መስከረም 3 ፣ 2011

ሰሜን አዲስ አበባ ውጥረት አለ፤ የከተማው ሕዝብ ሥጋት ላይ ነው፡፡

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎችኹነቶች

በዛሬው ዕለትም ከኦሮሚያ ክልል በጭነት መኪና እና በእግር ወደ ከተማዋ በመጓጓዝ የኦነግን(ሸኔ) የድርጅት ሰንደቅ ዓላማ አስፋልት ጠርዝ ላይ በሚቀቡ…

ሰሜን አዲስ አበባ ውጥረት አለ፤ የከተማው ሕዝብ ሥጋት ላይ ነው፡፡
በዛሬው ዕለትም ከኦሮሚያ ክልል በጭነት መኪና እና በእግር ወደ ከተማዋ በመጓጓዝ  የኦነግን(ሸኔ) የድርጅት ሰንደቅ ዓላማ  አስፋልት ጠርዝ ላይ በሚቀቡ  ወጣቶችና (ቄሮ) እና በከተማ ነዋሪው መካከል በትናንትናው እለት የጀመረው ግጭት እንደቀጠለ ነው፡፡በመኪናና በእግር የሚገባው ኃይል “ፊንፊኔን ከን ኬኛ!” [ፊንፊኔ የኛ ናት!] እያለ ሲጨፍር ተሰምቷል፡፡ በትላንትናው ዕለት የጀመረው ግጭት በዋናነት ሊፈጠር የቻለው ቀደም ሲል የአዲስ አበባ ነዋሪዎች (በፓስተርና አካባቢው) በየበራቸውና በየመንደራቸው ሰቅለውት የነበረውን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ (አረንጓዴ፤ ቢጫና ቀይ) ተሰቅሎ ከሰነበተበት በማውረድ በምትኩ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግን (ሸኔ) የድርጅት ሰንደቅ ዓላማ ኃይልና ጉልበት በተቀላቀለበት ሁኔታ በመስቀላቸውና በየመንገዱ በመቀባታቸው ነው፡፡በዛሬው እለትም ተጠናክሮ በቀጠለው የሰንደቅ ዓላማ ውዝግብ በተለይ ከፓስተር እስከ አውቶቡስ ተራ ባለው የከተማው ክፍል  የአዲስ አበባ ወጣቶች በመኪና ተጭኖ ከመጡት ቄሮዎች እና በመካከል ገብቶ ከነበሩት ከአድማ በታኝ ፖሊሶች ጋር ተጋጭተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ፖሊስ የአስለቃሽ ጭስ ተኩሷል፡፡ ውጥረቱ በአዲሱ ገበያ አካባቢም ነግሷል፤ ተኩስ እየተሰማ እንደሆነ የአዲስ ዘይቤ ምንጮች ገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰሜን አዲስ አበባ ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሯል፡፡ ከፒያሳ አራት ኪሎ ሙሉ ለሙሉ ንግድ ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ ከጊዮርጊስ እስከ አውቶቡስ ተራ ሱቆች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተዋል፤ ምን አይነት የሕዝብ ትራንስፖርት የለም፡፡ በአውቶቢስ ተራ እና አካባቢው ኃይል የተቀላቀለበት ግጭት ተከስቷል፡፡ ሰባተኛ አካባቢ በጭስ ተሞልቷል፤ ውጥረትም ነግሷል፡፡ የአካባቢው ወጣቶች በቡድን በቡድን እየሆኑ ይንቀሳቀሳሉ፡፡በትላንትናው እለት ግጭቱን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ኃይማኖት ዘለቀ  መንግስት በሆደ ሰፊነት የጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ሕብረተሰቡም መተግበር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድም በዛሬው እለት ባስተላለፉት መልእክት በሰንደቅ ዓላማ መጋጨት ችግሮቻችንን እንደማይፈታ ገልፀው፤ በተለይም በመጪው ቅዳሜ ወደ አገር ቤት የሚገቡ  የኦነግ አመራሮች አሁን እየታየ ያለው ሰንደቅ አላማን ሰበብ ያደረገ ግጭት ወደከፋ አቅጣጫ እንዳይሄድ ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ዘይኑ ጀማል  በዛሬው ዕለት ለሸገር ሬዲዮ እንደገለጹት በመጪው ቅዳሜ የኦነግ [ሸኔ] ደጋፊዎች የፈለጉትን ሰንደቅ ዓላማ እንዲይዙ የተፈቀደ መሆኑን ገልጸው፤ ቋሚ ንብረቶችና መንገዶችን ቀለም መቀባት ግን የተከለከለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የኦነግ(ሸኔ) አቀባበል ኮሚቴ ቃል አቀባይ ኦቦ ቶሌራ አደባ በሰጡት መግለጫ ቄሮ ከግጭት እንዲታቀብ ነገር ግን በሰላም ተግባሩን እንዲያከናውን አሳስበዋል፡፡ አያይዘው ሲናገሩም በከተማዋ ቀለም መቀባቱን ስህተት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡የተሰቀሉትም ሰንደቅ ዓላማዎች ከበአሉ በኋላ እንደሚነሱም አሳውቀዋል፡፡ አክለውም ፊንፊኔ የኦሮሚያ አካል መሆኗ ባይካድም የሁሉም ብሄሮች መኖሯም የታወቀ ሥለሆነ ነገሮችን