በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በማድረግ ላይ ያሉት የድጋፍና የምስጋና ሰልፍ በቅርብ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ አገሪቱን አስደማሚ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እየከተታት ይገኛል፡፡ በርግጥ አገሪቱ ገብታበት ከነበረው ውጥረት ወጥታ አበረታች ለውጥ እያሳየች ባለችበትና ዜጎች ድጋፋቸውን እየገለጹ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከትግራይ የሚሰማው ነገር ከዜማው ጋር የማይገጥም ነው ማለት ይቻላል፡፡ከዜማው ያልገጠመውን ይህን ድምጽ የተለያዩ ወገኖች በራሳቸው መንገድ (በእውቀትም ያለእውቀትም) መላ ሲመቱበት ይደመጣል፡፡ እንዲያውም አንዳንዶች ሲከራከሩ ‘የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ልዩ ጥቅም ሳያገኝና ወደፊት ታሪክ ይፋ የሚያወጣቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እየደረሱበት ተቃውሞውን በነጻነት የማይገልጸው ለምንድነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ:: ጥያቄውን ላይ ላዩን ለተመለከተው ታዛቢ በርግጥም የትግራይ ሕዝብ ዝምታና የአንዳንድ ግለሰቦች ከዜማው የማይገጥም ንግግር እንቆቅልሽ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ጥያቄ እኔ በገባኝ መጠን ጥቂት ምክንያቶችን ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡ - እንደ እኔ ዓይነቱ በፍርሃት ተሸብቧል፤ “በተሰበሰባችሁበት ቦታ ሁሉ እኔ በመካከላችሁ አለሁ!”
ሕወሃት ከትጥቅ ትግሉ ጋር ተያይዞ ገጠርና ከተማ ውስጥ የዘረጋው የስለላ መረብ ጠንካራ ነው፡፡ በተሰበሰብንበት ቦታ ሁሉ የመረጃው መስሪያ ቤት ከኛው ጋር አለ፡፡ ጆሮውን አሹሎ ያዳምጣል፣ ጣቱን አገጣጥሞ ይመዘግባል፣ አንደበቱን አስልቶ የስለላ ሪፖርት ያቀርባል፣ ልቡን አደንድኖ ዘብጥያ ያወርዳል፣ ይገርፋል፣ እንደ አስፈላጊነቱ ይገድላል፡፡ በዚህም የተነሳ ከሕወሓት የተለየ ሀሳብ ወይም አቋም የሚያንጸባርቅና የሚይዝ ሰው ከእስርና ከግርፋት ቢተርፍ እንኳን ፓርቲው ታች ድረስ የተዘረጋ እንደመሆኑ ከባድ የሆነ ከማህበራዊ ሕይወት የመገለል እጣ ፈንታ እንዲገጥመው ያደርጋል፡፡ የትግራይ ተወላጅ (በተለይ የገጠሩ ሕዝብ) ይህ በተደጋጋሚ በተግባር ስለገጠመውና አሁንም ስለሚገጥመው ይህንን ዋጋ ለመክፈል እንደ እኔ አይነቱ ፈሪ ዝግጁ አይደለም፡፡ - ከቆይታ ብዛት ሕዝቡ ከፓርቲው ጋር የፈጠረው ትስስር፤ “ከማያውቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን”
ላለፉት አርባ በላይ ዓመታት አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ ከሃርነት ትግሉ ጋር ተያይዞ ከፓርቲው ጋር የፈጠረው ሥነ-ልቦናዊ ትስስር (ልብ በሉ ኢኮኖሚያዊ ትስስር አላልኩም) ፓርቲው ምንም ባያደርግለት እንኳን፤ ልጆቹንም ቢያስገብረው እንኳን ፓርቲውን እንዲሁ ሜዳ ላይ እንዲጥለው መንፈሱ አይፈቅድለትም፡፡ ይህ ሕወሃት ለሁለት በተሰነጠቀችበት ጊዜ እንኳን በፓርቲው አመራር ደረጃ አብዛኛውን የሚወክለው የነተወልደ እና ስዬ አብርሃ ቡድን ተገንጥሎ ወጥቶ እንኳን ነገሩ ሆድ ሆዱን እየበላው ፓርቲው እንዲቀጥል ሥነ-ልቦናዊ ምርጫው ነበር፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት