(አዲስ ዘይቤ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር አሰሪው በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ በማኅበሩና በአባላቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ አንደሚገኝ አመራሮቹ ለአዲስ ዘይቤ ተናገሩ፡፡
የማኀበሩ አመራሮች አየር መንገዱ የተለያዩ መሰናክሎችን ሲፈጥር መቆየቱን ጠቅሰው በኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበር ኮንፌዴሬሽን ጠሪነት (ኢሰማኮ) መስከረም 10፣ 2012 ማኀበሩ ሊመሰረት እንደበቃ ተናግረዋል፡፡
አየር መንገድ ግሩፕ በመሰረታዊ የሰራተኛ ማኀበር አመራሮች የተለያየ መልክ ያለው ጫና ያደረሰባቸው እንደሆነና የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው በሚልም መሰረት የሌለው ውንጀላ እየቀረባበው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አንዳንዶቹን የማህበሩ አመራሮችን ከስራ የማገድ፣ ከስራ የማባረር፣ በግዳጅ የስራ ፍቃድ እንዲወስዱ ማድረግ፣ ስራ ያለመመደብ፣ ከስራ ውጪ የማድረግ እንዲሁም በግዳጅ ወደ ሌሎች ማዕከሎች (stations) እንዲመደቡ እና ሌሎች ተመሳሳይ በደሎች እየደረሰባቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
እንዲሁም ተቋሙ ሠራተኞች እርስ በርስ የመገናኛ መድረክ (communication platform) ባለማመቻቸቱ ምክንያት ሠራተኛው በኢ-መደበኛ መልኩ በቴሌግራም ግሩፕ መልዕክቶችን ለመለዋወጥ እንደተገደደ ገልጸው ነገር ግን ድርጅቱ የተቋሙን ስም የሚያጠፋ መልዕክት ጽፋችኃል፤ ተጋርታችኋል በሚል ማሸማቀቅ እያደረሰባቸው እንደሆነ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኀበር የምስረታ ጉባዔን ካካሄደበት ከመስከረም 10፣ 2012 ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ከ3 ሺህ 800 በላይ አዳዲስ አባላትን መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ምዝገባ በሚያካሂዱበት ወቅት አንዳንድ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ይመለከታል በሚል አየር መንገዱ በጥቅምት 17፣ 2010 ዓ.ም የማስጠንቀቂያ ደብደቤ ጽፏል፡፡ የደብዳቤው ጥቅል ይዘት ኢንዱስትሪውን በሚጎዳ መልኩ በደርጅቱ ግቢ እና በድርጅቱ የስራ ሰዓት አንዳንድ ሰራተኞች የአባላት ምዝገባ እያካሄዱ መሆኑን የሚጠቅስ ሲሆን ድርጅቱ ቅጥር ግቢ፣ በሠራተኞች መጓጓዣ ውስጥ፣ ውጪ ሀገር በሚገኙ ሆቴሎች፣ ምዝገባ ማድረግ እንደማይችሉና ይህንንም ሲያደርጉ ቢገኙ የስራ ውል እስከማቋረጥ እንደሚደርስ የሚገልጽ የኢሜይል መልዕክት መላኩን የማኀበሩ አመራሮቹ ይናገራሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ ዘይቤ ከሌሎች ምንጮች ባገኘችው መረጃ መሰረት የአብራሪዎች የሙያ ማኅበር፣ በማኅበራችን የታቀፉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውስጥ የሚሰሩ አብራሪዎች የተጋረጠባቸው የበረራ ደኅንነት ስጋት በሚል ለኢትዮጵያ አመራር ግሩፕ ኮርፖሬት ሴፍቲ እና ለኢትዮጰያ አየር መንገድ ግሩፕ ስራ አመራር ስጋቱን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደጻፈ ተረድተናል፡፡
ድርጅቱ በኢ-መደበኛ መልኩ ያቋቋመውን የቴሌግራም ግሩፕ ውስጥ ሰብሮ በመግባት በሕገ መንግስቱ የተጠቀሰውን የመናገር ነጻነት በሚገድብ መልኩ ሠራተኞች በዚሁ የመገናኛ ዘዴ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ምክንያት ከስራ የመታገድ፣ የማባረር፣ ቢሮ ጠርቶ የማስፈራራት እንዲሁም መሰል የመብት ጥሰቶች እየተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ አብራሪዎች ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ማሳደር የበረራ ደኅንነቱን ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስገባ የሙያ ማህበሩ ደብዳቤ ያትታል፡፡ እንዲሁም አብራሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ያለመረጋጋት እየተከሰተ በመሆኑ በበረራው ደኅንነት ላይ እክል ከመፈጠሩ በፊት የችግሩን አንገብጋቢነት በመረዳት ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ አካላት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን እርምት እንዲወስዱ ይጠይቃል፡፡
- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሰረታዊ የሰራተኛ ማኅበር