በስምምነት ማካሄድ እንዳለባቸው ኦቦ ቶሌራ አዳባ ተናግረዋል፡፡“ቀለም ቀቡ!” እንዴት ተጀመረ? “ቀለም ቀቡ” የሚል ቅስቀሳ ከባህርማዶ የተጀመረው ከሳምንት በፊት የአርበኞችና ግንቦት 7 ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራሮችን ለመቀበል በአገር ውስጥ ያሉ ደጋፊዎቻቸው በየመንደራቸው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን መስቀላቸውንና ዝግጅቱን ማድመቃቸው ብስጭትና ቁጭት ባደረባቸው ጥቂት የኦሮሞ አክቲቪስቶች ነው፡፡  “ቀለም ቀቡና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማን አጥፉ!” የሚለውን አፍራሽ መልእከት ሲያስተላለፉ የሰነበቱት በአውስትራሊያና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ አክቲቪስቶች የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለምን እንደማየት የሚጠሉት ነገር እንደሌላቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ቀስቃሾች ነጋ ጠባ በፌስቡክ ገጾቻቸው አሁን በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ በመምጣት ላይ ያለውን ለውጥ በማቋሸሽና ጸረ-ኢትዮጵያ መልእክትን በማስተላፍ  ይታወቃሉ፡፡ የዳውድ ኢብሳ ኦነግ(ሸኔ) ወደ አገር ቤት መግባትን በማስታከክ ቀደም ሲል የጀመሩትን የ “ቀለም ቀቡ” ዘመቻ ገፍተውበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በእቴጌ ጣይቱ የሀውልት ሥራ ፕሮጀክት ላይም ከፍተኛ ዘመቻ በመክፈት እቅዱ  እንዲስተጓጎል በአዲሱ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ላይ ጊዜውን ያልጠበቀ ጫና መፍጠራቸው የሚታወስ ነው፡፡ቅስቀሳው ሲጀመር የመንግሥት ኃላፊዎች ምን ሲሰሩ ነበር? ቅስቀሳው ሲጀመርና የውጥረቱ ምልክቶቹ ሲታዩ የከተማው አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግስት አንድም ጉዳዩ “የትም አይደርስም” በሚል መንፈስ በቸልተኝነት እንደተኙ፤ አሊያም መዋቅራዊ አቅም በማጣት ቀላል ሆነው ባገኙት ስብሰባና ጉዞ ላይ ጊዜያቸውን ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ቀስቃሾቹ በፀያፍ ሥድብ የታጀበ  ጠብ አጫሪ ዘመቻ ሲከፍቱ የከተማውንና ሌላውንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጣ የሚቀሰቅስ እቅድ ሲያወጡ የከተማው አስተዳደርም ሆነ የሚመለከታቸው የፌደራል መንግስት አካላት ጉዳዩ ገፍቶ እስኪመጣ ድረስ በዝምታ ተመልከተውታል፡፡ጸጥታ አለማስከበር ያሉት ፖለቲካዊ አንድምታዎች ምንድናቸው?በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በፌደራል መንግስት በኩል የሚስተዋለው ይህ መሰሉ ጸጥታና ሥርዐት ለማስከበር አለመቻል ፖለቲካዊ አንድምታዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ በአንድ በኩል ጸጥታንና ሥነ ሥርዓትን ለማስከበር ያለው አቅም ጥያቄ ውስጥ ሲገባ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኃይሎች ዘንድ እየገነባ ያለውን የቅቡልነትና የይሁንታ አስተያየት ያጣል፡፡ በሌላ በኩል አዲሱ የኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ከኦህዴድ ተወክለው እንደመምጣታቸው  በሥመ ‘ቄሮ’ በግልጽ እንደ  ሻሸመኔ አይነቱን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽምና አሁንም ከመፈጸም ወደ ኋላ በማይለው ኃይል ላይ ለዘብተኛ መሆናቸው በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በማግኘት ላይ ያለውን ቅቡልነት ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚከታቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ አንዳንድ ኃይሎች ሀገሪቷ ይህንን የሽግግር ወቅት አልፋ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከማለፏ በፊት ለተደበቀ እኩይ ዓላማ እየተፋጠኑ መሆኑን ያሳያል፡፡

አስተያየት