በክልሉ የተዘረጋው ጠንካራ ተቋም ፓርቲው በመሆኑ የትግራይ ሕዝብ ተላምዶታል፡፡ ይህን ሁኔታ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ ሎሎች ቦታዎች አናየውም። ለምሳሌ ከተሞችን ብንጠቅስ ባህርዳር ላይ የለም፣ ጎንደርም ከዚህ አይነት የተቋም-ሕብረተሰብ ቁርኝት በጣም የራቀ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ የተለየች ናት፡፡ አዲስ አበባ ማለት ደግሞ ሕዝቡ ይቅርና የክልልና የፓርቲ አመራሮች ደህና ሆቴል አረፍ ብለው የገዛ አለቆቻቸውንና ድርጅታቸውን የሚያሙበት ገነት የሆነች ሥፍራ ነች፡፡ አዱ-ገነት በሚል ቅጽል ስም የምትታወቀው ይህች ከተማ ለሁሉም “ታማኝ” ካድሬዎች ጭምር የሀሜትና የተቃውሞ ፋታ ስለምትሰጥ ይመስለኛል፡፡ወደ ተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ትግራይ ላይ ይህ የለም። ለነፃነቴ ታግሎልኛል የምትለው ፓርቲ ይቅርና አንድ ታጋች ከአጋቹ ጋር ለረጅም ጊዜ ከመቆየ የተነሳ የሚፈጥረው የመንፈስ ትስስር ከአጋቹ ነፃ ወጥቶ ለመለየት እንኳ ሊከብደው ይችላል (ከ እርሱ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ሕይወት መኖር እንደሚቻል ረስቷልና።) ይህንን በሽታ ፈረንጆች ስቶክሆልም ሲንድረም በማለት ይጠሩታል፡፡ አንዳንዴ ከማያቁት መልአክ የሚያውቁት ሰይጣን ይሻል ይሆናል ብሎ አምኖ የተቀመጠ ይመስላል (Better the devil you know than the angel you don’t know)፡፡
- የፓርቲው ጠበቃዎች የመጨረሻ ምሽግ (Last-ditch)፤ ሲሾሙ “ሥርዓቱ ገነት ነው! ሲሻሩ ገሀነም!”
አብዛኛዎቹ በኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና በአጋሮቹ አመራር ላይ ሕዝቡ ላይ ተዘፍዝፈው የኖሩ የሥርዓቱ ጥቅመኞች ጥቅማቸው ሲነካ ወይም ጥቅማችን ይነካብናል ብለው ሲገምቱ የመጨረሻ ምሽጋቸው የሚያደርጉት አንድም ቀን ዞር ብለው ያላዩትን ምስኪን ሕዝብ ነው፡፡ ይህን የፖለቲከኞች የታወቀ ባህሪ የሕወሃት ኃጥያት ብቻ የሚያደርጉ ካሉ የትግራይ ሕዝብንና ሕወሃትን በተለየ ፍርደ ገምድል ዓይን የሚያዩ ናቸው ብዬ እገነዘባለሁ፡፡ ሁሉም ፓርቲዎችና ሙሰኛ ባለሀብቶች ሲያደርጉት የኖሩትና አሁንም በማድረግ ላይ እንደሆኑ ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው ዜጋ እንዲገነዘብልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በሲዳማ ፖለቲከኞች የሚመራው የደህዴን አመራር አሁን በቅርቡ እንኳን ከየዞኑና ከየወረዳው የሚመጣው ፍትሀዊ ጥያቄ እየበረታበት ሲመጣ ከደቡብ ክልል ራሳችንን ማግለሉ ሥራ ይቀንስልናል በሚል የሰነፍ ምርጫ ጫምባላላን እንደጭምብል ተጠቅሞ አድርጎታል፣ በአቶ አባዱላ ገመዳ ሲዘወር የከረመው የመሬት ከበርቴው የኦህዴድ አመራር በዚህ ታክቲክ ግማሹን የቄሮ ንቅናቄ ከማስተር ፕላኑ ጋር አቆራኝቶ ራሱን ለማዳን መሀል ካዛንቺስ በገነባው ሆቴል ጋለል ብሎ አድርጎታል፣ ዛሬ በሌላ ቁመና የመጣው ብአዴንም የቅማነትና የወልቃይት ጉዳይ ውሃ ውሃ ሲያሰኘው ከዚህ ታክቲክ የጸዳ አልነበረም፡፡እኔ እንደማስታውሰው በ97 ዓ.