ነሐሴ 28 ፣ 2012

አለማቀፉ የጥናት ማዕከል መስኖ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት ሊከስት የሚችለው የምግብ ዋስትናና የንፁህ ውሀ ችግር ለመግታት ወሳኝ ሚና አለው አለ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በኢትዮጵያ መስኖ በሚጠቀሙና በማይጠቀሙ ገበሬዎች መካከል ቫይረሱ ስላለው የተለያየ የተፅዕኖ መጠን ልዩነትና መስኖ የምግብ ዋስትናን…

አለማቀፉ የጥናት ማዕከል መስኖ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት ሊከስት የሚችለው የምግብ ዋስትናና የንፁህ ውሀ ችግር ለመግታት ወሳኝ ሚና አለው አለ
የኮቪድ-19 ወረርሺኝ በኢትዮጵያ መስኖ በሚጠቀሙና በማይጠቀሙ ገበሬዎች መካከል ቫይረሱ ስላለው የተለያየ የተፅዕኖ መጠን ልዩነትና መስኖ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥና ዝናብ የማይዘንብባቸው ወቅቶች በምርታማነት ለማሳለፍ ያለውን ፋይዳ የሚያትት ጥናት አለምአቀፉ የጥናት ማዕከል ኢንተርናሽናል ዋተር ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት (The International Water Management Institute) አወጣ።የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝን ተከትሎ በኢትዮጵያ የተፈጠሩት የሰዎች እንቅስቃሴ ገደብ፣ የንግድ ሰንሰለት መዛባት፣ የምርት ዋጋ ማሽቆልቆል፣ የትራንስፖርት ዋጋ ማሻቀብና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች በአገሪቱ ገበሬዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን እያደረሱ ነው ያለው ድርጅቱ በአማራ ክልል ዳንግላ ዞን ልዩ ስሙ ዳንግፃ በመባል በሚታወቀው አካባቢ የሚኖሩ 32 ገበሬዎችንና ቤተሰቦቻቸውን እንዳነጋገረ በዘገባው አስረድቷል።መስኖን የሚጠቀሙ ገበሬዎች መስኖ ከማይጠቀሙ ገበሬዎች የተሻለ የምግብ ዋስትና እንዳላቸው የጥናቱ ውጤት ያሳያል። ጥናቱ እንደሚያስረዳው ከሆነ በጥናቱ ከተሳተፉት ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው መካከል ሁለት ሶስተኛ ያህሉ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ ከቀድሞ ያነሰ የአትክልት ምርት እየተመገቡ ይገኛሉ። ነገር ግን መስኖን የሚጠቀሙ ገበሬዎች በጓሯቸው በሚያመርቷቸው የአትክልት ምርቶች አማካኝነት መስኖ ከማይጠቀሙ ገበሬዎች የተሻለ የምግብ ዋስትናና የተመጣጠነ ምግብን የመመገብ እድል እንደሚያገኙ ጥናቱ ያስረዳል።በአንፃሩ ግን መስኖን የሚጠቀሙ ገበሬዎች በኮሮና ቫይረስና ቫይረሱን ለመከላከል በተወሰዱ እርምጃዎች አማካኝነት መስኖ ከማይጠቀሙ ገበሬዎች የበለጠ የገቢ ማጣት ወይም ኪሳራ እንደገጠማቸው ጥናቱ ያስረዳል። ለዚህም እንደዋና ምክንያትነት የተቀመጠው ቫይረሱ በአገሪቱ ከተገኘበት ወቅት ጀምሮ በነበሩት የመጀመርያ ወራት የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ሲሆን በመስኖ ተጠቅመው ለገበያ ምርት ያመረቱ ገበሬዎች በገደቡና ገደቡ በነጋዴዎች ጉዞ ላይ በፈጠረው ጫና የተነሳ መስኖ ከማይጠቀሙ ገበሬዎች በበለጠ መልኩ በገደቡ መጎዳታቸውን ጥናቱ ያስረዳል። ነገር ግን በእገዳው ምክንያት እንደጫት የመሳሰሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ገበሬዎች ከሌሎች ከተሞች የሚመጣው የጫት ምርት መቀነሱን ተከትሎ ገቢያቸው መሻሻሉን ጥናቱ አክሎ አስቀምጧል።በመጨረሻ መስኖ በሚጠቀሙም ሆነ በማይጠቀሙ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው ዘንድ ቫይረሱ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶ የተሻለ የውሀ አጠቃቀምና የንፅህና ባህል እንደሚስተዋል የጥናቱ ውጤት ያሳያል። ጥናቱ በተካሄደበት አካባቢ የሚገኙ ገበሬዎችና ቤተሰቦቻቸው መካከለኛ ጥልቀት ባላቸው የውሀ ጉድጓዶች የሚጠቀሙ ሲሆን የውሀ ጉድጓድ ያላቸው ቤተሰቦች የራሳቸውም ሆነ የጎረቤቶቻቸው የውሀ አጠቃቀም መጠንም ሆነ ንፅህና ወረርሺኙ ከተከሰተ ወዲህ በእጅጉ እንደጨመረ የጥናቱ ውጤት ያሳያል።የጥናቱ የተሰራው በኢትዮጵያዊው ዳግማዊ መላኩ፣ በኢኒስቲቲውቱ ከፍተኛ ተመራማሪ ታይ ሚን፣ በኢትንስቲቲውቱ የምስራቅ አፍሪካ ተወካው ኤቫ ሉዲና በኢኒስቲቲውቱ በምርምር ቡድን መሪነት በምታገለግለው ፔትራ ሽሚተር እንደሆነ አግሪሊንክስ (AgriLinks) የተሰኘው መካነ ድር ስለጥናቱ ባወጣው መረጃ ገልጿል። በተጨማሪም ዘገባው ኢኒስቲቲውቱ እንደጥናቱ አካል እንዲሆን ከዚህ ቀደም ከአካባቢው ገበሬዎችና ከባህር ዳር ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበር ለገበሬዎች በፀሀይ በሚሰራ የውሀ ፓምፕ አጠቃቀም ዙርያ ስልጠና እንደሰጠ ዘገባው አስታውሷል።

አስተያየት