የኢህአዴግ ሰራዊት በትጥቅ ትግል ስልጣን ከያዘበት ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በዋነኛነት በሚከተለው የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ምክንያት በርካታ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ መፈናቅሎች፣ አሰቃቂ ግድያዎች እንዲሁም የንብረቶች መውደም በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተደጋጋሚ ተከስተዋል።ተከታዩ ጽሑፍ በሃገራችን ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ የተከሰቱትን የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች እና በአጠቃላይ ሃገሪቱ ውስጥ ከእነዚህ አደጋዎች ጋር እየተከሰተ ያለውን ቀውስ በአጭሩ ለማስቃኘት ይሞክራል፤ በአጭር ግዜ ውስጥ ድንገት በዚህ መጠንና ስፋት ሊስፋፋበት የቻለበት ምክንያት ነው ብሎ የሚያስበውን ያስቀምጣል፤ በተጨማሪም ሌሎች ተዛማጅ አንደምታዎችን በስሱ ይዳስሳል።
የእርስ በእርስ ግጭቶችና መፈናቅሎች የታዩባቸው አካባቢዎች እና የማህበረሰብ አባላት ማክሰኞ ሰኔ 5፣ 2010 ዓ.ም. በሲዳማ ዞን ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ጥቂት የሲዳማ ብሔር አባላት የወላይታ ነዋሪዎች ላይ ባደረሱት ጥቃት ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ሞተዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል። ነዋሪዎች ለአሜሪካ ድምጽ (ቪኦኤ) የአማርኛው ክፍል እንደገለጹት ከጎረቤቶች እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ውጪ አንድም የክልሉ መንግስት አካል አልደረሰላቸውም፤ ይባስ ብሎም በስተመጨረሻ ፌደራል ፖሊስ መጥቶ አካባቢውን እስኪያረጋጋ ድረስ የክልሉ ፖሊስ ቆሞ ሲመለከት እንደነበር ገልጸዋል። በተመሳሳይ በወልቂጤ ከተማ በጉራጌና በቀቤና ብሄረሰብ አባላት መካከል በተከሰተው ግጭት ሁለት ሰዎች ሞተዋል፤ የብሪታኒያ ዜና ማሰራጫ ማዕከል(ቢቢሲ) የአማርኛው ክፍል እንደዘገበውም የግጭቱ መነሻ በከተማው እየተካሄደ በነበረው የስፖርት ጨዋታ የተነሳ አምባጓሮ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ለጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተካሄዱ ሰልፎች ግጭት አስተናግደዋል።
ቪኦኤ እንደዘገበው ሰኔ 23 ቀን በከሚሴ ልዩ ዞን (ባቴ) የድጋፍ ሰልፍ ከተካሄደ በኋላ አንዳንድ ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች የትግራውያንን የንግድ ተቋማት አቃጥለዋል።በዚህ ወር ከታዩት ግጭቶች በጣም አስከፊው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ዋና ከተማ አሶሳ ላይ የታየው ነው። ለቀናት በቆየው ግጭት የበርታ ብሄረሰብ አባላት "አበሻ" ብለው የሚጠሩዋቸውን ኢትዮጵያዊያንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል። አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለቪኦኤ በአካባቢው እንደዚህ አይነት ግጭት ተካሂዶ እንደማያውቅ እና አሁን የተከሰተበት ምክንያት ግራ እንዳጋባው ግልጿል፤ በአደጋው ባጠቃላይ ከ10 ሰዎች በላይ መሞታቸውን እና ከ 40 በላይ መቁሰላቸውን ቪኦኤ ገልጿል። ከኦሮምያ እና ከ ቤንሻንጉል ዞንም እንዲሁ ብዙዎች በብሄራቸው ምክንያት ተፈናቅለዋል፣ ንብረት ወድሟል፣ ህይወት ጠፍቷል።
