ጠላ በኢትዮጵያ ባህል ከግለሰቦች መኖሪያ ጀምሮ እስከ ነገስታት ጓዳ ድረስ የተለመደ ተጠቃሽ ባህላዊ መጠጥ ነው። ነገር ግን ምናልባትም በአዲሱ ትውልድ ተዘንግቷል ሊባል በሚችል ደረጃ ሲዘወትር አይታይም።
“በርካታ ኢትዮጵያውያን ኑሮን ለማሻሻል ወደ ከተማ ሲፈልሱ ባህላቸውን ለከተሜው ማስተዋወቅ እየቀረ ነው። ይልቁንስ ባህላቸውን አሳንሶ መመልከትና በዘመናዊ አኗኗር ስርዓት ውስጥ መደላደል ይስተዋላል” ይላሉ በአዲስ አበባ ላይ የጠላ መጠጥን ትንሳኤ ለመፍጠር ከሚተጉትና የሴሎ ጠላ መስራችና ባለቤት የሆኑት ዮሐንስ አይቸው።
አቶ ዮሐንስ እንደሚሉት የጠላ ባህል እየጠፋ መሄድ ለሴሎ ጠላ ቤት መቋቋም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀስ ነው። “የጠላ መዘዉተር ባህል ለመቀዛቀዙ ምክንያት የሆነው ደግሞ እንደ ርካሽ መጠጥ መቆጠሩ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ቢዝነስ ስጋት አለው፤ ያንን ስጋት ተጋፍጠህ ነው የምትጀምረው። ሴሎም በዛው መልክ ነው የተጀመረው” ይላሉ አቶ ዮሐንስ።
በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ልክ እንደ ሴሎ ጠላ፣ ዘመራ ጠላ በከተማዋ አምስት ቅርንጫፎችን ከፍቶ የባህላዊ መጠጥ ባህሉን እያለማመደ ይገኛል። ዘመራ ጠላ ከተጀመረ ሰባት ዓመት ሆኖታል፤ የተጀመረበት ምክንያት ደግሞ፣ “እናቶችን በማደራጀት የስራ ማስጀመሪያና ማስኬጃ ገንዘብ በመስጠት ገቢ የሚፈጥሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነበር” ሲሉ የዘመራ መስራቾች ይናገራሉ።
ባህላዊ መጠጦችን በከተማ በማስተዋወቅ ረገድ እንደ 'ጎጃም ጠላ' እና 'ሽፍታ ጠላ' የመሳሰሉ በአዲስ አበባ በሰፊው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
ቦሌ መድኀኒያለም አካባቢ በሚገኘው ሴሎ ጠላ ቤት ባህላዊ መጠጦች ባልተለመደ ሁኔታ ተሰናድተዋል። በተለምዶ ቁመታቸው ዝቅ ባሉ መደቦች ላይ የሚዘወተረው ጠላ፤ አሁን ለዘመናዊ መጠጦች የተዘጋጀ በሚመስሉ መቀመጫዎች፣ አዳራሽና እና መስተንግዶ ለተጠቃሚዎች ቀርቧል። ደንበኞቹም ጠላን በዚህ ሁኔታ ማግኘት መቻላቸው እንደሚያስገርማቸው አስተያየት ይሰጧቸዋል።
ሴሎ ጠላ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረ አንደኛ ዓመቱን በቅርቡ ይዟል። “ሴሎ ጠላ መጠጫ ሳይሆን ማምረቻ የመሆን እቅድ ነው ያለው” ይላሉ አቶ ዮሐንስ።
“ድርጅታችን፣ ጠላን በእጅ እንዳለ ወርቅ ነው የሚቆጥረው” የሚሉት መስራቹ፣ “ጠላን በከተማ የጀመርነው እኛ ባንሆንም እንደልብ ያለመገኘቱ ጉዳይ፣ ለገበያ ፍላጎት የሚዘጋጀው ጠላ ጥራቱንና ባህላዊ ሂደቱን የማይጠብቅበት እድል መኖሩ ሴሎ ጠላን ለመክፈት ሌላኛው ሰበብ ሆኗል” ሲሉ ለአዲስ ዘይቤ ተናግረዋል።
እንደ ዘመራ ጠላ መስራቾች አስተያየት፣ “ጠላ ባህላዊ መጠጥ እንደመሆኑ የአዘገጃጀት ሂደቱን መቀየር አይቻልም። አሁንም ድሮ እናቶች የሚያልፉበትን የአሰራር ሂደት ተከትሎ የሚዘጋጅ በመሆኑ እንደቀድሞው በእንጨት ማገዶና ተመሳሳይ መንገዶች በመጠቀም የሚሰራ መሆኑ አድካሚና የጉልበት ስራ የሚበዛበት ያደርገዋል።”
