ነሐሴ 26 ፣ 2012

"መጪው ክልላዊ ምርጫ የህወሀት ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው" ፕሮፌሰር መረሳ ፀሀዬ

ቃለመጠይቆችወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በቀጣዩ ሳምንት በትግራይ ክልላዊ መንግስት የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በክልሉ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ረብሻ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በኪውቤክ ካናዳ…

"መጪው ክልላዊ ምርጫ የህወሀት ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው" ፕሮፌሰር መረሳ ፀሀዬ
በቀጣዩ ሳምንት በትግራይ ክልላዊ መንግስት የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በክልሉ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ረብሻ ሊቀሰቀስ እንደሚችል በኪውቤክ ካናዳ የሚገኘው ጋርዳ ወርልድ (GardaWorld) የተሰኘው ድርጅት በመካነ ድር  በዛሬው እለት ባወጣው መረጃ የገለፀ ሲሆን ድርጅቱ እንደገለፀው ከሆነ በፊታችን ረቡዕ ጷግሜ 4፣ ቀን 2012 ዓ.ም ለመካሄድ እቅድ የተያዘለት የትግራይ መንግስት ክልላዊ ምርጫን ይከሰታል ብሎ የሚያስበው ግጭት ክልላዊ መንግስቱ ከፌደራል መንግስት እንዲሁም ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር ካለው ቅራኔ የተነሳ እንደሆነ ድርጅቱ መላምቱን አስቀምጧል። በተጨማሪም በክልሉ የተለያዩ ክፍሎች በተለይም በምርጫ ማዕከላት አካባቢ ሰላማዊና ሰላማዊ ያልሆኑ የተቃውሞ ሰልፎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጋርዳ ወርልድ ገልጿል። ድርጅቱ አክሎም በትግራይ ክልል የሚገኙ ግለሰቦች ምርጫው ከመደረጉ በፊት፣ በሚደረግበት ወቅትና ከተካሄደ በኋላ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያስጠነቀቀ ሲሆን በተጨማሪም በመንግስት አካላት የሚሰጡ መመሪያዎችን በመከተል ምርጫውን ተከትሎ ሊከሰት ከሚችለው ረብሻ ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ የተነሳ ሊያካሄዱ ታቅደው የነበሩትን ብሄራዊና ክልላዊ ምርጫዎች  ማስተላለፉን ተከትሎ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በሰኔ ወር ክልላዊ ምርጫን እንደሚያካሂድ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ይህ ውሳኔ በክልላዊ መንግስቱና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭትን ሊቀሰቅስ እንደሚችል ክራይሲስ ግሩፕን ጨምሮ የተለያዩ አለምአቀፍ የዜና ትንተና አውታሮች መዘገባቸውም የማይዘነጋ ነው። አዲስ ዘይቤ ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ምርጫ ኮሚሽን ማዕካላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር መረሳ ፀሐዬ ስለምርጫው ህጋዊነት “ይህ ምርጫ ክልላዊ ምርጫ ነው። በህገመንግስቱ የተቀመጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ከመጠቀም ውጪ በትግራይ ክልል ውስጥ የተጣሰ ወይም በምርጫው ወቅት የሚጣስ ህግ የለም።” በማለት እምነታቸውን ያስረዱ ሲሆን ክልላዊ መንግስቱ ምርጫውን ለማድረግ በወሰነበት ወቅት ለፌደራል መንግስትም ሆነ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቆ እንደነበረ አስታውሰዋል። አክለውም ክልሉ ተገቢ የሚለውን ምላሽ ባለማግኘቱ የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማዋቀር ምርጫውን ለማካሄድ ተገዷል ያሉ ሲሆን በዚህም ምክንያት ምንም የተጣሰ ህግ አለ ብለው እንደማያምኑ ፕሮፌሰር ሰመረ ገልፅዋል። አክለውም ጋርዳ ወርልድ በትግራይ ክልላዊ መንግስት የሚደረገው ምርጫን ተከትሎ ሊፈጠር ይችላል ስላለው ረብሻና ግጭት ዙርያ “ምርጫው እንደሚካሄድ ከተወሰነበት ወቅት ጀምሮ ሁሉም ነገር እየተካሄደ የሚገኘው ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነው። ከምርጫ ዘመቻዎች እስከ ምዝገባ ድረስ ሁሉም ነገር በሰላማዊ ሁኔታ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።” በማለት በምርጫው ቀንም ሆነ ከምርጫው በፊትና በኋላ ባሉት ቀናት ላይ ምንም አይነት ችግር ይፈጠራል ብለው እንደማያምኑ ፕሮፌሰሩ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።