መጋቢት 13 ፣ 2014

ከ20 በላይ ድረ-ገጽ የገነባው የ16 ዓመት ታዳጊ

City: Hawassaቴክ

ታዳጊው በቅርብ የሚመለከተውን ችግር ለመፍታት ከገነባቸው ድረ-ገጾች መካከል በኦንላይን የባስ ቲኬት መቁረጫ፣ ኦንላይን መገበያያ ይገኙበታል፡፡

Avatar: Eyasu Zekariyas
ኢያሱ ዘካርያስ

ኢያሱ ዘካርያስ በሀዋሳ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

ከ20 በላይ ድረ-ገጽ የገነባው የ16 ዓመት ታዳጊ
Camera Icon

Credit: Eyasu Zekariyas

የ16 ዓመቱ ታዳጊ ዳግማዊ ሌንጮ ከ20 በላይ ድረ-ገጾች ገንብቶ ለግልጋሎት ክፍት አድርጓል። የሀዮሌ አንደኛ እና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በስማርት ስልክ እና በኮምፒውተር በመጠቀም ድረ-ገጾችን ማበልጸግ የጀመረው ከ2 ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራል። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት “ለጊዜ ማሳለፊያ እንደ ቀልድ ስጀምረው ወደድኩት፤ ከዚያም ቀጠልኩበት” ይላል።

ታዳጊው በቅርብ የሚመለከተውን ችግር ለመፍታት ከገነባቸው ድረ-ገጾች መካከል በኦንላይን የባስ ቲኬት መቁረጫ፣ ኦንላይን መገበያያ ይገኙበታል፡፡ ለቢዝነስ ተቋማት እና ለበጎ አድራጎት ተቋማት ከገባቸው መካከል ደግሞ ቤልታ ቢዝነስ፣ ደመላሽ ቡና ኤክስፖርት፣ የመልካም ወጣት፣ ብላታ ቢዝነስ፣ አሴ ኒኮላስ ይገኙባቸዋል።

ለጥረቱ እና ከእድሜው በላይ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከ10 በላይ ሰርተፊኬቶችን አግኝቷል። እውቅናውን ከሰጡት ተቋማት መካከል የሐዋሳ ከተማ ትምህርት ቢሮ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር፣ ይገኙበታል፡፡ የድረ-ገጽ ማጎልበቻ ከሆኑ ተቋማት መካከል ደግሞ ከSolo learn, ከGoogle Digital garage ,ከeagle Coded, ከCenter of Human Right, ከStem center ያገኛቸው ሰርተፍኬቶች ይጠቀሳሉ። 

“ለዌብሳይት ሥራዬ Studio, Adobe Xd, Xampp Server, Java Idea, Brackets, የተባሉ ሶፍትዌሮችን እጠቀማለሁ” የሚለው ታዳጊው ፍላጎት ካላቸው 7 የእድሜ እኩዮቹ ጋር በመሆን የሶፍትዌር የማበልጸግ ስራዎችን መስራት መጀመራቸውን ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል።

ወደ ዌብሳይት ግንባታ የተሳበው በማኅበራዊ ሚዲያ (ቴሌግራም) አማካኝነት በአጋጣሚ ከተዋወቀው እና ነዋሪነቱን በባህር ማዶ ካደረገ “ጆን ስሚዝ” የሚባል ፕሮግራመር ጋር ሐሳብ መለዋወጥ ከጀመረ በኋላ መሆኑን ይናገራል። ፕሮግራመር ወዳጁ ልምድ እና እውቀቱን ከማካፈል በተጨማሪ አስፈላጊ ኮዶችን እና ትምህርታዊ ድረ-ገጾችን በመላክ ከፍ ያለ ድጋፍ አድርጎለታል። 

የ16 ዓመቱ ታዳጊ ተማሪ ዳግማዊ የመጀመሪያውን ዌብሳይት የገነባበትን አጋጣሚ ሲናገር “ኮሮናን ለመከላከል ሁሉም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ታግዶ ትምህርት ተዘግቷል፡፡ እኛ ግን በየጊዜው ትምህርት ቤት እየሄድን የፈተና እና የአሳይመንት ወረቀቶቻችንን እንቀበል ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ዌብሳይት ለመስራት የተነሳሳሁት ያን ጊዜ ነው” ሲል ያስታውሳል፡፡ የኮቪድ ንክኪን ለመቀነስ ይረዳል ያለውን የዌብሳይት ሐሳብ አሳድጎ ከ250 በላይ የክፍሉ ተማሪዎች ቤታቸው ሆነው ውጤታቸውን መመልከት የሚችሉነትን ድረ-ገጽ መስራቱ የመጀመርያ ሥራው ነበር፡፡

ከታዳጊው ሥራዎች መካከል የ8ኛ ክፍል ሐገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና (ሚኒስትሪ) ውጤትን የሚያሳየው ድረ-ገጽ አንዱ ነው። ከ20 በላይ በሆኑ አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች ሞክሮ ተግባራዊነቱን አረጋግጧል። ተማሪዎች ኢንተርኔት ባለበት ቦታ ሁሉ ሆነው (ወደሚማሩበት ተቋም በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው) ሊጠቀሙበት ይችላሉ። የተማሪ መለያ ቁጥር (ID) በማስገባት የሚኒስትሪ ውጤታቸውን መመልከት እንዲችሉ ታስቦ የተሰራው ድረ-ገጽ በመምህራን እና በተማሪዎች ተወዳጅነትን አትርፏል።

ሀልዮ ት/ቤት የአይቲ አስተማሪ የሆኑት መምህር ኤፍሬም ታምራት “ድረ-ገጹ በቀጣዩ ዓመት በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ በሚገኙ ከአራት በላይ ትምህርት ቤቶች ተግራዊ ይደረጋሉ። በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም የ8ተኛ ክፍል ተማሪዎች ያገለግላል” ብለዋል። ሁሉም የክልሉ ተፈታኞች የሚኒስትሪ ውጤታቸውን እንዲመለከቱ የሚያስችለውን ዳታ በመሰብሰብ ላይ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል። ወደ 100ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን የሚያካትተው የዳታ ስብሰባ እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም ሰምተናል።

ታዳጊ ዳግማዊ “አብሮኝ የሚሰራ እፈልጋለሁ። እኔን እና የቡድን ጓደኞቼን በገንዘብም ሆነ በማቴሪያል የሚያግዘን ብናገኝ ከዚህ በላይ በርካታ ችግር የሚቀርፉ ድረ-ገጾች፣ መተግበሪያዎች፣ ሶፍትዌሮች መስራት እንችላለን” በማለት ለአዲስ ዘይቤ ተናግሯል።

አስተያየት