ም. ምርጫ ወቅት ሕወሃቶች በመቀሌ ከተማ ውስጥ መኪና ላይ ሞንታርቦ ሰቅለው ‘የቀትር ጅብ መጣብህ’ እያሉ ቅንጅትን ያጥላሉ እንደነበር ልብ ይሏል፡፡ አሁንም የትግራይ ህዝብ በጠላት የመከበብ ስሜት (Siege-mentality) እንዲሰማውና ህልውናውን ከፓርቲው ህልውና ጋር እንዲያይዝ ለማድረግ ከውጭ የሚመጣውን ድምፅ ዘግተው አንድ አይነት ድምፅ ብቻ እንዲደርሰው እየተደረገ ነው ያለው፡፡ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ በሌሎች ክልሎች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ሰልፈኞች ይዘዋቸው የወጡትን አንዳንድ መፈክሮች፣ ባንዴራዎችና በትግራይ ተወላጆች ላይ የደረሱ ጥቃቶች እንደ ግብኣት ይጠቀሙባቸዋል። የክልሉ ሚዲያዎች የለውጡን በጎ ገፅታ ለማሳየት እስከ አሁን ፈቃደኝነታቸውን አላሳዩም፡፡በአሁኑ ወቅት ጡረታ የወጡት፣ በፈቃዳቸው የለቀቁትና የተቀነሱት ፖለቲከኞች መቀሌ ከትመው የዶክተር ዐቢይ ቡድን ከትግራይ ህዝብ ጋር ጥላቻ እንዳለው ለማስመሰል ባገኙት አጋጣሚ ከመናገር አልቦዘኑም (ዶ/ር ዐቢይም ይህንን ስለተረዳ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከትግራይ ህዝብ የወጡና በህዝቡ የሚነግዱ ጥቂቶች እንጂ የትግራይ ህዝብ ልዩ ጥቅም እንዳላገኘ ከመግለፅ አልቦዘነም)፡፡ህዝቡን እንወክላለን የሚሉ የክልሉ ተወላጆች የትግራይ-ህዝብና-ህወሓት-አንድ ናቸው አይነቱ ትርክታቸው በየክልሉ የተበተነውን ለፍቶ አዳሪ ትግራዋይ አላስፈላጊ ዋጋ እንዳያስከፍለው እሰጋለሁ፡፡ በትግርኛ አንድ አባባል አለ “መልሓስ ኣብ ፅኑዕ ሰፊራ፤ ንርእሲ ተስብራ” ይባላል…ምላስ ለራሷ ፅኑ ቦታ (አፍ ውስጥ) ተቀምጣ እየለፈለፈች አናትን/ጭንቅላትን ታስመታለች ለማለት አካባቢ ነው፡፡በቅርቡ የINSA ዳይሬክተር የነበሩት ጄነራል የተናገሩትን ነገር ፌስቡክ ላይ አንብቤዋለሁ፡፡የሜቴኩ ጄነራል ለአንድ በትግርኛ ለሚታተም መጽሔት ከሰጡት ቃለ መጠይቅ አንዳንድ ግራ የሚያጋባ ንግግራቸውን ቀንጨብ አድርጌ ላስነብባችሁ…ልማታዊ ዴሞክራሲ ኢ-ሃይማኖታዊ (secular) መሆን አለበት፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚከተሉት ስርዓት ግን ኢ-ሃይማኖታዊ አይደለም፡፡ Evangelicalism የፖለቲካ ስርዓት ነው የሚከተሉት... ስለዚህ ልማታዊ መሆንአይችሉም፡፡ ኢቫንጀሊካሊዝም ኦርቶዶክስን እንደ ጠላት፣ እስልምናን ደግሞ እንደ አሸባሪ ነው የሚቆጥረው፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያዊነት እስከ አሁን ድረስ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚገኘው … ከአዲስ አበባ ውጭ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተመናመነ ነው ብለው ነበር... እንደዚህ ብለው የሚናገሩት እንደ ድሮው በአንድ ቋንቋና ባህልሊጨፈልቁን ስለሚፈልጉ ነው፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከሆንንማ ከስረናል፡፡
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በየክልሉ የሚዞሩት ህዝቡን ለመከፋፈል ነው... ልማታዊ (አብዮታዊ) ዴሞክራሲ እየተሸረሸረ ነው፡፡
በዚሁ በተመሳሳይ መጽሔት የቀድሞው የአየር ኃይል ጄነራል አበበ ተክለሃይማኖት አብዮታዊ ዴሞክራሲ እየተሸረሸረ ነው ብለው ያስባሉ ተብለው ሲጠየቁ የሰጡት መልስ ከላይ ለተጠቀሰው ለጄነራል ተክለብርሃን ንግግር መልስ ሊሆን የሚችል ይመስለኛል፡፡አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተሸርሽሯል ብዬ አላስብም፡፡ እንዲያውም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰብአዊ ገጽ (human face) አላብሰውታል ብዬ ነው የማስበው፡፡
ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያዊነት በይበልጥ አዲስ አበባ ውስጥ ነው የሚንፀባረቀው ያሉት ነገር እንደኔ አስተሳሰብ እውነትነት አለው፡፡ ከተማዋ እስክትጨናነቅ ድረስ ከሁሉም የአገሪቱ ክፍል ሰዉ ሁሉ ወደ አዲስ አበባ የሚተመው ለምን ሆነና? በተነፃፃሪ መልኩ ሰው የብሔር ማንነቱ ሳይጠየቅ ኢትዮጵያዊ ስለሆነ ብቻ ስራ የሚቀጠርባት፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቀበሌ መታወቂያ አውጥቶ የሚመርጥባትና የሚመረጥባት፣ እስከ አሁን ድረስ ከተማችንን ለቃችሁ ውጡልን ያልተባለባት ከተማ ብትኖር አዱገነት ትመስለኛለች፡፡ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የአዲስ አበባን ተሞክሮ ወስደው ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት የማይሳቀቁበት፣ ዜጎች ስለሆኑ ብቻ ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔታ ቢያመቻቹ ችግሩ ታዲያ ምኑ ላይ ነው?ለዛሬ ግንዛቤ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ነገሮችን ጠቅሼ ጽሑፌን ልቋጭ፥ - አብዛኛው ህዝብ (silent majority) ሃሳቡን የሚገልፅበት ነፃ መድረክ እንዳላገኘና ክልሉን እንወክላለን ብለው ሚድያ/ሶሻል ሚድያውን የተቆጣጠሩት (vocal የሆኑት) የትግራይ ተወላጆች የትግራይን ህዝብ የማይወክሉ መሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በህዝቡ ስም ነግደው የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡት ግለሰቦች ህዝቡን እስከ አሁን ካስከፈሉት ተጨማሪ አላስፈላጊ መስዋትነት እንዳያስከፍሉት ሁለት ጊዜ አስበው ቢናገሩ የሚሻል ይመስለኛል፡፡
- አንዳንድ የሌሎች ክልል ነዋሪዎችም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በትግራዋይ ተወላጆች ላይ ጭፍን ጥላቻ ከማሳየት፣ ገፋ ሲልም ብሔር ተኮር ጥቃት ከማድረስ ቢቆጠቡ የሚሻል ይመስለኛል። እንደዚህ ሲያደርጉ ከላይ ለተጠቀሱት ውክልና አለን ባዮች መሣሪያ እያቀበሉ መሆናቸው ሊረዱት ይገባል፡፡
- የትግራይ ህዝብም ከስልጣናቸው ጋር ሞት እስኪለያቸው ድረስ ከተጣበቁት ጋር ተጣብቆ አላስፈላጊ መስዋእት የሚከፍልበት ሁኔታ ማብቃት አለበት እላለሁ፡፡ ክልሉ ውስጥ ወጣቱን የማብቃት ስራ እንኳ በበቂ ሁኔታ እንዳልተሰራ የሕወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ/ስራ አስፈፃሚ አባላት እድሜ ከሌሎች እህት ፓርቲዎች አባላት ጋር በማወዳደር ብቻ ማወቅ ይቻላል፡፡ ከለውጡ በኋላ ሌሎች ክልሎች አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲያቋቋሙና በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ሲፈቅዱ ትግራይ ክልል ውስጥ ግን አማራጭ በማሳጣት የአንድን ፓርቲ የበላይነት ለማስቀጠል እየተሞከረ ይገኛል፡፡ ህዝቡ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት በነፃነት ይወክሉኛል የሚላቸውን አባላት ለመምረጥ፣ አማራጭ ፓርቲዎች ለማደራጀት ይችል ዘንድ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ላይ በጊዜ ጫና ቢያሳድር አላስፈላጊ መስዋት ከመክፈል የሚታደገው ይመስለኛል፡፡