መስከረም 5 ፣ 2013

በፌስቡክ ድህረገፅ ላይ እየጨመረ የመጣው የጥላቻ ንግግር ኢትዮጵያን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊወስዳት ይችላል ተባለ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በፌስ ቡክ ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየጨመረ የመጣው የጥላቻ ንግግር አገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ግጭቶችና ወደ ከፋ የፀጥታ ችግር…

በፌስቡክ ድህረገፅ ላይ እየጨመረ የመጣው የጥላቻ ንግግር ኢትዮጵያን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ሊወስዳት ይችላል ተባለ
በፌስ ቡክ ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየጨመረ የመጣው የጥላቻ ንግግር አገሪቱን ወደ እርስ በእርስ ግጭቶችና ወደ ከፋ የፀጥታ ችግር ሊከታት ይችላል በማለት ቫይስ ኒውስ (Vice News) ዘገበ። የዜና አውታሩ በትላንትናው እለት ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያውያን ዘንድ እየጨመረ የመጣው የጥላቻ ንግግር የፌስቡክ ቸልተኝነት ታክሎበት ኢትዮጵያን ወደ ተለያዩ ዘር ተኮር ግጭቶች እየመሯት ነው።በሰኔ ወር የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ብጥብጥ ወቅት በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ የተከሰተውን ዘር ተኮር ጥቃትና ግድያ እንደዋቢነት ያቀረበው ዘገባው በወቅቱ ምንም እንኳን መንግስት የኢንተርኔት አገልግሎትን ከሀጫሉ ግድያ በኋላ በሰዐታት ውስጥ ቢዘጋም የተለያዩ ጥላቻን ያነገቡና አንድን ብሄር ወይም ሀይማኖት ለግድያው ተጠያቂ ያደረጉ መረጃዎች በማህበራዊ ድህረ ገፁ ላይ ተንሰራፍተው እንደነበረ ያስረዳል። በወቅቱ አማራ፣ ጉራጌና የኦሮሞ ክርስትያን የሆኑ ግለሰቦች የግድያና የንብረት አደጋ እንደደረሰባቸው ዘገባው አክሎ አስታውሷል። ከጥቅምት 2009 እስከ ጥር 2009 ድረስ የቆየውና የብዙ ሮሂንጋ ሙስሊሞችን ህይወት የቀጠፈውን የማይናማርን ተሞክሮ ያስታወሰው ዘገባው በወቅቱ ፌስ ቡክ ሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በደረሰው በደል ላይ እንደመጠቀምያ ሆኖ እንደነበር ዘገባው ይዘክራል። አክሎም ዘገባው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የመናገርና የሀሳብ ነፃነት ልዩ ራፖርቱር ዴቪድ ኬይን አጣቅሶ በኢትዮጵያ ከሚታየው የጥላቻ ንግግር ስር መስፋፋትና ከፌስ ቡክ ተገቢውን ጥንቃቄ አለማድረግ የተነሳ ኢትዮጵያም ተመሳሳይ እጣ ፋንታ ሊያጋጥማት እንደሚችል አስጠንቅቋል። ዘገባው በፌስ ቡክ በኩል እየተላለፉ ነው ወይም ተላልፈዋል ያላቸው መልዕክቶች በዘርና በሀይማኖት ለይተው የግድያና የጥቃት መልዕክት ከሚያስተላልፉት አንስቶ በቤት ውስጥ ፈንጂዎችን በመስራት እንዴት ከፍ ያለ ጥቃት ማድረስ እንደሚቻል እስከሚያስረዱ መልዕክቶች እንደሚደርስ ያትታል። ፌስቡክ በአፍሪካ አህጉር የተለያዩ የጥላቻ ንግግርን የሚቆጣጠሩ ግለሰቦችን እየቀጠረ ይገኛል ያለው ዘገባው አክሎም በኢትዮጵያ የሚገኘውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ያለመረዳት ችግር በማህበራዊ ድህረ ገፁ ዘንድ ያሉ ችግሮች እንደሆኑ በዝርዝር  ያስረዳል። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዋና አቃቢ ህግ ጌድዮን ጢሞትዮስ ከሹመታቸው ቀጥሎ የጥላቻ ንግግርን መዋጋትን እንደዋነኛ አጀንዳ መያዛቸው የሚታወስ ነው።  

አስተያየት