ሰኔ 3 ፣ 2013

አስገራሚ ክልከላዎች

ህግበብዛት እየተወራ ያለጉዳይ

በአብዛኛው የዓለም ሀገራት የሰብአዊ መብት እስከመሆን የደረሱ ነጻነቶች ሌላ ሀገር ላይ ተከልክለው እስከ “ሞት” ቅጣት ያስፈርዳሉ፡፡

አስገራሚ ክልከላዎች

ሰሜን ኮርያ በርካታ አስገራሚ የክልከላ ሕጎች ካሏቸው ሀገራት ውስጥ ትመደባለች፡፡ በሌሎች የዓለም ሀገራት የሰብአዊ መብት እስከመሆን የደረሱት እነዚህ ነጻነቶች የሐገሪቱን የመጨረሻ ቅጣት “ሞት” ያስፈርዳሉ፡፡ የስልክ እና የኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ፣ የሙዚቃና የፊልሞችን ማድመጥና መመልከት ስለሚቻልበት መንገድ፣ ስለ አለባበስ እና የጸጉር ቁርጥ፣ የስም አወጣጥ፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ… ላይ የተደነገጉት ሕጎችና የተቀመጡት ክልከላዎች እንዲሁም ሕጉን የተላለፉ ሰዎች የሚጠብቃቸው ቅጣት በሌሎች የዓለም ሐገራት ለሚኖሩ ሰዎች በድንቃድንቅ ዜናነት የሚነገሩ ናቸው፡፡

 የኪነጥበብ ውጤቶች

 ሰሜን ኮርያ አስገራሚ ሕጎች አንዱ የውጭ ሐገራት ፊልሞች እና ሙዚቃዎች ላይ ያለው ክልከላ አንዱ ነው፡፡ የሰሜን ኮርያ ባለሙያዎች ካዘጋጇቸው ሀገር በቀል የጥበብ ሥራዎች ውጭ የሌሎች የዓለም ሐገራትን ሙዚቃም ሆነ ፊልም መመልከት ወንጀል ነው፡፡ ሰሜን ኮርያውያን ይህንን በሕግ የማይፈቀድ ‘ወንጀል’ ፈጽመው ከተገኙ (የሌሎች ሐገራትን ፊልሞችና ድራማዎች ሲመለከቱ፣ ሙዚቃዎች ሲያደምጡ፣ የሙዚቃ ቪድዮዎችን ሲያዩ) ከተገኙ እስከ ሞት የሚደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል፡፡ ሙዚቃዎቹ እና ፊልሞቹ የጃፓን፣ የአሜሪካና የደቡብ ኮርያ ከሆኑ ቅጣቱን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ከ15 ዓመት እስራት የሚጀምረው ቅጣቱ የሞት ቅጣት ድረስ ይራዘማል፡፡ ፊልሞችን ማከማቸት ወይም በርከት ያሉ ፊልሞችን ይዞ መገኘት ከመመልከት የከፋ ቅጣት የሚያስከትል ‹ሕገ-ወጥ› ተግባር ነው፡፡ ከተጠቀሱት ሀገራት ውጪ ያሉ (ለምሳሌ ህንድ) ፊልሞችን መመልከት እስራት ብቻ ሊያስቀጣ ይችላል።

ቢቢሲ የዐይን እማኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው አንድ ሰሜን ኮሪያዊ የደቡብ ኮርያ ድራማ በመመልከቱ ምክንያት በሞት ተቀጥቷል፡፡ ቅጣቱ ሲፈጸም የአካባቢው ነዋሪዎች በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ መገደዱን በውቅቱ የ11 ዓመት ታዳጊ የነበረች የዐይን እማኝ ተናግራለች፡፡ 