ዘመራ ጠላ፤ በደብረማርቆስ ከተማ የሚገኙ እናቶች የሚያዘጋጁትን ድፍድፍ ጠላ ተረክቦ አዲስ አበባ በማስመጣት ይዛጋጃል።
“በደብረማርቆስ ከተማ የሚገኙት ባለሙያ እናቶች ጉልበት ያላቸው በራሳቸው ጋን ሰርተው ለዘመራ እንዲያስረክቡ፣ እንዲሁም ጉልበት የሌላቸው ደግሞ ሰራተኛ ተቀጥሮላቸው ጥራቱን እና ባህላዊ ሂደቱን ጠብቆ እንዲሰራ ነው የምናደርገው” ይላሉ መስራቾቹ።
የጥራት ጉዳይን በተመለከተ አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው እንደሚሉት፣ “ለገበያ የሚሰሩ ነገሮችን ተመልክተናል፣ እንደ እንጀራና ሌሎችም የምግብ ዓይነቶች ላይ ባእድ ነገር መቀላቀል በየጊዜው የምንሰማው ነገር ሆኗል፤ ጠላ ደግሞ ልበርዘው ልከልሰው ከተባለ በጣም ቀላል ነገር በመሆኑ በማጭበርበር ገንዘብ ለመሰብሰብ ምቹ ነው።”
የጠላ ዝግጅት ባህላዊ ሂደቱን እንዲጠብቅ ማድረጉ ፈተና እንዳለው የዘመራ እና ሴሎ ጠላ ቤቶች የጋራ ሀሳብ ነው። በሴሎ ጠላ የአዘገጃጀት ሂደት የምርት ይዘቱን እና ጥራቱን የምትከታተል ባለሙያ እንዲሁም ሌሎች የማዘጋጀት ሂደቱን የሚያከናውኑ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን በተቆጣጣሪዋ ልኬትና ትዕዛዝ መሰረት ብቻ ጠላው ይዘጋጃል።
እንደ ሴሎ መስራች ገለጻ የሴሎ ጠላ ጣዕም ሁልጊዜም አንድ ዓይነት እንዲሆን ግብዓቶቹ በሙሉ በልኬት ይዘጋጃሉ። ጠላውም ለደንበኞች እየተሸጠ የሚገኘው በዉሃ መያዣ ፕላስቲክ (ኮዳ) እንዲሁም አብረዋቸው በሚሰሩ ሆቴሎች ደግሞ በኩባያ ይቀርባል።
“ደንበኞች ንጹህ ነገር የሚፈልጉ በመሆኑ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ጥሩ ተቀባይነትና የሚያበረታታ ምላሽ አግኝተናል። ይሁን እንጂ የተወሰኑ ደንበኞች አስተያየታቸውን የሰጡን ቢሆንም በመደበኛ ቀናት ከ50 እስከ 60 ሊትር ሴሎ ጠላ በየዕለቱ ይሸጣል። በበዐላት ቀን ደግሞ እስከ 150 ሊትር ጠላ መሸጥ ችለናል” በማለት የሴሎ ጠላ ባለቤት ያስረዳሉ።
ሴሎ ጠላ በአንድ ሊትር 135 ብር፣ በጠላ ኩባያ ደግሞ (በግምት 0.4 ሊትር) 55 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ዋጋው ተወዷል በሚለው እንደማይስማሙ የሚናገሩት ዮሐንስ፣ “ዋጋው ተወዷል የሚለው አስተያየት ብዙ ጊዜ ለሀገር ውስጥ ምርትና ለባህላችን በምንሰጠው ዝቅተኛ ግምት የሚመነጭ ይመስለኛል። ነገር ግን በሴሎ እምነት ዋጋው መወደድ አለበት፤ ለራሳችን ክብር ብንሰጥ እኮ ለባህላችን ነው ከፍተኛ ዋጋ ማውጣት ነው ያለብን” ይላሉ።
ማህበረሰቡ በሚሰጠው የተሳሳተ ግምት የተነሳ የጠላ ዝግጅት እንደ ስራ እድልም ሆነ የገቢ ምንጭ መሆኑ እየቀነሰ በመሆኑ በርካታ እናቶች አሁንም ለፍተው የሚያዘጋጁት ጠላ ይባክናል።
አቶ ዮሐንስ ይህን ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ፣ “ጠላ የሚያዘጋጁት እናቶች ከፍ ያለ ዋጋ ቢጠሩ የሚጠቀም ባለመኖሩ ከጥራቱ ይልቅ ለገቢያቸው እንዲያስቡ ይገደዳሉ፤ ይህም በመሆኑ ተጠቃሚዎች 'ጠላው ቀጠነ' የሚል ቅሬታ ማቅረባቸው አይቀሬ ይሆናል።”
