ነሐሴ 25 ፣ 2012

ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ወደአገሩ ያልተመለሰበትን ምክንያት ገለፀ

ወቅታዊ ጉዳዮችዜናዎች

ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ መቆየትን እንደመረጠ የሰጠውን መግለጫ በፌስቡክ ገፁ…

ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ወደአገሩ ያልተመለሰበትን ምክንያት ገለፀ
ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ መቆየትን እንደመረጠ የሰጠውን መግለጫ በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው መልእክት አስተባበለ። በመልዕክቱ ላይ ያሲን እንደገለፀው ከሆነ በኢትዮጵያ መንግስት የጤና ሚንስቴር የወጣው አዲስ መመርያ ወደኬንያ እንዳይመለስ እንዳገደው የገለፀ ሲሆን በአዲሱ መመርያ መሰረት ከፌደራል መንግስት ከቫይረሱ ነፃ እንደሆነ የሚያሳይ የምስክር ወረቀት ለማግኘት ግለሰቦች ለ14 ቀናት በቤት ውስጥ እንዲቆዩ እንደሚጠይቅ ያሲን በመልዕክቱ ላይ አስቀምጧል። በተጨማሪም ጋዜጠኛው ወደ አገሩ ለመመለስ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ገልፆ የምስክር ወረቀቱን ከአፍሪካ ህብረት ለማግኘት በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም ለተከታዮቹ በመልእክቱ ገልጿል። ያሲን በመልዕክቱ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኘውን የኬንያ ኤምባሲ የተቸ ሲሆን “ከየት ሰማችሁት? ካላበድኩኝ በስተቀር በኢትዮጵያ የሚያቆየኝ ምን ምክንያት አለ? ያሳለፍኳቸው ቀናት እኮ ከእስርና በኮሮናቫይረስ ጋር የተጋፈጥኩባቸው ቀናት ናቸው” በማለት ከኤምባሲው የወጣውን መረጃ የተሳሳተ እንደሆነ ጋዜጠኛው ገልጿል። በተጨማሪም ይሲን በመልዕክቱ ላይ አሁንም ለደህንነቱ እንደሚሰጋና በእስርና በህክምና ከደረሰበት ጉዳት ለማገገም እረፍትን በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ ተናግሯል። ነገሮች ከተስተካከሉለት በያዝነው ሳምንት ወደ ኬንያ ለመመለስ ተስፋ እንዳለው የገለፀው ጋዜጠኛው “ነፃነት የሚሰማኝ ወደ አገሬ ተመልሼ የምወደውን ኡጋሊ ሳገኝ ነው። ወይም ቢፍ ፍራይ (Beef Fry)። እሱ ካልተገኘ ደግሞ ቻፓቲም ሊሆን ይችላል። ብቻ እንጀራ አይሁን።” በማለት ወደ አገሩ ለመመለስ ያለውን ጉጉት በመልዕክቱ ላይ አስፍሯል። ባሳለፍነው ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ ቀናት ላይ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተቀሰቀሰው ረብሻ ላይ በማነሳሳትና በቀጥታ ተሳታፊነት ተጠርጥሮ በሰኔ 26 ቀን በቁጥጥር ስር የዋለው ያሲን ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ, ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ከታሰረ ከ55 ቀናት በኋላ ከቫይረሱ ማገገሙን ተከትሎ ከወረዳ 7 የማቆያ ማዕከል መውጣቱ ይታወሳል። ጋዜጠኛው ለመፈታቱ በተለያዩ ማህበራዊ ድህረገፆች ላይ ከተደረገው በኬንያ መንግስት ለኢትዮጵያ መንግስት ከተላኩት ድብዳቤዎችና #FreeYassinJuma ከተሰኘው ዘመቻ በተጨማሪ የተለያዩ በሚዲያ ነፃነትና በሰብአዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ። 

አስተያየት