ሰኔ 18 ፣ 2010

“የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ” እንደሆነ አየሁ!

ፖለቲካባሕልታሪክ

ሀ. ሁሉም መንገዶች ወደ መስቀል አደባባይ ያመራሉ!አይነጋ የለም፤ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ተመመ፡፡…

“የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ” እንደሆነ አየሁ!

ሀ. ሁሉም መንገዶች ወደ መስቀል አደባባይ ያመራሉ!አይነጋ የለም፤ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ መስቀል አደባባይ ተመመ፡፡ እንደውም ከፊሉ ሕዝብ ዋናውን የመሰብሰቢያ ቦታ ቀድሞ ለመያዝ በሌሊት ገሰግሷል፡፡ ጨለማውን ታግሷልና ጸሐይዋ ሥትወጣ የዓይን ምሥክር ለመሆን መቸኮሉ አይገርምም፡፡  ይህ ሕዝብ የምስጋናና የድጋፍ ጽሁፍ የሰፈረባቸውና በአብዛኛው የዶ/ር ዐቢይ ምስል የታተመባቸው ቲሸርት ለብሷል፡፡ የአቶ ገዱና የአቶ ለማ ምስል ያረፈባቸውን የለበሱም ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሚጓዝበት ሁሉ ይዘምራል፤ ይጨፍራል፤ መፈክር ያሰማል፡፡ ካየኋቸው መልክቶች መካከል ደርባባ እህት አበባዎች የለበሱት “አ.ብ.ይ. ንድ ንሆን በጀናል” የሚለው ፈጠራ ትኩረቴን ስቦት ነበር፡፡ አንዱ ኢትዮጵያዊ ጸጉሩን በራስተፈሪያን ልማድ የጎነጎነ ጎልማሳ ያነገበው ደግሞ “አሁን መኖር አማረኝ!” ይላል፡፡ እውነት ብሏል፡፡ በዕለቱ የነበረው የጉጉት፤ የደስታና የተስፋ መጠን በቃላት አይገለጽም፡፡ ብዙ አይነት ሰንደቅ ዓላማዎች በብዛት ይውለበለቡ ነበር፡፡ መስቀል አደባባይ  እንኳን በሰልፉ ለተመለከትናቸው ታላላቅ ምልክቶች ለሌላም ሰንደቅ ዓላማ አይጠብም፡፡ እውነት ለመናገር  በሰልፉ እንደልቡ የናኘው  የኢትዮጵያው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ነበር፡፡  ይህን በዓይኑ ያየ ታዛቢ አገሩ የኢትዮጵያውን እንደሆነ ይረዳል፡፡ ወንድ፤ ሴት፤ ወጣት፤ ጎልማሳና ሽማግሌ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሰንደቅ ዓላማዎች ፋና ወጊነት ከያቅጣጫው እንደታላቁ ግዮን ወንዝ ፈለጉን ተከትለው ሲፈሱ አርፍደዋል፡፡ ለዘመናት “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ” ሲባል ኖሯል፡፡ በዕለተ ቅዳሜ ሰኔ 16 2010 ዓ.ም. ግን ያለምንም ማጋነን በመዲናዋ እና በዙሪያዋ ያሉ መንገዶች ሁሉ ወደ መስቀል አደባባይ አምርተዋል፡፡ለ. የ97 ሰልፍ አምሳያውን አገኘ!ሰልፉ ግዙፍ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መስቀል አደባባይ አልበቃውምና በያቅጣጫው መንገዱን ተከትሎ ባገኘው ሥፍራ ሁሉ ተመመ፡፡ የግዝፈቱ ምክንያት በአዲስ አበባ እና በዙሪያ ባሉ ከተሞች የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ስለተሰለፈ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሰልፈኛው በሚሊዮኖች ይገመታል፡፡ ግን ግን በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የኢትዮጵያዊ ብዛት ስንት ነው? ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት የሌለው ከተሜ ቁጥሩን ባይታወቅ ምን ይገርማል?አዲስ አበባ ይህን መሰል ግዙፍ ሰልፍ ያስተናገደችው በምርጫ 97 ወቅት ነበር፡፡ ብዙዎች በዕለተ ሰንበት የተካሄደውን የመጀመሪያውን እና በቀዳሚት ሰንበት የዋለውን የአሁኑንን ለንጽጽር ማስታወሳቸው ልክ ነበር፡፡ በእርግጥ አዲስ አበባ ከሰኔ 16፣ 2010 ዓ.