ሰኔ 22 ፣ 2010

ጠ/ሚ ዐቢይና ሠልጣኝ “አርቲስቶቻችን”

ፖለቲካባሕል

ሀ. “[ጠ/ሚኒስትር] ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ግን ደግሞ…ሰዉ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ እንዳልደገፈዎት አውቃለሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ገናናነት፣ ስለ ዘረኝነት…

ጠ/ሚ ዐቢይና ሠልጣኝ “አርቲስቶቻችን”
ሀ. “[ጠ/ሚኒስትር] ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ግን ደግሞ…ሰዉ እንዲሁ ከመሬት ተነስቶ እንዳልደገፈዎት አውቃለሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ገናናነት፣ ስለ ዘረኝነት ጠንቅ፣ ስለ ዝርፊያ ነውርነት እና ሌሎችም ነፍስ አባቴ (አለኝ ግን?) አደራ በምድር አደራ በሰማይ ብለው የሚመክሩኝን መንፈሳዊ ጉዳዮች በየጊዜው ብቅ እያሉ ተስፋ ለናፈቀው ሕዝብ ስለነገሩት (ሕገ-መንግስቱ ኃይማኖትና መንግሥት ተለያይቷል ቢልም) እርስዎን መደገፉ ግልጽ ነው፡፡ በተጨማሪም የገዛ ራስዎ መንግሥት ያሰራቸውን ኢትዮጵያውን እርስዎ ስለፈቱ፣ የተሰደዱትን ስላስመጡ እንደተወደዱም አይጠፋኝም፡፡ በዚህ በዚህ እንዲያውም አንዳንድ አማኞች ከእግዜር እንደተላኩ ያምናሉ፡፡ ይህ ጽሑፍ ለመካነ-ድር ስርጭት እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔርም “እንዲህ ያለ ሰው እኔ አልላኩም!” ብሎ ሳላላስተባበለ በበኩሌ የምለው የለኝም፡፡ የሰሯቸውን ሥራዎች ግን እንዲሁ በቀላሉ አላያቸውም፡፡ “ሺህ ዓመት ያንግሳቸው” ብዬ ላንድ ወዳጄ ስሜቴን ባካፍለው በ2012 ዓ.ም. ምርጫ አለኮ አለኝ፡፡ ምናለበት ምርጫ ቦርድ በይቅርታ ቢያልፈው? ዘመኑ የዚያ ነው ተብሏል፡፡…ግን ደግሞ አርቲስቶችን በተመለከተ ሲበዛ ግብዝ ሆነው አግኝቼዎታለኹ፡፡ የእርስዎ ይቆይና በአርቲስቶቹ ልጀምር፡፡ለ. ክፉ አመል አይለቅም፤ የጥሪው ወረቀት በግልጽ ያስቀመጠውን እንደጴጥሮስ ደጋግሞ መካድሰልጣኝ አርቲስቶች፣ አሰልጣኝ ጠ/ሚኒስትር፣ የሥልጠናው ርዕስ፣ ከማይንድ-ሴት (mind-set) እስከ ፈረደበት ቅዱስ ያሬድ ድረስ ሆኖ እያለ “ይህ ነገር እንዴት ነው?” ብዬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኪነ-ጥበብ ማኅበረሰብ በሚሰጡት ስልጠና ላይ አንዲገኙ ለተጋበዙ ወዳጆቼ ከሰጡኝ መልስ ከፊሉ እንዲህ ይላል፡፡ “የባህል ሚኒስትር ስህተት ነው!”