መጋቢት 9 ፣ 2015

በሲዳማና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ለሚነሱ ግጭቶች ተጠያቂው መንግስት ነዉ

City: Hawassaፖለቲካወቅታዊ ጉዳዮች

የሲዳማ ክልል ከኦሮሚያ ከሚያዋስናቸዉ አከባቢዎች ወቅትን እየጠበቁ በተደጋጋሚ ለሚነሱት ግጭቶች ተጠያቂዉ የሁለቱ ክልል አመራሮች ናቸዉ ሲሉ ነዋሪዎች ለአዲስ ዘይቤ ተናገሩ ።

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

በሲዳማና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ለሚነሱ ግጭቶች ተጠያቂው መንግስት ነዉ

የሲዳማ ክልል ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ጉጂ ዞን እና በምዕራብ አርሲ ዞን አዋሳኝ ድንበር ላይ በሚገኙ ስፍራዎች ጊዜን እየጠቁ የሚነሱ ግጭቶች ለበርካቶች ህይወት ማለፍ እና ንብረት ዉድመት ምክያት ሆነው መቀጠላቸው ነዋሪዎችን ስጋት ላይ ጥሏል። 

አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት "ከአምስት ዓመት ወዲህ በሚነሱ ግጭቶች በሚመለከታቸው አካላት እርቅና ዉይይት ቢካሄድም ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ አልቻለም።"

 "በማህበረሰቡ ዘንድ እየተነሱ ለሚገኙት ጥያቄዎች ዘላቂ መፍትሔ የማይሰጥ ከሆነ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበሩ ላይ ግጭቶች በድጋሚ ማገርሸታቸዉ እንደማይቀር" ስጋታቸውን የሚግልጹት የአካባቢው ማህበረሰቦች መንግስት ዘላቂ መፍትሄ በማበጀት ስጋታቸውን ሊቀርፍ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ተነስተው አሁን በሲዳማ ክልል ጭሬ ወረዳ ነዋሪ የሆኑትና ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት የማህበረሰቡ አባል እንደሚናገሩት "ከ2011 ዓ.ም. ወዲህ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ተከስቶ የማያዉቅ ቢሆንም በመሬት ይዞታ ይገባኛል ጥያቄ መነሻ ያደረገዉ ግጭት" ስር እየሰደደ ይገኛል። 

በሁለቱ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ “ከመሬት ይገባኛል ጥያቄዎች” በተጨማሪ “የክልል ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ባለፈ በሲዳማ ወይም በኦሮሚያ ምዕራብ ጉጂና አርሲ ዞኖች መካለል እንፈልጋለን” የሚሉ ሀሳቦች እየሰፉ መሄዳቸው በየወቅቱ ለሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ሆነዋል።

"እኔ በምኖርበት አከባቢ በአንድ ዓመት ዉስጥ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ግጭት ይከሰታልም" የሚሉት መረጃ ሰጫችን ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ መሳሪያ የያዙ ታጣቂዎች ከብቶችን ከመዝረፍ በተጨማሪ ተኩስ በመክፈት በአርሶ አደሩ ላይ ጥቃት እንደሚያደርሱም ይገልጻሉ። 

አዲስ ዘይቤ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአከባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት “የሲዳማ ክልል መሆንን ተክትሎ በተፈጠረዉ ግጭቶች አሁን ለሚከሰተዉ ችግሮች የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል” ያሉ ሲሆን “ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በሲዳማ ክልል በሚገኙ አዋሳኝ የሆኑት ቦታዎች ላይ የሚኖሩት ማህበረሰቦቸ በኦሮሚያ ክልል ስር መሆን እንፈልጋለን” የሚል ጥያቄም ማንሳታቸዉን ተናግረዋል። 

በተደጋጋሚ ለግጭት መንስኤ የሆኑትን ጥያቄዎች አስመልክቶ ከስድስት ጊዜ በላይ የሁለቱም ክልል መንግስታት ዉይይት ማድረጋቸውን የሚገልጹት የአሮርሳ ነዋሪው አቶ በአጅጉ አደገ “መሪዎቹ በውይይቶቻቸው ጊዜያዊ  መፍትሔ ከመስጠት ባለፈ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አልተቻላቸውም” ብለዋል። 

እንደ አቶ በአጅጉ ገለጻ "በሲዳማ ክልል እና ዞኖቹን የሚያስተዳድሩ አመራሮች በወቅቱ የሚፈጠረዉን ችግሮች ከማስታገስ ዉጪ ዘላቂ መፍትሔ መስጠት አለመቻላቸው” ጊዜን እየጠበቀ ለሚነሳዉ ግጭቶች ምክንያት ሆነዋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ እና ምዕራብ አርሲ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል ከሚያዋስኗቸዉ አከባቢዎች ዙሪያ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. የደረሰዉን ግጭት ጨምሮ ከስድስት ጊዜ በላይ ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ሲደርስ በርካቶች ህወታቸዉ እንዲያጡ መሆናቸው ይታወሳል።

አስተያየት