ስለ ጉዳዩ ዘርዘር ያለ ዘገባ በአዲስ ስታንዳርድ ላይ የወጣውን ይህን ዘገባ ከዚህ መስፈንጠሪያ ማግኘት ይቻላል።ይሄ እንዳለ ሆኖ ባለፈው አመት መስከረም ወር 2009 ዓ.ም. በኦሮምያ እና በኢትዮጰያ ሶማሊ ክልሎች የጠረፍ አካባቢ በተነሳ ግጭት 1 ሚልዮን የሚሆኑ ዜጎች (በአብዛኝው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች) መፈናቀላቸው ይታወሳል። ልዩ ፖሊስ የሚባለው ተጠያቂነቱ ለኢትዮጰያ ሶማሊ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አብዲ ኢሌ የሆነው የፖሊስ ሃይል በአካባቢው በጣም አሳዛኝ እና ዘግናኝ ወንጀሎችን እና ግድያዎች ያለምንም ማን አለብኝነት እየፈፀመ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ከሰብአዊ ድርጅቶች ክስ እና ዘገባ ይቀርብበታል። የፖሊስ ሃይሉ በቅርቡ እንኳን በምስራቅ ሃረርጌ ነዋሪዎች ላይ አሰቃቂ ወንጀሎችን እየፈጸመ እንደሚገኝ ማህበራዊ ሚድያዎች ላይ በሰፊው እየወጣ ይገኛል።ምናልባትም የሚገባውን ያህል ትኩረት ያላገኘው እና በአሁን ሰአት ወደ አንድ ሚልዮን ለሚጠጉ ሰዎች መፈናቅል ምክንያት የሆነው ግጭት በጌድኦ እና በጉጂ ዞኖች ጠረፍ አካባቢ የተከሰተው ግጭት ነው። በግጭቱ ከ 793 ሺህ በላይ የጌድዮ ተወላጆች ከቀያቸው ብሄርን መሰረት ባደረገ ጥቃት ሲፈናቀሉ ቢያንስ 185 ሺህ የጉጂ ኦሮሞዎች በተመሳሳይ ምክንያት ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ይህን አሳሳቢ ጉዳይ በማስመልከት መንግስት እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ተፈናቃዮችን ለመርዳት 117.7 ሚልዮን ብር በቀጣዩ 6 ወራት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች እና ተዛማጅ አንደምታዎች ግጭቶቹ በታየባቸው አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ተፈናቃዮች ለጥቃቱ የአካባቢውን የጸጥታ ሃይሎች ተጠያቂ ያደርጋሉ፤ ብዙዎቹም ነዋሪው ሕዝብ በአብዛኛው እንደሌለበት ብቻም ሳይሆን ተጠቂዎቹን በተለያየ መንገድ ሲረዳ እንደነበር ገልጸዋል። ቪኦኤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝን ግጭት በተመለከተ በሰራው ዘገባ ለችግሩ የክልሉ ባለስልጣናት ተጠያቂ እንደሆኑና ሁኔታው ‘የማይታዩ እጆች’ አሉበት በማለት ነዋሪዎችን አነጋግሮ ገልጿል። መፈናቀልና ብጥብጡን ተከትሎ በተለይም በቤንሻንጉል ከክልሉ ፕሬዝዳንት ጀምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ከስልጣናቸው ተነስተዋል፤ በተመሳሳይም በኦሮምያ አንዳንድ ባላስልጣናት ከስልጣናቸው ተባረዋል። ነገር ግን ከችግሩ ስፋትና ክብደት አንጻር መንግስት ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቀዋል። በግጭቱ ተሳታፊ የነበሩ የጸጥታ አባላት እና ሌሎች በየወረዳው የሚገኙ የክልል ባለስልጣናት ላይ ማጣራት ተደርጎ ወንጀለኞች ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል።
