የአዳማ ከተማ የማስተር ኘላን ማሻሻያ በ2008 ዓ.ም. ሲካሄድ ከተማዋ 31 ኪ.ሜ. ስኩዌር (31ሺ ሔክታር) ስፋት እንዳላት ተቀምጧል። ከአዳማ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የተገኘ መረጃ ደግሞ ከከተማዋ አንድ ጫፍ ወደ ሌላኛው ጫፍ ያለው ርቀት 10 ኪ.ሜ. እንደሆነ ያሳያል። የተለያዩ ጥናቶች ወደላይ ከማደግ ይልቅ ወደጎን እየተለጠጠች እንደሆነ የሚናገሩላት አዳማ የትራንስፖርት አማራጯ የስፋቷን ያህል እንዳልሆነ ነዋሪዎቿ ይናገራሉ። በአሁን ሰዓት የፈረስ ጋሪ፣ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ)፣ ሞተር ሳይክል፣ ሳይክል፣ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ (ሚኒባስ) እና የከተማ አውቶቡስ አዳማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። በመንግሥት በኩል የከተማዋን ነዋሪዎች እንዲያገለግሉ 10 መለስተኛ የህዝብ ማመላለሻ የከተማ አውቶብሶች የተመደቡ ሲሆን ከ12 ሺህ በላይ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ)፣ አንድ ሺህ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ የፈረስ ጋሪዎችን ጨምሮ የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በስልክ መተግበሪያ እና በስልክ ጥሪ አገልግሎት የሚሰጡ ሜትር ታክሲዎች በዘርፉ ተሰማርተው ተንቀሳቅሰዋል። አዲስ አበባ ውስጥ ሥራ የጀመረው “ታክሲዬ” አገልግሎቱን ሲያሰፋ ቅድሚያ ከሰጣቸው የኢትዮጵያ ከተሞች መካከል አዳማ አንዷ ነበረች። በአሁን ሰዓት “ታክሲዬ” በአዳማ እየሰራ ይገኛል። በተጨማሪ “የሮን” ከ2013 ዓ.ም. መስከረም ወር ጀምሮ የዘመነውን የታክሲ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ተቋማት ናቸው። በቅርቡ ሥራ የጀመረው “ሄይ ራይድ”ም አዳማን ማዕከል አድርገው ከሚንቀሳቀሱ የሜትር ታክሲ አግልግሎት ሰጪዎች መካከል አንዱ ነው። “ስማርት”፣ “ጋሪ” የተሰኙ ተቋማትም ለጥቂት ጊዜ ገበያውን ተቀላቅለው ሥራ ያቋረጡ ናቸው።
መቅደስ ሙላቱ የአደማ ኗሪ ናት። ራይድ አገልግሎት ሰጪ መተግበሪያ አልያም አጭር ስልኮች ተጠቅማ እንደማታውቅ አንስታ “የራይድ አገልግሎት እንሰጣለን” በሚሉ የቤት መኪናዎች ከጓደኞቿ ባገኘችው ተንቀሳቃሽ ስልክ ደውላ እየጠራች እንደምትጠቀም ነግራናለች።
“አብዛኛውን ጊዜ የምገለገለው ከምሽት 4 ሰዓት በኋላ ነው” የምትለው መቅደስ ታሪፉ የግምት ዋጋ እንደሆነ ትናገራለች። "እንደማንኛውም ኮንትራት ነው። ቦታውን ቀድመህ ተናግረህ ዋጋ ይነግሩህና ነው የሚወስዱህ" ብላለች። ዋጋውን በተመለከተም ከተማ መሀል ለሚደረግ ጉዞ ከ100 እስከ 200 ብር እና ከመሀል ከተማ ከራቀ እስከ 400 ብር ድረስ እንደሚያስከፍሉ ነግራናለች። “ልዩነቱ ተሽከርካሪዎቹ የቤት መኪና መሆናቸውና የራይድ አገልግሎት እንደሚሰጡ መለጠፋቸው ነው” ትላለች።
ሌላዋ የገጠማትን የነገረችን ሀሴት ዓለማየሁ የማስታወቂያ ባለሙያ ነች። ከ2 ጓደኞቿ ጋር ከምሽት መዝናኛ ስትወጣ ባገኘቸው የራይድ አገልግሎት ሰጪ የቤት መኪና በአፕሊኬሽኑ የተጠቀመ መስሎ እንዳታለላትና የተጋነነ ብር እንዳስከፈላት አስታውሳለች። “ለሦስት ኪ.ሜ. ጉዞ 6መቶ ብር ከፍያለሁ። ዋጋው የተጋነነ ነው። በዚህ ምክንያት ከዚያች ቀን በኋላ ተጠቅሜ አላውቅም። የኮንትራት አገልግሎት ሲያስፈልገኝ የባጃጅ ደንበኞቼ ጋር እደውላለሁ” ብላለች።