፣ “አሁን እሱ ይሄን የሚያየው ይመስልሃል?!” ፣“ስልጠና አይደለም ውይይት ነው”፣ “አሻጥር የሚሰሩ የቀን ጅቦቹ ስራ ነው”  አብዛኛዎቹ ጊዜው እስኪደርስ በእግር ጣት እንደቆሙ ጠቅሰው (አንዳንድ አርቲስቶች ከቤተ-መንግሥት ሲደወል እንዲህ ያረጋቸዋል) የጥሪ ወረቀቱን በየገጾቻቸው ለጥፈውት ነበር፡፡ የጥሪው መግቢያ “ጉዳዩ:- የስልጠና ጥሪን ይመለከታል” ይላል፡፡ በማስከተልም ዓላማውንና የሠልጣኝ እና አሰልጣኝ ግኑኝነት በግልጽ አስቀምጦ በክብር እንዲገኙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ ቀጣይ ነጥቦችን ከማንሳት በፊት እዚህ ላይ ሊባል የሚገባው ነገር ግን አለ፡፡ ብዙዎቹ አርቲስቶች ከሆነው ነገርና ካለው ሐቅ ይልቅ የጥበብ ጥብቅና ልዕልናዋና እውነት በሆነበት ሁኔታ ወረቀቱ ላይ በግልጽ የተቀመጠውን ነገር መካድ ለምን አስፈለጋቸው? ስለፍትህና እውነት ይሞግታሉ ተብሎ የሚጠበቁ ጠቢብ ሆነው ሳለ እንዲህ ያለው ነገርን በግልጽ ዓይን በመካድ ለአገር ይጠቅማል የሚባለውን ማህበራዊ ሐቅ እንኳን አንዴት ሊያቀርቡ ይችላሉ? መልሱን ለእናንተ እተዋለው፡፡ሐ. ድኅረ ሥልጠና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክተራቸውን ወጥረው በፓወር-ፖይንት (power-point) የታገዘ ሀሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ ኪነ-ጥበብ ምንድን ነው? ከያኒስ ማን ነው? ከሚለው ተነስተው ጥበበኛው ይሄ ነው የሚባል የሚያስተሳስረን ስራ እንዳልሰራ አውስተው በቀጣይነትም የሕዝብ ለሕዝብ ክዋኔ ፕሮግራም እና ቤተ-መንግስቱ ውስጥ ሊያቋቁሙ ስላሰቡት የኪነ-ጥበብ ማዕከል ለፍፈው፣ ግብር አብልተው አርቲስቶችን ሸኝተዋል፡፡ በመትረየስና በታንክ በሚጠበቅ ግቢ ውስጥ ቀርቶ ውጪ ያሉት የጥበብ ማእከሎች ነጻነት አጥተው በሚቸገሩበት አገር ስለ ቤተ-መንግሥት ኪነ-ጥበብ ማዕከል ማውራት ምን የሚሉት ግብዝነት እንደሆነ አልገባኝም፡፡ መጀመሪያ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ያሉትን መች አሰሩና ነው መትረየስና ቦምብ በሞላው ግቢ ውስጥ አዲስ የኪነ-ጥበብ  ማዕከል የሚወራው? ነው ወይስ ለስሟ መጠሪያ አንድ ቁና ሰፋች ነው?ብዙ ተሳታፊዎች የጥሪው ወረቀት ላይ እንደተቀመጠው ስልጠና ሳይሆን የማይንድ ሴት (mind-set) ፕሮግራም (program) ነው በሚለው ይስማማሉ፡፡ ምንም ዓይነት ጥያቄና መልስ ያልነበረበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥበብ እንዴት ለአገር ጥቅም መዋል አለበት የሚለውን የደሰኮሩበትና በማያሻማ መልኩ ለመሰልጠናቸው ጉንጭ ማልፋት ሳያስፈልግ ማይንድ ሴት ነው የሚሉትን ብንቀበል እንኳን የነገሩን ነውርነት የበለጠ ያጎለዋል እንጂ አይቀንሰውም፡፡መ. ከሙያ ውጪ ሄዶ ማሰልጠን፤ ነውር + ድፍረት + 500 = ጥፋትበመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የባህልና… ሚኒስትር መስሪያ ቤትን ዘለው በቀጥታ እርሳቸው በአርቲስቶቹ ፊት መቆም ምን አስፈለጋቸው? ሁለተኛ ሰበር ዜና ራሱ በተሰበረበት ፍጹም ተለዋዋጭና