መስከረም 18 ፣ 2013

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተባለ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

በኢትዮጵያ በያዝነው አመት የሰሊጥ ምርት በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አማካኝነት ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥመው እንደሚችል ዋጌኒገን ዩንቨርስቲ ኤንድ ሪሰርች…

የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ በኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርት ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል ተባለ
በኢትዮጵያ በያዝነው አመት የሰሊጥ ምርት በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ አማካኝነት ከፍተኛ ጉዳት ሊያጋጥመው እንደሚችል ዋጌኒገን ዩንቨርስቲ ኤንድ ሪሰርች (Wageningen University & Research) የተሰኘው የጥናት ማዕከል አስታወቀ። የጥናት ማዕከሉ የተለያዩ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችንና ድርጅቶች ጋር ካደረገው የዳሰሳ ጥናት በኋላ ይዞት በወጣው መረጃ መሰረት በቀጣዩ አመት የሰሊጥ ምርት መጠን በእጅጉ ሊያንስ እንደሚችል የገመተ ሲሆን አክሎም በሰሊጥ ምርት ላይ የተሰማሩ ገበሬዎችና የቀን ሰራተኞች በኮሮና ቫይረስ የመጠቃት እድላቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ማዕከሉ ተናግሯል። ይህን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርትና ግብይት መረብ የድጋፍ ፕሮግራም ምክትል ስራ አስኪያጅና የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አንተነህ መኩርያ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለፁት ከሆነ የሰሊጥ ምርት የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ከቡና ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ከመደገፍ በተጨማሪ ለበርካታ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ለሚመጡ ገበሬዎችና የቀን ሰራተኞች የስራ እድል ይፈጥራል። “የሰሊጥ ምርት በአገሪቱ ኢኮኖሚና የውጭ ምንዛሬ ላይ ትልቅ ሚናን ይጫወታል። ከዚህ በተጨማሪ ለበርካታ ሰራተኞች የስራ እድልን በመፍጠር የብዙ ገበሬዎችንና የቀን ሰራተኞችን ህይወት ይደግፋል” ያሉት አቶ አንተነህ በኮቪድ19 ወረርሺኝ የተነሳ ግን ዘርፉ መዳከሙን ሳያስታውሱ አልቀሩም።በጥናቱ ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ የሆነው በሰሊጥ እርሻዎች ላይ ስለሚሰሩ የቀን ሰራተኞችና ገበሬዎች የጤና ጉዳይን አስመልክቶ አቶ አንተነህ ለአዲስ ዘይቤ የሰሊጥ ምርት በአገሪቱ ሜካናይዝድ ካለመደረጉ የተነሳ ከ500,000 በላይ ለሚሆኑ ከአገሪቱ ደጋማ ስፍራዎች ለሚመጡ የቀን ሰራተኞችና ገበሬዎች የስራ እድልን እንደሚፈጥር ገልፀዋል። ባለሙያው አክለውም ምርቱ እስከሶስት ድረስ እንደሚታረም አስታውሰው በወቅቱ የተንሰራፋው የኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ግን በዘርፉ የተሰማሩ ሰራተኞችን ሊያጠቃ እንደሚችል ተናግረዋል። በሰራተኞቹ የኢኮኖሚ አቅም ማነስና በሽታውን ለመከላከል በሚያስፈልጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች ዙርያ ከሚታየው የእውቀት ማነስ የተነሳ የበለጠ ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ እንደሚያሰጋ የገለፁት አቶ አንተነህ “ሰራተኞቹ አብረው ነው የሚጓዙት። በካምፖችም ውስጥ አብረው