ግንቦት 30 ፣ 2013

የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የመብራት ክፍያ ሮሮ

City: Adamaመልካም አስተዳደር

የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የመብራት ኃይል አገልግሎት ክፍያ ላይ የሚያሰሙት ሮሮ አሁንም እንደቀጠለ ነው፤ ተቁዋሙ ችግሩን ለመፍታት የአገልግሎት የክፍያ ሂደቱን እያዘመነ እንደሆነ ይጠቅሳል።

የአዳማ ከተማ ነዋሪዎች የመብራት ክፍያ ሮሮ

የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል ከሚነሱበት ቅሬታዎች ውስጥ የክፍያ ጉዳዮችን የሚመለከተው አንዱ ነው፡፡ ተቋሙ የደንበኞቹን የአገልግሎት ክፍያ በሁለት መንገዶች ይሰበስባል፡፡ በካርድ አማካኝነት የሚከወነው የቅድመ ክፍያ አገልግሎት እንዱ ሲሆን፤ ከተጠቀሙ በኋላ በቆጣሪ ንባብ አማካኝነት ክፍያ የሚፈጽሙበት ደግሞ ሁለተኛው መንገድ ነው፡፡ የክፍያ አማራጮቹ የሚወሰኑት ደንበኛው በሚገለገልበት የቆጣሪ ዐይነት ሲሆን ሁሉም ክፍያዎች ተገልጋዮች በአካል በመቅረብ በጥሬ ገንዘብ ልውውጥ የሚያከናውኗቸው ናቸው፡፡ የድህረ-ክፍያ ስርአቱን ወደ ቅድመ ክፍያ በመለወጥ ላይ የሚገኘው ተቋሙ የጥሬ ገንዘብ ክፍያዎች በባንክ የሚፈጸሙበትን መንገድ ዘርግቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል፡፡ በሐገሪቱ ብቸኛ የኤሌትሪክ ኃይል አገልግሎት ሰጪ የሆነው የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ‘የሚቀርቡብኝን ቅሬታዎች ለማሻሻል አሰራሬን እያዘመንኩ ነው’ ይበል እንጂ ተገልጋይ ደንበኞቹ ‘አዳዲሶቹ የድርጅቱ አሰራሮችም የግልጽነት ችግር አለባቸው፣ ተገልጋይን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ ላይም ሁሉም ቅርጫፍ ቢሮዎች ለማለት በሚቻል ሁኔታ እንከን አለባቸው’ ይላሉ፡፡

የአዳማ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መዲና ከድር ከቅሬታ አቅራቢ ደንበኞች መካከል አንዷ ናቸው፡፡ የቅድመ ክፍያ ካርድ ተጠቃሚ የሆኑት ወይዘሮዋ ሰፊ ሰዓት ወስደው ከረዥም የጥበቃ ሰልፍ በኋላ የሚሞሉት ካርድ ላይ የፈጸሙት ክፍያ ቆጣሪያቸው ከሚያነበው የገንዘብ መጠን ጋር ባለመመጣጠኑ መቸገራቸውን ነግረውናል፡፡ “ላለፈው ተከታታይ አንድ ዓመት ካርድ ሞልቼ ወደ ቤቴ ስለመለስ ገንዘቡ ይጎድላል፡፡ የሚጎድለው የገንዘብ መጠንም ተመሳሳይ አይደለም፡፡ ለምሳሌ የ100 ብር ካርድ ሞልቼ ቆጣሪው ላይ ሰባም ሰማኒያም ሊያሳየኝ ይችላል” ብለውናል፡፡ የገጠማቸውን ችግር ለአገልግሎት ሰጪ ድርጅቱ በተደጋጋሚ ቢናገሩም አጥጋቢ መልስ አለማግኘታቸውን የሚናገሩት አስተያየት ሰጪአችን ሁኔታው እየተበባሰ መምጣቱን እና ችግሩ ካርዱን የሚሞሉት ባለሙያዎች ነው ብለው እንደሚያምኑ አስረድተዋል፡፡ በአንድ ወቅት በአካል ቀርበው የቅርንጫፍ ቢሮ ሠራተኞችን ስለጉዳዩ በጠየቁበት ጊዜ “ሳይከፈል የቆየ ውዝፍ በመኖሩ” መሆኑ ቢነገራቸውም ካርድ ሳይሞሉ ኃይል ያገኙበትን ጊዜ ባለማስታወሳቸው ግራ እንደተጋቡ ከአዲስ ዘይቤ አዳማ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