በሀገሪቱ ሕግ መሰረት ፊልሞቹን በመመልከታቸው ተጠያቂ የሚሆኑት የድርጊቱ ፈጻሚዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ‹ወንጀል› ፈጻሚው በቤተሰብ ቁጥጥር ውስጥ ያለ ታዳጊ ከሆነ ቤተሰቦቹም በሕግ ተጠያቂ ይሆናሉ፡፡ የድርጊቱ ፈጻሚ ተቀጣሪ የሆነ እንደሆነ ደግሞ አሰሪዎቹ በቀጠሩት ሰው ድርጊት የሚጠየቁ ይሆናል፡፡

የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች

ከሙዚቃ እና ፊልሞች በጨማሪ ከተጠቀሱት ሐገራት የሚተላለፉ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ወይም ዜና ወይም ሌሎች መዝናኛዎች መከታተልም በሕግ ከተከለከሉ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ ይመደባል፡፡

አንድ ሀገሩ ላይ የሚኖር የሰሜን ኮርያዊ ሦስት በመንግሥት የሚተዳደሩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን እንዲታደም የሚፈቀድለት ሲሆን ተጨማሪ የመረጃ ወይም የመዝናኛ አማራጮችን ከፈለገ የመንግሥትን ቅጣት ለመጋፈጥ መቁረጥን ይጠይቀዋል፡፡ 

ልዩ ልዩ

ሙያ- ዜጎች የት መኖር እና በምን ሙያ መስማራት እንዳለባቸው የሚወሰነው በመንግሥት ነው።

እንቅስቃሴ- ከሰሜን ኮሪያ ወደ ሌላ ሀገር ያለ ፈቃድ መንቀሳቀስ ክልክል ነው፡፡ ክልከላውን የተላለፈ ግለሰብም ከባድ ቅጣት ይጠብቀዋል።

ቱሪስቶች- ሀገሪቱን ለመጎብኘት የሚመጡ ቱሪስቶች የኮሪያን ምድር ሲረግጡ ስልክ እና ኮምፒውተራቸውን ለመንግሥት አስረክበው ወደመጡበት ሲመለሱ መልሰው የሚረከቡበት አሰራር አለ፡፡

ፕሬዝዳንቱ- የሰሜን ኮርያን ፕሬዝደንት ቤተሰብ ክብር የሚነካ ማንኛውም ድርጊት ወንጀል ነው፡፡ ፕሬዝደንቱ በሚናገሩበት ስብሰባ መሀል መተኛት ወይም ማሸለብ ወንጀል ነው።

መኪና መንዳት- ሴቶች መኪና መንዳት አይችሉም፡፡ ሴቶች መኪና አይንዱ እንጂ ትራፊክ ፖሊስ ሆነው ማገልገል ይችላሉ፡፡ 

የጸጉር ቁረጥ- ለሴቶች እና ለወንዶች የጽጉር አቆራረጥ ዘዬዎች በመንግሥት ቀርበዋል፡፡ መንግሥት ካዘጋጃቸው ከ10 በላይ ቁርጦች ውስጥ መርጦ ጸጉርን ማሳመር ይቻላል እንጂ አዲስ ዘዬ ፈጥሮ ራስን ለማሳመር መጣር አይፈቀድም

ጅንስ- ሰማያዊ ቀለም ያለው ጅንስ መልበስ አይፈቀድም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ ጅንስ የምእራባዊያን አስተሳሰብ ነው በሚል እምነት ነው፡፡ አስገራሚው ነገር የጅንሱ ቀለም ሰማያዊ ካልሆነ መልበስ መፈቀዱ ነው 

አጭር ቀሚስ- ሴቶች አጭር ቀሚስ ከለበሱ ሰውነታቸው እንዳይታይ ሌላ ልብስ (ታይት) መደረብ ይጠበቅባቸዋል

ስም- ማንኛውም ኮርያዊ በፕሬዝደንቱ ስም መጠራት አይችልም፡፡ ለራሱም ሆነ ለልጁ ‘ኪም ጆንግ ዑን’ በሚል መጠሪያ መገልገል ክልክል ነው፡፡ ይህ ሕግ ከመውጣቱ በፈት ስያሜውን የተጠቀሙ ግለሰቦች ስማቸውን እንዲያስቀይሩ ሕግ ወጥቷል፡፡

አስተያየት