ነሐሴ 25 ፣ 2012

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጀ የመሬት ወረራ እንደተካሄደ ደርሼበታለሁ አለ

ዜናዎች

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ የፖለቲካ ማህበር(ኢዜማ ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በብዙ የከተማው አካባቢዎችና ሰፋፊ…

ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ የተደራጀ የመሬት ወረራ እንደተካሄደ ደርሼበታለሁ አለ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ የፖለቲካ ማህበር(ኢዜማ ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደው የመሬት ወረራ በብዙ የከተማው አካባቢዎችና ሰፋፊ መሬቶችን ዒላማ ያደረገ በተናጠል የሚደረግ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም እንደሆነ በጥናቱ እንዳረጋገጠ ገለፀ።ኢዜማ ይህንን የተናገረው ለሁለት ተከታታይ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ በፖሊስ ከተከለከለ በኋላ ዛሬ በፅሕፈት ቤቱ ባደረገው ገለፃ ነው፡፡በአዲስ አበባ ከተማ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልፅ የሆነ የመሬት ወረራና ሕገ-ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ እንደተካሄደ ማረጋገጡን ፓርቲው የተናገረ ሲሆን ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የጥናት ቡድኑ በዋናነት ጥናት ያደረገው በአዲስ አበባ 5 ክፍለ ከተሞች የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብቻ መሆኑን ጠቅሶ በዚህም መሠረት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 88,100 ካሬ ሜትር፣ በየካ ክፍለ ከተማ 63,000 ካ.ሜ.፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ 15000 ካሬ ሜትር፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ 23,600 ካሬ ሜትር፣ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 23,000 ካሬ ሜትር ቦታዎች በወረራና ከሕግ አግባብ ውጪ እንደተያዙ በወረራ ተይዟል የተባለው ቦታ የሚገኝበትን እያንዳንዱን አካባቢ በዝርዝር በመጥቀስ አመልክቷል፡፡ኢዜማ በማከል የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በተመለከተ በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከታሰበለት ጊዜ በጣም ዘግይቶ ችግሩን መቀነስ አለመቻሉ ሳያንስ ቤቶቹን ለመረከብ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ከ15 ዓመታት በላይ የቆጠቡ የከተማዋ ነዋሪዎች ቤት ሳያገኙ ግንባታቸው ያለቁ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላልተመዘገቡ እና ቁጠባ ላልፈፀሙ ሰዎች ተላልፈው እየተሰጡ መሆኑን በጥናት ደርሼበታለሁም ብሏል። በሥልጣን ላይ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ በመቀየር በግለሰብ ትዕዛዝ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በጥናቱ ተረጋግጧልም ያለው ፓርቲው "የከተማው አስተዳደር እያየና እየሰማ በሕገ ወጥ እና በተደራጀ መልኩ በወረራ የተያዙ ቦታዎች በፍጥነት ካርታ እና ፕላን ተሠርቶላቸው ለ3ተኛ ወገን በሽያጭ ተላልፈዋል በማኅበር እና በግል፣ ለማምረቻና ለንግድ አገልግሎት እንዲውሉም ተደርገዋል" ብሏል፡፡

አስተያየት