ፈጣን በሆነው የፓለቲካ ውጥንቅጥ እውነታ ውስጥ አርቲስቶችን ግብር መጥራት ለምን አስቸኮለ? በመጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስዕል እስከ ሙዚቃ ከቲያትር እስከ ስነጹሑፍና ፊልም ድረስ ያሉ የጥበብ ሰዎችን ለማሰልጠንም ሆነ የአስተሳሳብ አድማስ ለማስቀመጥ የሚያስችል ምን ዓይነት የሞራል ልዕልናም ሆነ የዕውቀት ማዕቀፍ አላቸው? ሶስተኛውን ጥያቄ በተመለከተ ውስጥ ውስጡን ሲወራ የሰማሁት ነገር አለና እኔው ልመልስ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ከመከላከያና ከኢንሳ (INSA) የዕውቀትና የስራ ልምዳቸው ባሻገር የነበራቸውን የኢትዮጵያን የጥበብ ዕውቀት ቀድሞም ወደ ቤተ-መንግሥት ሲያንጋጥ የከሳ እና በወጣትነቱ ጥቂት ሽበት ያወጣ ዝነኛ አጭር ማብራሪያ ቢጤ እና ግንዛቤ አስጨብጠዋቸዋል፡፡ እሷኑ ላፍ አርገው አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ ቤት እኚህ ሁለት የአደባባይ ሰዎች የኢትዮጵያ ጥበብ ዕውቀት ጥግ ናቸው፡፡ ወይ የሚመሩትን አገር አለማወቅ!ይልቅ ከሠራዊት ፍቅሬ አንጃ ተወጥቶ አዳም ረታን ጋሽ ኃይሌ ገሪማን እሸቱ ጥሩነህ እና ቴዲ አፍሮን በመድረኩ አስቀምጦ ስለፍቅር ምሕረትና አንድነት መተረክ አንድምታው ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ይጠቅማል፡፡ ደግሞም የሰላ ትችት ከማቅረብ ወደ ኋላ ያላሉ (ግሩም ዘነበ፣ በረከት በላይነህ)፣ የተሰደዱ (ዓለምፀሐይ ወዳጆ)፣ መንግሥትን በውብ ግጥም በመተቸቷ በሰራዊት ፍቅሬና በሸዋአፋረሁ ደሳለኝ አጋፋሪነት በሽመልስ ከማል ቢሮ ውስጥ ማስፈራሪያና ወቀሳ ተሰጥቷት ከስክሪን የጠፋችው ሜሮን ጌትነት ጠርቶ ማናገሩ የአባት ነበር፡፡በትረ-ስልጣናቸውን ከያዙ ገና ሶስት ወር የሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የመጀመሪያ ደረጃ መረጃ ከባለቤቱ መውሰድ፣ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ያለበትን ችግርና ባለቤቱም ከመንግሥት ምን እንደሚጠብቅ ከመስማት ባለፈ መታበይ ፕሮጀክተራቸውን አብርተው ሌክቸር ማድረግ የመረጡበት ድፈረት ባይገባኝም የስሜትና የስነ-ውበት ኃይል ባለቤት የሆነውን የጥበብ ሰው ፊት ሞገስ ማግኝት ትልቅ ትርፍ እንዳለው ሂሳብ መስራት ግን አያዳግትም፡፡ ምልኪውም ለጥበብ ተልዕኮ ማስቀመጥ ሲሆን አመክኖያዊ የተጠየቅ ጥያቄዎችን የሚመልስበት ዩነቨርስቲ የአስተሳሰብ አድማስ የሚሰራበትን ጥበብ ከላይ ሆኖ ልምራ የሚል አገዛዝ መጨረሻው ከተቋም ይልቅ የሰው ትከሻ ላይ የሚያርፍ መሆኑን ማጤን መልካም ነው፡፡[caption id="attachment_719" align="alignnone" width="663"] ሐዊ ተዘራ፣ መንግሥትን የሚቃወሙ ሙዚቃዎችን ለሕዝብ በማቅረቧ ለእስር እና እንግልት የተዳረገች[/caption]የሞራል ልዕልናን በተመለከተ አርቲስቱ የሚጠበቅበትን እንዳልሰራ ለዚህ ማስረጃው ደግሞ ድንጋይ አንወራወር እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይሄ ቀስቱን ወደ እርሳቸው ይመልሰዋል፡፡ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በብሔርና በመከፋፈል ስሌት ስር ቢቆይም የመከፋፈል ተልዕኮውን እንዳይመታ ያደረገው እግዜር በኪነጥበቡ እና ኪነ-ጥበብ ራሷ ነበረች፡፡ እርሳቸው ዛሬ የሚያቀነቅኑት የይቅርታ፣ የምሕረት እና የአንድነት ሐሳብ የወረሱት ሕዝቡ ይፈልገው እንደነበር ተረድተው የሕዝቡን የባህል አድማሱን ደግሞ ኪነ-ጥበብ ትጠብቀው እንደነበር ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ በሙዚቃው ብቻ ያለው ቴዲ አፍፎ የበለጠ አስረጅ ነው፡፡ ዘረኝነትንና የጎጥ ሀሳብን የታደገውን አዳም ረታን ማስታወስም ግድ ይላል፣ የመዝገቡ ተሰማ እውናዊ ስዕሎችንም እንዲሁ፡፡ በተቃራኒው ግን እርሳቸው ለነበሩበት መንግሥት ግን ጥያቄው ቢወረወር ተገቢ ያደርገዋል፡፡ በአገሪቱ ትልቁ የፖሊሲ ሰነድ የትራንስፎርሜሽንና ዕቅድ ንድፍ ስር አንዲትም መስመር ቦታ ያልያዘው የኪነ-ጥበብ ዘርፍ እንዲህ አናት አናቱን ብለነው እንኳን ለዘመን የሚጠቀሱ ስራዎች መበርከታቸው ተአምር ነውና በራሴና በአመራሩ ስም ይቅርታ ልጠይቃችሁና ለሁሉም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ቢሉ የበለጠ ትርጉም ይሰጥ ነበር፡፡በደርግ ጊዜ በዘመቻ መልክ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባህል እንዲያንጸባርቅና ለውጭ እንዲያስተዋውቅ በሰፊው ተሰርቶበት የነበረውን የሕዝብ ለሕዝብ ኪነት ቡድን ስለመድገምና መደራጀት፣ እንዲሁም ቤተ-መንግሥት ውስጥ የኪነ-ጥበብ ማዕከል ስለማቋቋም ያላቸውን አጀንዳም አቅርበው ነበር፡፡ በመሰረቱ ሀሳቡ ክፋት የለውም ነገር ግን ኪነ-ጥበብ በራሷ እንድትቆም የመንግሥት አሸርጋጅነትን ማስወገድ የሚጀምረው ነጻነቷን እንድታገኝ መጫወቻ ሜዳ በመስጠት ነው እንጂ ዳኛ በመሆን አይደለም፡፡ የሐቁ ነጸብራቅ እንድትሆን ማኅበራዊ እውነታውን መቀየር ይቀድማል፡፡ ቤተ-መንግስቱን ጎብኝተን ወጣን ከሚለው ቡረቃ በተለየ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሄዳችሁ አነቃቋቸው የሚል ግልብና የተለመደ ሀሳብ ብቻ አንስተው በትምህርት ስርዓት ሊኖረው ስለሚገባው ጉዳይ አለመወራቱ የበለጠ ያስደነግጣል፡፡ሠ. አሮጌው አቁማዳ ስር ለምን እደመራለሁ?!"