘዉ የመዋቅር ጥያቄዎች ላይ እጃችሁ አለበት በሚል የሚታሰሩ የብሔሩ ተወላጆች መጨመሩን የሚናገሩት የክልሉ ምክር ቤት አባሉ አቶ ታረቀኝ “ከ1987 ጀምሮ ጥያቄዎችን አንስተዋል፣ ተሟግተዋል የተባሉት ወጣትና አዛዉንቶች ለስቃይን እንግልት እንዲዳረጉ በተጨማሪ ከስራ ገበታቸዉ እንዲሰናበቱና ከማህበራዊ አገልግሎቶች እንዲታገዱ ሆነዋል” ብለዋል።
ጉራጌ ክልል ቢሆን "የራሱን ገቢ ያመነጫል፣ የተለያዩ የኢንዱስትሪ አማራጮችን ወደ አካባቢዉ በማምጣት ያድጋል፣ ከፌደራሉ መንግስት ጋር በቀጥታ በማናቸዉም ጉዳዮች መደራደር ይችላል፣ በመሰረተ ልማት በቂ ትኩረት ያልተደረገበት አካባቢዉን ማልማት ይችላል፣ በተጨማሪም ህዝብ ቋንቋዉንና ባህሉን እንዲያሳድ ያግዛል” የሚሉት የክልልነት ጥያቄ የሚደግፉ የብሔረሰቡ ተወላጆች ናቸዉ።
ከ28 ዓመታት በላይ የክልልነት ጥያቄዎችን እያነሳ የሚገኘዉ የጉራጌ ዞን በሶስት ክልሎች የተከፋፈለዉንና ስያሜዉን እንዲሁም አደረጃጀቱን ለመቀየር የመጨረሻ ምዕራፎች ላይ የሚገኘዉን የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስር ከስልጤ፣ ሃዲያ ፣ ሀላባ እና ከምባታ ጠምባሮ ዞኖች እንዲሁም የም ልዩ ወረዳ ጋር በአንድ ላይ በመሆን "ማዕከላዊ ኢትዮጵያ" ክልል ይመሰርታሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህን ዉሳኔ በመቃወም የክላስተር (ኩታ ገጠም) አስተሳሰብ በህገ መንግስቱ ላይ ያልሰፈረ እና ወደ ማህበረሰብ ወርዶ ጥናት ያልተደረገበት በመሆኑ ተቀባይነት የለዉም የሚሉት የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ታረቀኝ ደግፌ "ጥያቄዉ የህልዉና ጉዳይ ነዉ" ብለዋል።