የጠቅላይ ሚንስትር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት በተለይ የሕወሃት እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክሪያሳዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ባለስልጣናትን እንዳላስደሰተ ከምርጫው ሂደት እና ቀጥሎ ባሉት ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። በሃገሪቱ ብሔርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ላለፉት 27 ዓመታት በተለያየ ግዜያት የታዩ ቢሆንም በዚህ ደረጃና መጠን እንዲህ በአጭር ግዜ ሲታይ ግን የመጀመርያው ነው፤ ይህም ጉዳዩ በእርግጥም ድብቅ እጅ እንዳለበት ያሳያል። በአሁኑ ሰዓት ሃገሪቱን ሁለት መንግስት የሚመራት በሚመስል ሁኔታ የጠቅላይ ሚንስትሩ የለውጥ አካሄድን የሚቃወሙ በተለይም የሕወሃት አንዳንድ ባለስልጣናት በግልጽ ጠቅላይ ሚንስትሩን በመቃወም ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። ለውጡንም ለማደናቀፍ ሕዝብን ከሕዝብ ማጣላትን እንደ አንድ ስልት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ እሙን ነው ። የችግሩ አሳሳቢነት በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም፤ ሃገሪቱን ወደ አስከፊ የርስ በርስ ግጭት ሊመራት ይችላል። በመሆኑም አሁን ባለንበት አሳሳቢ ሁኔታ ጠቅላይ ሚንስትሩን በሚቻለው ሁሉ በመደገፍ እና ሃገሪቱ ውስጥ ያንዣበበውን አደጋ ከመቀልበስ ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ ያለ አይመስልም።ላለፉት አስርት ዓመታት ኢትዮጵያን በእጅጉ እየተፈታተናት እና ትልቅ የራስ ምታት የሆነባት ብሔረተኝነት ኢትዮጵያዊነት ስሜትን በእጅጉ አውርዶ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮያውያንን ራሳቸውን እና ሌሎችን በብሔር መነጽር ብቻ እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል።
ሃገሪቷ ስትከተለው የቆየችው የከፋፍለህ ግዛ ስልት እና የብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። በአሁን ሰዓት ሃገራዊ መፈናቀሎችን ተከትሎ አብዛኖቹ የማህበራዊ ሚድያው አሽከርካሪዎች መፈናቅሎቹን የሚገልጹበት መንገድ ላስተዋለ ሰብአዊነት እውን አለን ብሎ መጠየቁ አይቀርም። እንዲሁም እንደ ጌዲኦ ያሉ የሚወክላቸው የተማረ ክፍል ወይም አራማጅ የሌላቸው ማኅበረሰቦች ከ800 ሺህ ሰው በላይ ቢፈናቀለባቸውም በበቂ ሁኔታ ድምጽ የሚያሰማላቸው አላገኙም። በተለይ በጌዲኦ እና በጉጂ ማህበረቦች የደረሰው እና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህዝብ መፈናቀል ምክንያት ስለሆነው ግጭት በመንግስትም ሆነ በግል ሚድያ ይሄ ነው የሚባል ሽፋን አልተሰጠውም።
በዚህ ሳምንት አዲሷ የደኢህዴን ሊቀመንበር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በክልሉ ከ600 ሺህ ሰው በላይ ተፈናቃዮች የሚገኙበትን መጠለያዎች ጎብኝተው መንግስት ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።በሃገሪቷ በአሁን ሰዓት ከሁለት ሚልዮን በላይ ሰዎች የሃገራዊ መፈናቀል (internal displacement) ሰለባ ሆነዋል፤ ይህም እንደ ቦትስዋና ላሉ ሃገራት የጠቅላላ የሃገሪቱ ህዝብ ማለት ነው። በዚህ ጽሑፍ መግቢያ የተጠቀሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዘገባ የጠቀሰው የገንዘብ ድጋፍ ለጊዜአዊ እና መሰረታዊ ፍጆታዎች ብቻ የሚውል ነው፤ ለተፈናቃዮቹ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት እጅግ ከፍ ያለ የገንዘብ፣ የቁሳቁስና አስተዳደራዊ ቅንጅትን ይጠይቃል።