ከእንግዲህ ከመጣው ጋር ማሸርገድ ያቆማል" ጠ/ሚ አብይ አህመድ(ዶ/ር)፡፡ ይህ ንግግር በዓለ-ሲመቶ ቀን የኢትዮጵያን ሕዝብ አሸርግደው ባገኙት ስልጣን ማማ ላይ ይቅርታ ከጠየቁ በኃላ ስለሆነ በግሌ ትርጉም ይሰጠኛል፡፡ ሌላው ቢቀር ከይቅርታው ጋር ምን ላይ ቆመሸ ማንን ታሚያለሸን አያስተርትም፡፡ ነገር ግን የሰበሰቧቸው አርቲስቶች አብዛኛዎቹ እንደ እርሳቸው ሕዝቡ የይቅርታ ደብደቤያቸውን ይፈልጋል፡፡ ኧረ… ኅሊና የሚባል ነገር አለ፡፡ አንዳንዱ አርቲስት ደግሞ ይህን ሀቅ የአሉታዊ አመለካከት ነጸብራቅ አድርጎ ወስዶት በማጣጣል ስሜት በማኀበራዊ ሚደያዎች መናገሩ አሳዘነኝ፡፡ ቴዲ አፍሮ ይህን ቢያደርግ ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም የሚሊዮኖችን ድምጽ በጽናትና በቁርጠኝነት  አሰምቷል፤ ለዚህም በልጅነቱ ዋጋ ከፍሏል፡፡ የአገር ጉዳይ የማይጨንቀው፣ የትውልድ ነገር የማያሳስበው የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ተብዬ ጭንጋፍ ሁላ ሲሆን ይቅርታ፣ ካልሆነም ዝምታን ቢመርጥ መልካም ነበር፡፡ተው እንጂ? ከቤተ-መንግሥት በሚወጣ የቀጥታ ጨረታ ብዙ ሚሊዬን ብር የሚቆጠር ሲያፍሱ የነበሩ የማስታወቂያ ባላባቶች፣ ከስምንት መቶ ሺህ በላይ የኦሮሞን ሕዝብ በልዩ ጦር ታጅቦ ሲያፈናቅል ከነበረው አብዲ ኢሌ መስተንግዶ በጉብኝት መልክ ጅጅጋ ከርመው ያገር ፍየል  ሲያነክቱ ቆይተው አንዲትም ነገር ያልተነፈሱት የህግ ባለሙያ ነኝ (እግዚኦ የኦሮሞ ተፈናቃይ አምላክ) አርቲስትም ነኝ ባዩ (መለፋደድ ትወና ነው እንዴ?) ጠረንገሎ፣ ዛሬ በሹመት የዳበረው ከፌዴሬሽን ምክር-ቤት አፈ-ጉባዔና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቦርድ ሰብሳቢ ስር ስር እንደ ሳሎን ውሻ ይከተል የነበረው ብሔር ብሔረሰብን በፌዴሬሽን ምክር ቤት ሲሰብኩንና (ባላገርን በቴሌቪዥን ከሚወዱ፣ ልጆቻቸውንም በውድ የግል ት/ቤት ከሚያስተምሩ ተጋዳላዮች አንዱ) ሲያገለግሉ የነበሩ የሙዚቃ አዋቂው (ጠዋት አፈ-ጉባዔው ጋር ከሰዓት የዩኒቨርሰቲ የፍልስፍና መምህር ቤት)፣ የአ.አ.ዩ.ን አለ ፈለገ-ሰላም የኪነ-ጥበብ ተቋም አንድ ለአምስት በማደራጀት ምሳሌ የሆነው እፍረተ-ቢስ ካድሬ የቀድሞ ዲን ኤርሚያስ ለገሰ፣ ብዙ ጉድ ያጫወተንና በጥር 2009 ዓ.ም. አዲስ ዘመን ላይ የቀን ጅቦቹን ደግፎ ቃለ-መጠይቅ የሰጠው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪውና የዓመቱ 'በግ' ሰው ሽልማት ድርጅት ኃላፊ እና የመሳሰሉትን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይቅርታና በምሕረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሳያቀራርቡ ለምን የኪነ-ጥበብ ባለሙያውን ይደምሩናል?!ለነጋሪም እንዲቀር ሌላው ቢተርፍሎት አይሻልም ወይ?  “[ጠ/ሚኒስትር] ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ!” ግን ደግሞ ሲበዛ ግብዝ ነዎት!

አስተያየት