ጌሾ፣ ብቅል፣ የጠላ ቂጣ እንዲሁም ሌሎችም ግብዓቶቹ በራሳቸው በሴሎ ሰራተኞች የሚዘጋጁ ናቸው የሚሉት የሴሎ መስራች ግብዓቶቹን የሚያቀርቡ በርካታ ነጋዴዎች ቢኖሩም በራሳቸው እንዲዘጋጅ የተደረገበት ምክንያት ለትርፍ ሲባል የሚቀላቀሉ ባእድ ነገሮችን ለማስቀረት መሆኑንም ይገልጻሉ።
የዳጉሳ ጠላ፣ የገብስ ጠላ፣ የስንዴ ጠላ፣ የጤፍ ጠላ እንዲሁም የዘንጋዳ ጠላ ሴሎ ጠላ ከሚያቀርባቸው ዓይነቶች መካከል ናቸው። አቶ ዮሐንስ እንደሚያስረዱት፣ ለጥራት ለሚሰጡት ትኩረት ማሳያ ከሚችሉ ነገሮች ጠላዉን ለማዘጋጀት እንኳን የታሸጉ ዉሃዎችን መጠቀማቸው አንዱ ነው።
ሴሎ ጠላ፣ ጠላ ብቻ ከሚያስተናግድባቸው የራሱ ቤቶች በተጨማሪ የመሸጫ ቅርንጫፎቹን በሆቴሎች በማድረግ ከሌሎች መስተንግዶዎች ጎን ለጎን እንዲቀርብ ለማድረግ በማለም የመጀመሪያ ሙከራዉን ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው ውጥማ ሆቴል ጀምሯል። ባህላዊ መጠጥ እንቅፋት ሳይፈጥርበት የተጠቃሚዎች ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ በመምጣቱ በዚሞል (ZMALL App) መተግበሪያ የኦንላይን ግብይት ዘዴም ሴሎ ምርቶቹን መሸጥ ጀምሯል።
ዘመራ ጠላ ጠማቂ ባለሙያዎቹ የሚጠቀሙበት ባህላዊ ሂደት ተገቢዉን ዋጋ እንዲያገኝ ማድረግን ያለመ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የጠላ ፌስቲቫል የማዘጋጀት እቅድ እንዳላቸው መስራቾቹ ለአዲስ ዘይቤ ገልጸዋል። በተጨማሪም ለባህሉ እስካሁን መቆየት አስተዋፅዖ ያደረጉ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት በማዘጋጀት ላይ ይገኛል።
የጠላ ዝግጅት ስራ ሰፊ ቦታ የሚፈልግ በመሆኑ ያለን አነስተኛ ቦታ በስራችን ላይም ውስንነት ፈጥሮብናል የሚሉት የሴሎ ጠላ መስራች፣ “የሴሎ ጠላ ትልቁ እቅድ የጠላ ፋብሪካ በመሆን ተደራሽነቱን ማስፋት እና ባህሉ እንዲጠበቅ የራሱን ድርሻ መወጣት ነው” ብለዋል።
ዮሐንስ አይቸው ሲያጠቃልሉ፣ “በእኔ እይታ የጠላ ምርት ለሀገርም የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፤ ለምርቱ ወጪ የሚደረገው ገንዘብ የት የት እንደሚደርስና ማን ተጠቃሚ እንደሚሆንበት በግልፅ የሚታይ ነው። ከእኛ ግብዓቶች ለመግዛት የሚወጣው ገንዘብ በቀጥታ ገበሬው ጋር ይደርሳል፤ ምርቱን ወደ አዲስ አበባ ለማምጣት የመጓጓዣ ወጪ ይኖራል፤ እዚህ ደግሞ በምርት ሂደቱ የሚሳተፉት ሰራተኞች በስራቸው ክፍያ ያገኛሉ። ይህም ማለት በሀገር ውስጥ ምርት እና ባለሙያ የሚዘጋጀው ጠላ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሀገሪቱንና ዜጎችን ይሆናል፤ ከእዚህ ባለፈ ከተሳካ እና ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ከተጀመረ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ብለን እናስባለን” በማለት ያላቸውን ሰፊ ህልምና እቅድ ይናገራሉ።