ዜጎች ከአንድ ክልል ወደ ሌላኛው ሲፈናቀሉ ከሚደርስባቸው የሞራል፣የስነልቦና፣ እና የንብረት ጉዳት ባሻገር በመጠለያዎች ውስጥ ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችም ይጋለጣሉ፤ በተለይ ሰብዓዊ ቀውሱ እንደ አሁኑ በክረምት ሰሞን ሲያጋጥም ይብሳል። ተማሪዎችም በጊዜያዊነት ተጠልለውበት የሚገኙበት ቦታ የስራ ቋንቋ በፊት ከተማሩበት ስለሚለይ በቀላሉ ትምህርት ቤት መግባት ስለማይችሉ ውድ ጊዜያቸውን እንዲሁ ያባክናሉ።ብዙዎች ብሔረተኛ የማኅበራዊው ሚድያ ሰራዊቶች (ከልባቸው ለሕዝብ ግድ ኖሯቸው የሚሰሩ የመኖራቸውን ያህል) ለአደጋዎቹ መፍትሄ ፍለጋ ሳይሆን ችግሩን ወክለነዋል በሚሉት ምስኪን ተፈናቃይ ስም የደጋፊዎቻቸውን ቁጥር ለማብዛት ሲጠቀሙበት ይታያሉ። በውጭ ሃገራት ያሉ ጥቂት እንደ ጎፈንድሚ (gofundme) ያሉ የገንዘብ ማሰባሰብያ ገጸች መልዕክቶች በቀጥታ የተፈናቀሉትን ወይም የተለያየ ችግር ሰለባ የሆኑትን ብሔር አባላት ብቻ አላማ አርገው የተነሱ ናቸው። የብሔር ፖለቲካን እንደሚጸየፉ በተደጋጋሚ የሚገልጹት ኢትዮጵያዊ ብሔረተኞች በበኩላቸው የተቀናጀ የእርዳታ መስመር ዘርግተው መፍትሄ ለመፈለግ ሲንቀሳቀሱም ሆነ ይሄ ነው የሚባል ስራ ሲሰሩ አይታይም። የአለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን የሚባል ድርጅት ሃገራዊ በሆነ ሁኔታ የተቻለውን ለማድረግ ቢሞክርም ከችግሩ ስፋት አንጻር ተጽእኖው ያን ያህል የሚባል አይደለም።
ባጠቃላይ ብሄርተኝነት ልክ እንደ ሌሎች ጉዳዮች በተለይ በውጭ ሃገራት ያሉትን የሰብአዊው እርዳታ ሙከራዎች ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህ ደግሞ አንደኛውን ቡድን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን በየትኛውም አይነት ብሄረተኝነት (ሃገራዊም ሆነ ብሄር ተኮር) ላለው ይሰራል።ይህን የመሰሉ ሰብዓዊ ችግሮች (humanitarian crisis) ሲያጋጥሙ በጋራ መተባበር አንድ ትልቅ ቋጥኝን የመውጣት ያህል እትዮጵያውያንን ከብዶናል። የተቀናጀ እና የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ተጎጂ የሚረዳ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጠቀሜታው ከሞራል አንጻር እንኳን ባይታይ ቢያንስ ከፖለቲካዊ ፋይዳው አንጻር የሚያየው ሰው እራሱ ይህን ያህል አይደለም። አሁን ባለው ሁኔታ ችግሮች የሚቀጥሉ ከሆነ እና ሃገሪቷ ውስጥ የእርስ በእርስ ግጭት ቢካሄድ ቀውሱ ቤቱን የማያንኳኳበት ምንም የማኅበረሰብ ክፍል አይኖርም። ቢያንስ እንወክለዋለን የምንለውን ብሔር ወይም ቡድን ደህንነት ከሌላው ሕዝብ ጋር በእጅጉ የተሰናሰለ መሆኑን መረዳት እና ችግሮችን “ከሌሎች” ጋር እንዴት ተባብሮ መስራት እንደሚቻል ማሰብ ያስፈልጋል።
ሌላው ቢቀር በጉርብትናም ለመኖር ሰላም እንደሚያስፈልግ ለኢትዮጵያውያን ነጋሪ አያስፈልገንም።በአሁን ሰዓት በአሳሳቢ ሁኔታ እየተስፋፋ ያለውን ሃገራዊ ግጭትና መፈናቅል ለማስቆም ዋናው እና ትልቁ ድርሻ የመንግስት እንደሆነ ባያጠያይቅም ዜጎችም የሚጠበቅብንን ሃላፊነት በቻልነው አቅም እየተወጣን መሆናችንን መጠየቅ ይገባል፤ ችግሮችን መፍታት ባንችል እንኳን እንዳይባባሱ ምን እያደረግን ነው? ይህ ጽሑፍ ሃገራችን ብዙዎች ለነጻነት ህይወታቸውን ካጡበት ረጅም የመንግስት ተቃውሞ በኋላ የተገኘውን መልካም እና ልዩ አጋጣሚ በመጠቀም የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር አንባቢው ይሆናል ያለውን መፍትሄ እንዲጠቁምና በማኀበራዊ መካነ-ድሮች እና ጎበና መንገድን ጨምሮ ሌሎች ሚዲያዎች ሃገራዊ ውይይቱን እንዲቀጥል በመጋበዝ ይሰናበታል።