ፕሮፌሰር መረሳ በተጨማሪም ምርጫውን በማስመልከት ሊፈጠር የሚችል ምንም አይነት ረብሻም ሆነ ግጭት ቢኖር ከክልሉ ውጪ በሚገኙ ሀይሎች የሚቀሰቀስ እንደሆነ ገልፀዋል።  “እንደነገርኩህ ከህዝቡ ፍላጎትም ሆነ የምርጫውን ዝግጅት ብትመለከት ምንም አይነት ረብሻ ከእሮቡ ምርጫ በኋላ ይከሰታል ለማለት የሚያስችል ምክንያት ማግኘት አይቻልም።”  ፕሮፌሰር መረሳ አክለው ምናልባት የፌደራል መንግስት፣ የኤርትራ መንግስት እንዲሁም የአማራ ክልላዊ መንግስትን ጨምሮ በተለያዩ  ሀይሎች የሚቀሰቀስ ግጭት ሊኖር እንድሚችል ግምታቸውን ካስቀመጡ በኃላ ይህንንም ህጋዊ በሆነ መልኩ ለመቆጣጠር ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡በምርጫው ዝግጅት ዙርያ ለተነሱላቸው ጥያቄ ምላሽን የሰጡት ፕሮፌሰሩ “ምርጫውን ለማካሄድ የህዝብ ምዝገባን ባካሄድንበት ወቅት ለመመዝገብ ያሰብነው 2.6 ሚልዮን እድሜያቸው ለመምረጥ የክልሉ ነዋሪዎችን ነበረ። በአሁኑ ወቅት በቀጣዩ እሮብ ለሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ ከ2.7 ሚልዮን በላይ ሰዎችን መመዝገብ ችለናል። ይህ የ102.78 መቶ ስኬትን የሚያሳይ ነው።” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በመጨረሻም ምርጫው አገሪቱ ዲሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን  ለማስፈን በምታደርገው ጉዞ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው የገለፁት ፕሮፌሰሩ፣ አክለውም እስከአሁን ድረስ በትግራይ ማህበረሰብ ውስጥ ምርጫው ከፍተኛ ተቀባይነት እንዳለው ነው የምንረዳው። ለዚህም የምርጫው ምዝገባ በሁለት ቀናት መጠናቀቁ ትልቅ ማሳያ ነው ብዬ አምናለው። ስለዚህ ምርጫው በአገሪቱና በምስራቅ አፍሪካ ለሚደረገው ዲሞክራሲን የማስፈን ስራ ትልቅ ሚናን ስለሚጫወት ምርጫውን መደገፍ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን መደገፍ ነው። ምርጫው የትግራይ ህዝብን የሚያስተዳድረውን  አካል የመምረጥ ህገ መንግስታዊ መብት ለማረጋገጥ የሚደረግ ምርጫ ነው።” በማለት በመጪው ሳምንት በክልሉ የሚካሄደው ምርጫ የህውሓት እንደሆነ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። ምርጫው ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝና ወረርሺኙ እንዳይስፋፋ አገሪቱ እያደረገች ካለችው ጥረት አንፃር ይኖረዋል ተብሎ ከሚጠበቀው ተፅዕኖ ጋር በተያያዘ ከአዲስ ዘይቤ ለቀረበላቸው ጥያቄም ክልሉ ምርጫውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ከማድረግ እኩል የምርጫውን ስኬታማነት የሚለካበት አንዱ መስፈርት በምርጫው ሂደት ኮሮናን በአግባቡ መከላከል እንደሆነ ፕሮፌሰር መረሳ የገለፁ ሲሆን “የተለያዩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማደራጀት በሁሉም የምርጫ ጣብያዎች የኮሮና መከላከያ መመርያዎችን እንዲያስከብሩ ለማሰማራት ተገቢውን ዝግጅት አድርገናል። በተጨማሪም በተለያዩ ባለሀብቶችና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ የተለያዩ ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የህክምና እቃዎችና የመጀመርያ የህክምና እርዳታ መስጫ እቃዎችን በየምርጫ ጣቢያው አዳርሰናል።” ሲሉ በክልል መንግስቱ ቫይረሱ እንዳይሰራጭ የተወሰዱትን እርምጃዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።