ነው የሚኖሩት። ይህም ቫይረሱ በቀላሉ እንዲተላለፍ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል።” በማለት በዘርፉ ስለተሰማሩ ሰራተኞች የጤና ሁኔታ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል። በተጨማሪም አቶ አንተነህ “ማስተዋል ያለብን የተጠቀሱት ሰራተኞች ስራቸውን ለመስራት ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ የቀን ሰራተኞች ናቸው። ስለዚህ ለቫይረሱ ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ወደመጡባቸው ስፍራዎች በሚመለሱበት ወቅት በሽታውን የማሰራጨት እድላቸው ከፍተኛ ነው።” ያሉት አቶ አንተነህ ለጉዳዩ ተገቢው ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ሳያስታውሱ አላለፉም።ይህ በእንዲህ እንዳለ በምርት አመቱ መጀመርያ ባለፈው አመት ከነበረው የምርት እጥረትና በቫይረሱ አማካኝነት ከተተገበረው የእንቅስቃሴ መገታት አንፃር የሰራተኞች እጥረት ይከሰታል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በአንፃሩ ገበሬዎች ወደማሽላ ምርት ከማድላታቸው የተነሳ የሰራተኞች እጥረቱ በተጠበቀው ልክ እንዳልሆነ አቶ አንተነህ ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የሰራተኞች ደመወዝ ካለፈው የምርት አመት አንፃር እንደቀነሰ የተናገሩት ባለሙያው አክለውም “በቫይረሱ አማካኝነት የሰራተኞች አቅርቦት ይቀንሳል ተብሎ ቢገመትም፣ ስራው ለአብዛኞቹ ገበሬዎችና ወቅታዊ ሰራተኞች አስፈላጊ ስለሆነ ይህ ሳይሆን ቀርቷል።” በማለት ዘርፉ ከኮሮና ቫይረስ መከሰት ወዲህ ስላሳየው ለውጥ አብራርተዋል። በመጨረሻም አቶ አንተነህ ዘርፉን ለመደገፍ መደረግ አለበት ስለተባለው የብድር ድጋፍ በሰጡት ምላሽ “በሰሊጥ ምርት ዘርፍ ከሚታዩ ችግሮች አንዱ በምርት ደረጃም ሆነ ምርቱን በመሸጥ ወቅት የሚታይ የብድር እጥረት ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም ባንኮችና የብድር አገልግሎትን የሚሰጡ የፋይናንስ ማህበራት ብድርን ለመስጠት ማስያዣ ስለሚጠይቁ ዘርፉ አሁንም የፋይናንስ ችግር አለበት ብለዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ድርጅታቸው የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ አንተነህ ለአራት አመታት ያህል በድርጅታቸው የተተገበረውን ጋራንቲ ፈንድ “Guarantee Fund” የተሰኘውን መርሀ ግብር እንደማሳያነት አቅርበዋል። “ከተለያዩ ባንኮች ጋር በመተባበርና የብድሩን የተወሰነ መጠን በማስያዝ ለህብረት ስራ ማህበራት ላለፉት አራት አመታት ድርጅታችን ስኬታማ የብድር አገልግሎቶች ለሰሊጥ አምራች ማህበራት አመቻችቷል።” ያሉት አቶ አንተነህ ሌሎች በዘርፉም ሆነ በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ግለሰቦችና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ሊማሩበት የሚችል መርሀ ግብር እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የሰሊጥ ምርትና ግብይት መረብ የድጋፍ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሰሊጥ ዘርፍን ለመደገፍ የተመሰረተ መረብ ሲሆን ከመረቡ አጋር ድርጅቶች መካከል የአማራና የትግራይ ክልሎች የግብርናና የገጠር ልማት ቢሮዎች፣ የትግራይ የግብርና ጥናት ማዕከል፣ የአማራ የግብርና ጥናት ማዕከል፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፍያ ኤጀንሲ፣ ቤኔፊትና (Benefit) ጥናቱን ያካሄደው የዋጌኒገን ዩንቨርስቲ ኤንድ ሪሰርች (Wageningen University & Research) የተሰኘው የጥናት ድርጅት እንደሚገኙበት ከመረቡ ድህረገፅ መረዳት ይቻላል። 

አስተያየት