ም. ሆነ ሚያዝያ 30፣1997 ዓ.ም. የሚቀድም ታላቅ ሕዝባዊ የፖለቲካ ሰልፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደችው በሚያዝያ 12፣1966 ዓ.ም. እንደሆነ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያውያን ለኃይማኖት እኩልነት በጋራ ወደ አደባባይ በመትመም ሙስሊም ክርስቲያኑ በጋራ ተሰልፈው ድምጻቸውን አሰምተው ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ በዚህ ትውልድ ዘመን የ1997 ሕዝባዊ ሰልፍ ከ13 ዓመታት የብቸኝነት ዝና በኋላ በ2010 ዓ.ም. አምሳያውን አግኝቷል፡፡ሐ. ኦሮሞዎች ለማን ብለው ኢትዮጵያን ይተዋሉ? በከተማና በገጠር የሚኖሩ ማህበረሰቦች ያለምንም የካድሬ ቅስቀሳና የቀበሌ አስገዳጅነት ወደ መስቀል አደባባይ በዚህ መጠን ለመጀመሪያ ጊዜ የመጡት በሰኔ 16 ሰልፍ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በርግጥ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ርዕሰ ብሔር በሆኑበት የአብዮቱ ዘመን የአዲስ አበባ ዙሪያ ፈረሰኛ ኦሮሞዎች ለጄኔራሉ ድጋፍ መጥተው እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል፡፡ በሰኔ 16 ሰልፍ የኦሮሞ ፈረሰኞች ወደ አደባባዩ በሚገቡበት ጊዜያት የነበረው የደስታ ጩኸት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል የፍቅር ሕዝብ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ ማህበረሰቦችና የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ያለ ኦሮሞ ተስፋ የላትም፡፡ ኦሮሞዎች ዘመናዊት ኢትዮጵያን መስርተዋታል፤ ገንብተዋታል፤ ሞተውላታል፡፡ ለመሆኑ ኦሮሞዎች ለማን ብለው ኢትዮጵያን ይተዋሉ? ታሪክ እንደሚያስረዳን ዋናዎቹ እጩዎች እነሱ አይደሉምን? በሌላ በኩልም ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን ቢተዋት ብዙ ይጎዱበታል፡፡ ለጥቂት አሥርት ዓመታት እንደታየው ኦሮሞዎች ከውስጣቸው ኢትዮጵያን ለማውጣት በሞከሩ ጊዜ ፍቅራቸውን፤ ርህራሄያቸውን፤ ትሕትናቸውን፤ ሰው ወዳድነታቸውን፤ ሰው አቃፊነታቸውን፤ ሕግ አክባሪነታቸውን፤ ባህላቸውንና ሥልጣኔያቸውን ያጡታል፡፡ በአጠቃላይ ኦሮሞነታቸው ይሸረሸራል፡፡ ይህ ሐቅ ነው፡፡መ. ዶ/ር ዓብይ መንፈስ የሚያጠግብ ነገር ተናገሩን፤ጎንበስ ብለውም እጅ ነሱን!የኔልሰል ማንዴላ ምስል ያረፈበት ሎሚ አረንጓዴ ቲሸርትና ክብ ባርኔጣ አጥልቀው የመጡት  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንደተለመደው ልብን የሚያርስ ንግግር አደረጉ፡፡ ንግግራቸው አሁንም፤ አሁንም በአድናቆት ጩኸት ይቆራረጥ ነበር፡፡ እንደወትሮው ሁሉ ብዙ ሃሳቦች አንስተዋል፡፡ በንግግራቸው ያነሱዋቸው ሐሳቦች በግፍና ጡር ባለመፍራት የኢትዮጵያውያን ቁሳዊና መንፈሳዊ ሕይወት ያቆረቆዙትንና ያቆሰሉትን አሰራሮችንና አመለካከቶች ያወገዙበት ነበሩ፡፡ ዘረኝነት፤ ጥላቻ፤ ሌብነት፤ ፍርደ-ገምድልነት፤ ራስ ወዳድነት ያልተነሳ ነቀርሳ አልነበረም፡፡ በእነዚህ ሰንኮፋዎች የአብዛኛው ሕዝብ መንፈስና ኑሮው ለዓመታት ታውኮ፤ተረብሾና ተመሳቅሎ  ነበርና ዶ/ር ዐቢይ በአንደበታቸው አከሙት፤ በአስገምጋሚው ድምጻቸው አጽናኑት፤ በተከሸኑ መልካም ቃላት ፈወሱት፡፡ የብሔር መገፋት ይብቃ አሊያ ቅኝ ገዢዎች ከዚህ በላይ ምን አደረጉ አሉ፡፡ የሐይማኖት አባቶችንም ፍርድ ሲጓደል፤ ደሀ ሲበደል ዝም አትበሉ አሉ፡፡ ሕዝቡንም አደራም አሉት፡፡ “አይጥ በበላ ዳዋ አይመታ!”