“አሁን አሁንማ ወር ሲደርስ ሐሳብ ይይዘኝ ጀምሯል” በማለት ሐሳባቸውን የጀመሩት አቶ ዘለቀ መኮንን የአዳማ ከተማ ነዋሪ ናቸው “የቢል ተጠቃሚ ነኝ፡፡ ከባድ የኤሌትሪክ ኃይል የሚያስፈልጋቸው ቁሳቁሶች የሉኝም፡፡ ካውያ፣ ልብስ ማጠቢያ ሌሎችም ኃይል የሚፈልጉ ነገሮች አልጠቀምም፡፡ በየወሩ ቢል ላይ የሚመጣብኝ ክፍያ ግን እነዚያን እቃዎች ከሚጠቀሙት ሰዎች በላይ ነው፡፡ በየወሩ በሺህ የሚቆጠር ብር ነው የምንከፍለው፡፡ አንድ ሺህ እና ሁለት ሺህ ብሮችን ለምደናቸዋል፡፡ ከዚያ ከፍ ሲል ነው እየደነገጥን ያለነው” ሲሉ ምሬታቸውን ነግረውናል፡፡ አቶ ዘለቀ ኃይል ይፈልጋሉ ብለው የዘረዘሯቸውን ቁሳቁሶች ለመጠቀም በመኖርያ አካባቢያቸው ያለው ኃይል እንደማይፈቅድ፣ የሚመለከታቸው ቢሮዎች ሄደው ሲያመለክቱ ይስተካከላል የሚል ተደጋጋሚ መልስ እንደሚያገኙ የነገሩን ሲሆን፤ ወር ላይ የሚከፍሉትን ከፍተኛ ክፍያ በማሰብ በጣም ካልመሸ አምፖል እንኳን እንደማያበሩ ይገልጻሉ። አቶ ዘለቀ በመደምደሚያቸው “በጣም ከፍ ያለ ክፍያ በምንጠየቅበት ጊዜ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ሄደን አቤት እንላለን፡፡ እንባችንን ያዩ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች የቆጣሪ ንባቡ በግምት ስለሚሰራ ነው ባሁኑ ከፍ ካለ በሚቀጥለው ይስተካከላል ብለው ያጽናኑናል፡፡ እንደሚሉትም ለአንድ ለሁለት ወር ጥሩ ይሆንና ወደነበረበት ይመለሳል” ይላሉ፡፡

የአዳማ ዲስትሪክት ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ-አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ዮሃንስ የተቋሙ ደንበኞች እያነሱ የሚገኙትን ቅሬታ አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በስልክ መስመር በነበራቸው ቆይታ “ቅሬታው ተገቢነት ያለው ነው” ያሉ ሲሆን የኤሌትሪክ ተጠቃሚ ደንበኞች ማወቅ ይገባቸዋል ያሏቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ዘርዝረዋል፡፡ “የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ካለፈው ታህሳስ 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ 4 ዓመታት ጭማሪ ተደርጎበታል፡፡ ህዝቡ በፊት የለመደውን ታሪፍ መጠበቅ የለበትም አንደኛው ችግር ይሔ ነው፡፡ የቅድመ ክፍያ ካርድን በተመለከተ ደግሞ ደንበኛው ወይም ተገልጋዩ ከሚሞላው ካርድ ላይ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚቆረጥ መታወቅ አለበት፡፡ ተቀናሽ የሚደረገው ገንዘብ ዴስክ ላይ ላሉ ሠራተኞች ወይም ለተቋሙ የሚውል ሳይሆን ለመግንሥት ገቢ የሚደረግ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ሲስተሙ ምንም የሚቀንሰው ገንዘብ የለም፡፡ አልፎ አልፎ ሲስተሙ መቀነስ የሚገባውን ክፍያ ላይቀንሰው ይችላል፡፡ ይህ ግን ሁልጊዜ አይሆንም፡፡ በዚህኛው ወር ካልቆረጠው በቀጣዩ ጊዜ የሁለቱንም ደርቦ ይቆርጣል፡፡ ከሁለትም ሦስትም ጊዜ በላይ አቆይቶ ውዝፉን ይቀንሳል፡፡ ይህ በሚያጋጥምበት ጊዜ ተገልጋዩ ላይ ግርታ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህም ቢሆን አልፎ አልፎ የሚከሰት እንጂ የዘወትር ገጠመኝ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ገጠመኞች ሲኖሩ አሰራሩን በማስረዳት ተገልጋዩን እንሸኛለን፡፡” ብለዋል፡፡

በአሰራር ሂደቱ ምክንያት ከሚፈጠረው በተጨማሪ ጥቂት የማይባሉ ገንዘብ ተቀባዮች ከተከፈላቸው ገንዘብ ቀንሰው ካርዱ ላይ በመሙላት ለግል ጥቅማቸው ያውላሉ መባሉን አስመልክቶ ከአዲስ ዘይቤ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሥራአስኪያጁ ሲመልሱ

“አልፎ አልፎ ጥቂት ሠራተኞች ላይ የሥነ-ምግባር ጥሰት ሊታይ ይችላል፡፡ ተቋሙ የአሰራር ስርአቱን በማሻሻል የስርቆት እና የማጭበርበር ተግባራትን በማጋለጥ የሚታመን ተቋም ለመገንባት እየተሰራ ነው፡፡ በደረሰው ጥቆማ መሰረትም የማጣራት ሥራ እየሰራ ነው” ብለዋል።

የአዳማ ቁጥር ሦስት ቅርንጫፍ ኃላፊ አቶ ስላሺ በቀለ በበኩላቸው በቅርንጫፋቸው ከዚህ ቀደም ለክፍያ አላስፈላጊ ሰልፎች መኖራቸውን በዚህም ተገልጋዮች ለአላስፈላጊ ወጪና ብክነት መዳረጋቸውን አንስተዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍም ክፍያዎች በሞባይል ባንኪንግ እንዲፈጸም የሚያስችል አሰራር ዘርግተናል ብለዋል። በሠራተኞች ስነ-ምግባር ላይ ያለውን ክፍተት ለመሙላትም ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሆነ ገልጸዋል። 

አስተያየት