ከሰሞኑ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባላት፣ ግለሰቦች፣ የሚዲያና የሙያ ማህበራት በሀገሪቱ የሚገኙ የፓለቲካ ፓርቲዎችን ስም እየጠቀሱ በሽብርተኝነት ሊፈረጁ ይገባል ሲሉ እየተደመጡ ነው።
እነዚህን ጥያቄዎች የሰማችው አዲስ ዘይቤ በሀገሪቱ አንድን ቡድን ወይም የፓለቲካ አደረጃጀት በሽብርተኝነት ለመፈረጅ ምን ምን ቅድመ-ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው የሚለውን ጥያቄ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ባለሙያዎች አነጋግራለች።
አዲሱ ሽብርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ከበፊቱ የጸረ-ሽብር ህግ በተለየ ሁኔታ አንድን ቡድን ሽብርተኛ ብሎ ለመሰየም በርካታ ዝርዝር ነገሮችና ስነ--ስርዓት ያስቀምጣል ይህንንም ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው ኢትዮጵያ በቅርቡ የህግ ማሻሻያ ተደርጎባቸው ወደ ትግበራ ከገቡት ህጎች መካከል አንዱ የሆነው የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያጸደቀችው አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ነው።
ጠበቃና የህግ አማካሪ የሆኑት አቶ አመሀ መኮንን ከዚህ በፊት የነበረው የሽብርተኝነት ፍረጃ በአብዛኛው በህጉ ላይ ተመርኩዞ ሳይሆን የፖለቲካ ፍረጃ ነበር፣ በሂደቱም የደኅንነቱ መስሪያ ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በአዲሱ አዋጅ መሰረት ግን ድርጅቶችን በአሸባሪነት ስለመሰየም ስለሽብርተኝነት በሚመለከተው ክፍል ሶስት ላይ አንቀፅ 18 ስር በግልጽ የሚያስቀምጠው በኢትዮጵያ በሽብር ወንጀል የተሳፈ ድርጅትን በአሸባሪነት የመሰየም ስልጣን የተሰጠው እንደ ቀድሞው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ይላል፡፡ አቶ አመሐ በአዲሱ ህግ “ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከመነሻው ጀምሮ ቡድኑን መርምሮ ለማሳየም በአዋጁ የተቀመጠ ብዙ ሚና አለው" ይህም አዲሱን አዋጅ የተለየ ያደርገዋል ብለው ይከራከራሉ ፡፡
የህጉ አርቃቂ ቡድን አባል በመሆን ያገለገሉት ጠበቃና የህግ ባለሙያ አቶ ደሞዝ አማን በኩላቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል የውሳኔ ሀሳብ ከመቅረቡ በፊት የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቀድሞ ጉዳዮችን በማጣራት ድርጅቱ በህጉ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ማሟላቱን እንዲመረምር ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ህጉ እንድ ደርጅት የሽብር ወንጀል ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፣ የድርጅቱ የስራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካል ወንጀሉን በአሰራርም ሆነ በግልፅ ከተቀበለው ወይም አፈፃፀሙን በግልጽ የመራ እንደሆነ ፣ በአሰራር ወይም በአፈፃፀም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ሲሆን ወይም አብዛኛው የድርጅቱ ሰራተኛ ወንጀሉን በሚያውቁት ሁኔታ የሚንቀሳቀስ እንደሆነና ዐቃቤ ህግ ከነዚህ መካከል አንዱን ስለማሟቱ ካመነ ድርጅቱ በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሀሳብ ማቅረብ ይጠበቅበታል ይላል፡፡
አቶ ደሞዝ አክለውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉዳዩን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ አካሄዱን አስረድተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ብሎ ወደ መሰየም ከመግባቱ በፊት ለሚሰየመው ድርጅት ወይንም ቡድን አግባብነት ያለው ጊዜ ሰጥቶ በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጥሪ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ይህም ድርጅቱ የውሳኔ ሀሳቡን ለመቃወም ለምክር ቤቱ ማስረጃ ማቅረብ እንዲችል በቂ ጊዜም እንዲኖረው ያደርጋል። በመጨረሻም የህዝብ እንደራሴው የሚንስትሮች ምክርቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ እንዲሁም ድርጅቱ ያቀረበውን የተቃውሞ ማስረጃ እና በራሱ አነሳሽነት ያገኛቸውን ማስረጃዎች በመመርመር ውሳኔ እንደሚሰጥ አዋጁ ያብራራል፡፡
በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት አንድን ድርጅት በአሸባሪነት ሲሰይም የሚንስትሮች ምክርቤት ውሳኔውን በመገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ይፋ በማድረግ ስያሜው በኢትዮጵያ ተፈጻሚ እንዲሆን ማድረግ እንደሚችልም በግልጽ ያትታል።