ታህሣሥ 10 ፣ 2015

የሰራተኞች እድገት እና ቅጥር መታገደ ጫና እንደፈጠረባቸው የደቡብ ክልል ሰራተኞችና ስራ ፈላጊዎች ገለፁ

City: Hawassaማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮች

አንድ ተቋም አዲስ ሰራተኛ የሚያስፈልገው ከሆነ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥያቄ አቅርቦ ካቢኔዉ ካመነበትና ዉሳኔ ከተሰጠበት ነው አዲስ ቅጥር የሚፈፀመው

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

የሰራተኞች እድገት እና ቅጥር መታገደ ጫና እንደፈጠረባቸው የደቡብ ክልል ሰራተኞችና ስራ ፈላጊዎች ገለፁ
Camera Icon

Credit: Addis Zeybe

በደቡብ ክልል በሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር እንዲሁም የደረጃ እድገት በመታገዱ ምክንያት ተመራቂዎች ስራ ለማግኘት እና ሰራተኞች ደግሞ ለስራ መደራረብ መጋለጣቸውን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዉስጥ በኃላፊነት ደረጃዎች ተቀጥረዉ የሚሰሩ አመራሮች በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገሩት “በአንድ የስራ ክፍል ውስጥ ከ10 ሰዉ በላይ በሚያስፈልግበት የስራ መደብ በሁለትና በሶስት ሰዉ ብቻ እየተሰራ ይገኛል” ብለዋል።

ለደህንነታቸው ሲሉ የሚሰሩበት ተቋምና ስማቸዉ እንዲገለፅ ያልፈለጉ ኃላፊዎች እንደሚያስረዱት “ከደቡብ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት በመጣ ትዕዛዝ” አዲስ ሰራተኞችን ማስታወቂያ አዉጥተው መቅጠር እንዳልቻሉና ለሰራተኞችም የደረጃ እድገት ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

በክልሉ በከምባታ ጠምባሮ፣ በሀዲያ፣ በሀላባ፣ በጉራጌ፣ በስልጤ እንዲሁም በሌሎች ዞኖች ዉስጥ አዲስ ዘይቤ ባደረገችው ማጣራት ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ታህሳስ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ፤ ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር እና ለነባር ሰራተኞች የሚደረግ የደረጃ እድገት መታገዱን ለማወቅ ተችሏል።

በሀዲያ ዞን ውስጥ ካሉ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት እየሰራ ያለ እና በተመሳሳይ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ግለሰብ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረው በሚሰራበት ተቋም ዉስጥ "አዲስ ሰራተኞች የሚያስፈልጉባቸው ክፍት የስራ ቦታዎች ቢኖሩም በተጣለዉ እገዳ ምክንያት መቅጠር አልቻልንም፤ በዚህ ምክንያት በግዴታ ክፍት የሆኑ ቦታዎችን ለመሸፈን አንድ ሰራተኛ ተጨማሪ ስራ ያለ ክፍያ እያሰራን ነው" ብሏል።

ሌላኛው በከምባታ ጠምባሮ ዞን ዉስጥ በሚገኝ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥራ በመስራት ላይ የምትገኘዉ ወ/ሮ አልማዝ ትዕግስቱ (ለዘገባዉ ሲባል ስሟ የተቀየረ) እንደተናገረችው "እገዳዉ ያመጣዉ ጫና ከፍተኛ በመሆኑ በትርፍ ሰዓትም እንድንሰራ ይደረጋል" በማለት ገልፃ "ቀኑ በትክክል መቼ እንደሆነ እርግጠኛ ባልሆነም የስራ ቅጥር በመቆሙ የስራ ጫና ፈጥሮብናል" ብላለች።

በክልሉ የስራ ቅጥር መቆሙ ከመንግስት ሰራተኞችና ተቋማት በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ስራ ፈላጊዎች ላይ ጫና ፈጥሯል። ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀዉ ስራ ማግኘት ያልቻሉ ወጣቶች የተጣለዉ እገዳ መቼ እንደሚያበቃ በግልፅ ባለመቀመጡ ስራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲሄዱ ማስገደዱን ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸዉ በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች በግብርና እንዲሁም በሌሎች የትምህርት ዘርፎች መመረቃቸውን እና በመንግስት ተቋማት ዉስጥ ምንም አይነት የስራ እድል እንደሌለ ገልፀዋል። “ተመርቀን ቤተሰቦቻችን ላይ ሸክም ከመሆን ባለፈ ስራ ለማግኘት ያለ ፍላጎታችን ከመኖሪያ አካባቢያችን ወደ ሌሎች ቦታዎች እንድሄድ ሆነናልም” ይላሉ።

የደቡብ ክልል መንግሥት በበኩሉ የአዲስ ሰራተኞች ቅጥርና የደረጃ እድገት መታገዱ በደቡብ ክልል ብቻ የሆነ ሳይሆን እንደ ሀገር የተቀመጠ አቅጣጫ ነዉ ሲል ለአዲስ ዘይቤ አስታውቋል። የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ፎላ "ችግሩ በደቡብ ክልል ብቻ የተፈጠረ ሳይሆን በሀገር ደረጃ የተቀመጠዉ አቅጣጫ ተግባራዊ በመሆኑ ነዉ" ብለዋል።

የአዲስ ቅጥር እና የደረጃ እድገት መታገድን ተከትሎ አሁን ያለውን የቅጥር ሂደት በተመለከተ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰዉ ሀብት ልማት ቢሮ የሚከተለው አሰራር “አንድ ተቋም ሰራተኛ የሚያስፈልገው ከሆነ ለርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄ ያቀርባል፤ በመቀጠልም ካቢኔዉ ካመነበት ዉሳኔ ይሰጣል ቅጥሩም ይፈፀማል” ሲሉ የተቋሙ የኮምኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ወ/ሮ ፍሬህይወት ገልፀዋል።

ከግንቦት ወር 2014 ዓ.ም. ወዲህ ታግዶ ያለዉ የሰራተኞች ቅጥር እገዳ ሊነሳ የሚችልበትን የተቆረጠ ቀን በተመለከተም ኃላፊዋ “እስካሁን ቁርጥ ያለ ቀን ባይኖርም ነገር ግን እየተደረገ የሚገኘዉ የፖሊሲ ጥናት ሲያልቅ” እንደሚሆን ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። 

ይህን ችግር ይፈታል ተብሎ የታመነበት የፖሊሲ ጥናት ምንን ያካትታል የሚለዉን እና ከእገዳው ጋር በተያያዘ እየተነሳ ያለዉን ጥያቄ በሚመለከት ምላሽ ለማግኘት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰዉ ሀብት ልማት ሚኒስቴርን ምላሽ ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

አስተያየት