መስከረም 4 ፣ 2013

ኮቪድ19ን በመዋጋት ላይ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችን ታሪክ የሚያትተው የፎቶ ዘገባ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በኢትዮጵያ በሚገኘው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚገኙ የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ስለሚያጋጥሟቸው…

ኮቪድ19ን በመዋጋት ላይ የሚገኙ የህክምና ባለሙያዎችን ታሪክ የሚያትተው የፎቶ ዘገባ
በኢትዮጵያ በሚገኘው ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚገኙ የተለያዩ የህክምና ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ስለሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ጫናዎች የሚያትት የፎቶ ዘገባ ዘጋርድያን የተሰኘው የዜና አውታር ይዞ ወጥቷል። የኢትዮጵያዊውን ፎቶግራፈር ዮሃንስ ታደሰ ስራዎች ያካተተው የፎቶ ኤሴይ (Photo Essay) ቫይረሱን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦችን ታሪክ ይዘግባል። ዶክተሮች፣ ነርሶች፣ ፅዳቶችና የጥበቃ ስራ ባለሙያዎች ያካተተው ዘገባው ቫይረሱን በመከላከል ወቅት ሰራተኞቹ የሚገጥማቸውን ስነልቦናዊ ጫናን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳዮችን ያነሳል። ዶ/ር ቃልኪዳን በኢትዮጵያ በመጋቢት ወር የተገኘውን ጃፓናዊ የኮሮና ቫይረስ ታማሚ እንደተቀበለች በመናገር በወቅቱ የመጀመርያውን የኮሮና ቫይረስ ታማሚ የመንከባከቡ ስራ ፍርሀት አሳድሮባት እንደነበረ ትናገራለች። “ታማሚው ወደ ህክምና ማዕከል ይመጣል ብለን አልጠበቅንም ነበር። የህክምና ማዕከሉን እንድናዘጋጅና ታማሚያንን እንድናስተናግድ ትዕዛዝ ተሰጥቶን የነበረ ቢሆንም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ወደ ማዕከሉ ሲመጣ ግን ተደናግጠን ነበር” የምትለው ዶ/ር ቃልኪዳን ቫይረሱን በዚህ ልክ መፍራት አይጠበቅብንም ትላለች።በፎቶ በተደገፈው ዘገባ ላይ የተጠቀሰው በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ውስጥ ሳኒታይዘር በመርጨትና በጥበቃነት የሚያገለግለው ወርቅነህ ሆራ በበኩሉ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ላይ መሳተፉን አስታውሶ ይህን ስራ ከአገር ግዳጅ ለይቶ እንደማይመለከተው ይገልፃል። “በሆስፒታሉ ውስጥ በጥበቃነትና በሳኒታይዘር መርጨት ስራ ላይ በመሰማራት አገሬን በማገልገል ላይ እገኛለው። በተጨማሪም በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፉ ግለሰቦችንም በመቅበር ስራ ላይ ተሳታፊ ነኝ።” ያለው ወርቅነህ በጦርነት ማለፉ ሞትን እንዳይፈራ ስላደረገው ወደ ስራው ለመግባት ስጋት እንዳላደረበት ይናገራል።ሌላኛው በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ውስጥ እንደወርቅነህ ሳኒታይዘር በመርጨት ስራው ላይ የተሰማራው ጳውሎስ ሰኢድ በበኩሉ በሆስፒታሉ ቫይረሱ ከመከሰቱ በፊት ለአምስት ወራት ያህል በጥበቃነት እንዳገለገለ ገልፆ “ቫይረሱን ለመከላከል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የሰው ሀይል በማነሱ ምክንያት ወደ ሳኒታይዘር መርጨት ስራ እንድገባ ተጠየኩኝ።” በማለት ወደስራው የገባበትን ሁኔታ ያስታውሳል። ጳውሎስ ሳኒታይዘር መርጨቱ ቫይረሱን እንዳጠፋው ያህል ስሜት ስለሚሰጠው ስራውን ቢወደውም ድሮ አብረውት የሚሆኑ ጓደኞቹ ጋር ግን በዚህ ስራ አማካኝነት እንደማይገናኝ ይናገራል። “በእግዚአብሄር ስም እንዳልጠጋቸው ይጠይቁኛል። ይህ ልብ የሚሰብር ነገር ነው” በማለት ጳውሎስ በስራው ላይ በመሰማራቱ አማካኝነት የደረሰበትን መድሎ በዘገባው ላይ ተናግሯል። በነርስነት በሆስፒታሉ በማገልገል ላይ የምትገኘው ነርስ ማክዳ በበኩሏ በሆስፒታሉ ካሳለፈቻቸው ጊዜያት የከፋው የመጀመርያው የኮሮና ቫይረስ ታማሚ ህይወት ያለፈበት ቀን እንደሆነ ተናግራ በሆስፒታሉ በሰራችበት ወቅት ስለቤተሰቦቿ፣ ስለአገሯና ስለህዝቡ ብዙ ለማሰብ አጋጣሚውን እንዳገኘች ትናገራለች። በአንፃሩ ዶ/ር ረድኤት በሆስፒታሉ ውስጥ በህክምና በምታገለግልበት ወቅት የእርዳታ ጥሪ ካደረጉ በኋላ የመጀመርያ እርዳታ ጥሪ ተደርጎላቸው ከሞት አፋፍ ስለተረፉት አቶ ተስፋዬ አስታውሳ “የእርዳታ ጥሪውን መስማታችን እድለኝነት ነው።” በማለት የግለሰቡን ህይወት ያተረፈችበትን ወቅት በዘገባው ታስታውሳለች። ዘገባው አክሎም በሆስፒታሉ በፅዳትነት በማገልገል ላይ የምትገኘውን የደሞዝ ታሪክ ያጋራ ሲሆን የ3 ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ደሞዝ የደም ግፊት በሽታ ቢኖርባትም ካለባት ኢኮኖሚያዊ ሀላፊነት የተነሳ ይህን ስራ ለመስራት መገደዷን ትገልፃለች። የስራ ባልደረባዋ የ50 አመቷ ወ/ሮ እታገኝ ተሰማ በበኩላቸው “ቫይረሱ በተከሰተበት ወቅት ቤተሰቦቼን የምደግፈው እኔ ስለነበርኩኝ ይህን ስራ እንደሰራ ጥያቄ ሲቀርብልኝ አላቅማማሁም።” በማለት ወደ ስራው የገቡበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ። እንደ ወ/ሮ እታገኝ ገለፃ ከሆነ ከዚህ ቀደም በወዳጅነት ለረጅም አመታት አብረዋቸው የቆዩ ጎረቤቶችና ጓደኞች አሁን እንደሚያርቋቸው ገልፀው ቫይረሱ ተወግዶ ወደመደበኛው ማህበራዊ ህይወታቸው ለመመለስ ያላቸውን ጉጉት ገልፀዋል። የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ከተገኘበት ወቅት አንስቶ 186 ቀናት ያለፉ ሲሆን እስከአሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 64,301 መድረሱን ከአለም የጤና ድርጅት መረዳት ይቻላል። በተጨማሪም ተመሳሳይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ 24,983 ታማምያን ከቫይረሱ ሲያገግሙ 1,013 ወገኖች ደግሞ ህይወታቸውን በኮቪድ19 የተነሳ አጥተዋል። ፎቶ፡ በዮሀንስ ታደሰ የተነሳና ከዘ ጋርድያን (The Guardian) መካነ ድር የተወሰደ።

አስተያየት