እኚህ መሪ ከኢትዮጵያውያን ልብ ሌላ ሁለተኛ ሀገር እንደሌላቸው በየጊዜው እያሳዩ ነው፡፡ በዜጎች ፊት ራሳቸውንም ዝቅ አርገው ስለ ሰብዓዊነት መቆርቆራቸውን እያሳዩ ነው፡፡ የታሰሩትን፤የታመሙትን፤የተፈናቀሉትን ይጎበኛሉ፡፡ በመስቀል አደባባይም እኛን ሰልፈኞችን ጎንበስ ብለው በትሕትና እጅ ነስተውናል፡፡ እንዲህ ያለ መሪ ታይቶ ያውቃልን?ሠ. የፈነዳው ቦምብ ተሥፋን ለማጨለም፤ደስታን ለማጉደል አልቻለም፡፡ ከጸጥታና ከደህንነት ጋር በተያያዘ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለመደ ጨዋነቱና ሰላም ወዳድነቱ ሰልፉን በስኬት ጀምሮ በድል አጠናቋል፡፡ የጸጥታ ኃይሎችም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ግን ደግሞ መሰሪ አሻጥሮችና የጥፋት ድግስም እንደነበረ አይተናል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪዎች በጋዜጣዊ መግለጫዎች እንዳስታወቁት አንበሳ ሕንጻ ላይ ለእኩይ ድርጊት የተዘጋጁ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንዲት የፖሊስ መኪናም ለጥፋት በመድረክ አቅራቢያ ለልዩ ዓላማ ተዘጋጅታ እንደነበር ተግለጿል፡፡ አስተባባሪዎቹ እነሥዩም ተሾመ የይለፍ መታወቂያ ይዘውም እንዳያልፉም ታግደዋል፡፡  ከጠ/ሚኒስትሩ ንግግር በኋላም የቦምብ ጥቃት ተፈጽሟል፡፡ ለፍቅርና ለአንድነት የጓጉ ብርቅ ኢትዮጵያውን በቀን ጅቦች ተገድለዋል፡፡ እልቂት የደገሱ ኃይሎች በርግጥ ቢሳካላቸው አዲስ አበባን ሰኔ 16 ቀን በደም አበላ ሊያጥቧት ይችሉ ነበር፡፡ የመጠፋፋት ዘመን እያበቃ እንደሆነ ህዝቡ ለዚህ ቁርጠኝነት እንዳለው የሚያስረዳው ሰልፉ ቦምቡ በፈነዳበት እጅግ ውስን ቦታ ብቻ  በተፈጠረ ግርግር ለጥቂት ጊዜ ወዲያውኑ ሚሊዮኖች በምስጋናና በመደመር ሰልፉ መቀጠላቸው ነው፡፡ረ. ዘመናችን ለኢትዮጵያ ያበረከታቸው የትውልዱ ሥጦታዎች ሰልፉን አስተባበሩት! ጉደታ ገላልቻ፤ ሥዩም ተሾመ፤ አበበ ቀስቶ፤ ሥንታየሁ ቸኮል እና ሌሎችም ቁርጠኛ ኢትዮጵያውያን በልበ ሙሉነት ሰልፉን አስተባብረውታል፡፡ የሰልፉ አስተባባሪዎች የትግል ጽናት በርግጥም   የጀግንነት ትርጉሙ በረሀ ገብቶ ሰው መግደል ለሚመስላቸውና ይህም እምነታቸው ኃላፊነት ለጎደለው እብሪት ለዳረጋቸው ጥቂት ጥጋበኞች ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ከብዙ የኢትዮጵያ ባለውለታዎች መካከል እነ ሥዩም፤ እነ ጉደታ፤እነ አበበ    እነ ሥንታየሁ በርግጥም ዘመናችን ለኢትዮጵያ ካበረከተላት የትውልዱ ሥጦታዎች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ጀግኖችን በማፍራት በኩል መቼም መክና እንደማታውቅ  አስተባባሪዎቹ ጥቂት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ አገር ናት የሚባለው ሌላ ሳይሆን የኢትዮጵያ ልጆች በየዘመኑ ታሪክ ይሠራሉ ማለት ነው፡፡ የልጆቿ የዘወትር ሕልምም በተቻለ መጠን ታሪክ መሥራት ነው፡፡ አስተባባሪዎቹ እና ሚሊዮኖች ከብዙ አሻጥር አልፈው  ሰኔ 16 ታሪክ ሠሩ! የእልቂት ድግሱም በምንተነትነውም መተንተንም በማችለው ረቂቅ መንፈስ ሳይሳካ ቀረ፡፡ በእርግጥ ሁከትና እልቂቱ በመቀልበሱም ቅዳሜ እለት “የሕዝብ ድምጽ የእግዜር ድምጽ” እንደሆነ አየሁ!

አስተያየት