መስከረም 15 ፣ 2013

ባሳለፍለው አመት ኢትዮጵያ የተለያዩ አበረታች ድሎችን እንዳስመዘገበች የጠቅላይ ሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ተናገሩ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በትላንትናው እለት በአዲሱ የሚድያ ስቱድዮ ከጠቅላይ…

ባሳለፍለው አመት ኢትዮጵያ የተለያዩ አበረታች ድሎችን እንዳስመዘገበች የጠቅላይ ሚንስቴሩ ቃል አቀባይ ተናገሩ
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በትላንትናው እለት በአዲሱ የሚድያ ስቱድዮ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዪን ጢሞትዮስ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አገሪቱ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ አመት የተለያዩ አበረታች ድሎችን አስመዝግባለች አሉ። የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት አመርቂ የሚባል የኢኮኖሚ እድገት አሳይታለች ያሉት ወ/ሮ ቢልለኔ የተለያዩ በአገሪቱ ውስጥ ባሳለፍነው አመት የተሰሩ ስራዎችን ዘርዝረዋል። የብልፅግና ፓርቲ ኢህአዴግን መተካት፣ የህዳሴው ግድብ የመጀመርያ ሙሌት መጠናቀቅ፣ የአገሪቱን የመጀመርያ ሳተላይት በስኬት መምጠቅ፣ በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ያስመዘገባቸው ስኬቶች፣ የሸገርና አንድነት ፓርኮች መመረቅ፣ የህገ ወጥ የገንዘብ፣ የጦር መሳርያና የሰው ዝውውር ላይ የተሰሩ የተለያዩ ፌደራላዊና ክልላዊ ስራዎች፣ ለኮሮና ወረርሺኝ የተሰጠው አገራዊ ምላሽና የአገሪቷ አህጉራዊ ሚና፣ በተለያዩ የአለም ክፍሎች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተሰጠው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ፣ በስራ ፈጠራ ኮሚሽንና በግል ዘርፉ ተሳታፊነት፣ የተፈጠሩ ከሶስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ የስራ እድሎች ከተጠቀሱት ከአገሪቱ አበረታች ድሎች መካከል አንዳንዶቹ ናቸው።ወ/ሮ ቢልለኔ አክለውም ምንም እንኳን በ2012 ዓ.ም የተለያዩ አመርቂ ድሎች የተመዘገቡ ቢሆንም በተለያዩ ወቅቶች የሰላም ችግሮች እንደተከሰቱ የገለፁ ሲሆን በቅርቡ በመተከል አካባቢ የተከሰተውን ግጭት በመጥቀስ የፌደራል መንግስት በአመቱ የተከሰቱትን ግጭቶችን እንደሚያወግዝ ተናግረዋል። ይህንንም ለመፍታት የተለያዩ የህግ የበላይነትን ለማስፈንና የአገሪቱን የደህንነት አቅም ለማሳደግ በሰላም ሚንስቴር የሚመሩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልፀዋል። በተጨማሪም ወ/ሮ ቢልለኔ በአገሪቱ በሚገኙ አምስት ክልሎች ውስጥ የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች በ22 ዞኖች የሚገኙ 43 ወረዳዎች በጎርፍ መጠቃታቸውን አስታውሰው በፌደራል መንግስትና በተገቢው የክልል መንግስታ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር በተሰጠው ምላሽ ምንም አይነት የሞት አደጋ እንዳይከሰት የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል። በመጨረሻም ቃል አቀባዯ በጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድ የተጠራውን “ገበታ ለአገር” የተሰኘውን የአገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ በተቀረፀው መርሀግብር ዙርያ የተለያዩ ነጥቦችን ያነሱ ሲሆን በፕሮግራሙ በአዲስ አበባ የተሰራውን ስራ በአማራ፣ ኦሮምያና ደቡብ ክልሎች ለመድገም የወጠነው እንደመሆኑ መጠን ተገቢው ድጋፍ እንደሚያሻው ተናግረዋል። የ“ገበታ ለአገር” መርሀግብር በሶስቱ ክልሎች ለሚከናወኑት ቱሪዝም ተኮር ስራዎች ሶስት ቢልዮን ብር ለማሰባሰብ ታስቦ የተቀረፀ መርሀግብር ነው።

አስተያየት