ኢትዮጵያ ስድስተኛ ብሄራዊና ክልላዊ ምርጫን ለማካሄድ በያዝነው አመት መጨረሻ አቅዳ የነበረ ቢሆንም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ጋር በተያያዘ ምርጫው እንደማይካሄድ ባሳለፍነው ሰኔ ወር የህገመንግስት ጉዳዪች አጣሪ ጉባኤ የሰጠውን ምክር ተከትሎ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ጨምሮ ከሌሎች ታዳሚዎች በምርጫው ዙሪያና ህገ መንግስቱን ለማስከበር የፌደራል መንግስት ምን ሊወስዳቸው ይገባል ባሏቸው እርምጃዎች ዙርያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ “በትግራይ ክልል ወይ ከአማራ ክልል፣ ወይ ከኤርትራ መንግስት ወይ ከፌደራል መንግስት ግጭት እንዲያነሳ በጣም የሚፈልጉ ሀይሎች አሉ። እንደዚሁ ከምንሸነፍ በጉልበት ተመታን በሚል መጨረሻችን ይደምደም የሚሉ ኃይሎች አሉ። እኔ እንድ ለእርሶ (የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው ዶ/ር አረጋዊን ለማለት ነው) ላረጋግጥ የምፈልገው ከትግራይ ክልል ጋር ውግያ የመክፈት ፍላጎት የለኝም። የትግራይ ክልልምም የጥይት ድምፅ መስማት ይበቃዋል የሚልም እምነት አለኝ። በቂ ጊዜ ወስዷል ብዬ ስለማስብ።” በማለት የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ሀይልን የመጠቀም እቅድ እንደሌለው ጠ/ሚንስትሩ ገልፀዋል።ጠቅላዩ አክለውም በወቅቱ “አሁን መምረጥ ነው። እኛ ብዙ ነን፣ ገንዘብ አለን፣ ፌደራል ነን፣ ፖሊስ አለን፣ ወታደር አለን ብለን ከገባን ያው እንደምታውቁት እነዚህ ማስገደል እንጂ መሞት የማያውቁ ሰዎች አይሞቱም። ውጊያ ደግሞ ሰው አይመርጥም። አርሶአደርን ይገላል፣ ሴትን ይገላል፣ ህፃንም ይገላል።” በማለት በወቅቱ መንግስት በትዕግስት ሁኔታውን ለማለፍ እያደረገ ነው ስላሉት ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት እንቅስቃሴ ለማስረዳት ሞክረዋል።ነገር ግን ምንም እንኳን የፌደራል መንግስት ጉዳዩን በሰላማዊ መንግስት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ጠቅላይ ሚንስትሩ በወቅቱ ቢገልፁም አክለው ግን የትግራይ ክልላዊ መንግስት ከፌደራል አስተዳደሩ ጋር ሊጋጭ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም በውይይቱ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል። “ምርጫ ህግ አለው ስርአትም አለው። እኛ ምርጫ እንዲደረግ የነበረንን አቋም ታውቃላቹ። ኮሮና አስቀረው። አሁን ቢበዛ እንደእኔ እምነት ዘጠኝ ወይ አስር ወር ቢቆይ ነው።” በማለት የፌደራል መንግስት ምርጫውን ለማድረግ የነበረውን ፍላጎት አስታውሰው በክልሉና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭት ሊፈጠር የሚችልበትን ሁኔታ ሲያስረዱ የፌዴሬሽን ምክርቤት እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ በክልልም በፌደራልም አሁን ስልጣን ላይ ያሉ መንግስታት በስልጣናቸው ላይ እንዲቆዩ  መወሰኑን አስታውሰው ህውሓት የምርጫው አሸናፊ ከሆነ እስከሚቅጥለው አመት ድረስ ክልልሉን እንዲመራ የተሰጠውን ውሷኔ ከመድገም ባለፈ አዲስ የሚፈጠር ነገር እንደሌለ ማስረዳታቸው ይታወሳል።ጠቅላዩ አክለውም “ችግር የሚፈጠረው ህውሓት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አድርጎ ስልጣኑን ለአረና[አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ] ከሰጠ ያኔ እንጋጫለን። ምክንያቱም አረና እስከሚቀጥለው አመት ድረስ መንግስት መሆን አይችልም። የትግራይ ክልል መንግስት አረና የሚሆን ከሆነ በምርጫው ተወዳድሮ ያኔ ከፌደራል መንግስት ጋር ፀብ ይፈጠራል… ህውሓት ግን መልሶ ቢመጣ እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ቆይ ብሎታል።” በማለት ምርጫውን ተከትሎ በትግራይ ክልላዊ መንግስትና በፌደራል መንግስት መካከል ግጭት ሊፈጠር ስለሚችልበት ሁኔታ ማስረዳታቸው ይታወሳል። የትግራይ ክልላዊ መንግስት የ2012 ዓ.ም ክልላዊ ምርጫን በፊታችን እሮብ ጷግሜ 4 ቀን 2012 ዓ.ም ለማካሄድ ዝግጅቱን ጨርሶ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።  

አስተያየት