እንዲህ ዓይነት መጭበርበሮች መኖራቸው፣ ሰዎች ስለ አገልግሎቱ ያላቸው ግንዛቤ ማነሱ፣ የከተማዋ መጥበብ የከተማዋ ነዋሪዎች ለሜትር ታክሲ ጥሩ አመለካከት እንዳይኖራቸው ማድረጉን እና ጥቂት የማይባሉ ተቋማት በኪሳራ ከገበያው እንዲወጡ ማስገደዱን ያምናሉ። በተጨማሪም የ’ባጃጅ’ አገልግሎት በጣም የተለመደ መሆን፣ እንደልብ መገኘትና የዋጋው ተመጣጣኝነት ነዋሪው የሜትር ታክሲዎችን ለመጠቀም እንዳላበረታታው ባለሙያዎች ይገምታሉ።
በአሁን ወቅት በስራ ላይ ከሚገኙት የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች መካከል በየሮን ትራንስፖርት ሰርቪስ የሚተዳደረው “የሮን ራይድ” አንዱ ነው። በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ከ10 የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ 50 መምህራን አማካኝነት እንደተቋቋመ ሥራ አስኪያጁ ዶ/ር ከይረዲን ተማም ይናገራሉ። “በተገልጋይ ዘንድ ሥራውን ያለመቀበል ችግር አለ” የሚሉት ዶ/ር ከይረዲን አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በንቃት አለመከታተላቸው ሌላው በስራቸው ላይ ያጋጠመ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል። ዶ/ር ከይረዲን እንደሚሉት ተገልጋዮች ብዙውን ጊዜ መተግበሪያ ባለመጠቀማቸው እና ትዕዛዝ ባለመኖሩ አሽከርካሪዎች መተግበሪያውን ከፍቶ መጠበቅ እንደሚያሰለቻቸው አስረድተዋል።
ድርጅታቸው በራሱ 5 ተሽርካሪዎች እንዲሁም አባላቱ ባስመዘገቧቸውና በኮሚሽን አብረዋቸው በሚሰሩ እስከ 50 በሚደርሱ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። “አብረውን የሚሰሩ የተሽከርካሪ ባለንብረቶችን ለማበረታታት እና ገበያውን ለማስለመድ ተሽከርካሪውን እና ተጠቃሚውን በማገናኘታችን የምናገኘውን የ10% ኮሚሽን ትተን በነጻ የምንሰራበት ጊዜም አለ” የሚሉት ስራ አስኪያጁ ዶ/ር ከይረዲን ተማም ናቸው።
የተሽከርካሪ አቅርቦታቸውን ለመጨመር መንግሥት ከቀረጥ ነጻ ወደ ሐገር ውስጥ የሚገቡና በሙሉ በሐገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎችን እንደፈቀደላቸው አንስተው አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት “ሙሉ ለሙሉ የሚለው በከፊል ሀገር ውስጥ በሚገጣጠሙ ተሽርካሪዎች እንዲቀየርልን ጥያቄ አቅርበን በሂደት ላይ ነን” ብለዋል።
የሜትር ታክሲ አገልግሎቱን ከቱሪዝም ዘርፉ ጋር በጋራ በመስራት ላይ ከሚገኘው “የሮን” ሥራ አስኪያጅ ለመረዳት እንደሚቻለው በሌሎች የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ባልተለመደ መልኩ የመንፈሳዊ ጉዞ፣ የሀገርህን እወቅ እና የጉብኝት ‘ፓኬጆች’ በማዘጋጀት የገበያውን ክፍተት ለመሙላት እየጣሩ ይገኛሉ።
በተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴሌቭዥን ተቋማት እና የቢራ አምራቾች ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ በኃላፊነት እንደሰራ የሚናገረው አቶ ቃልኪዳን ሰለሞን የገበያ ጥናት እና የ’ፕሮሞሽን’ ችግር በራይድ አገልግሎት ሰጪዎች በኩል መታዘቡን ይናገራል። በትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና በተገልጋዮች ዘንድ የነበረውን አለመተማመን የሚቀርፈው፣ ምቾት ያለው ዘመናዊ አገልግሎት የሚሰጠው ሜትር ታክሲ በአዳማ ከተማ መጀመሩ አስደሳች መሆኑን አንስቶ የከተማዋን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ እንደ ‘ባጃጅ’ ያሉ ተሽከርካሪዎች ገበያውን መቀላቀል እንዳለባቸው ይመክራል።
“ሌላው ድርጅቶቹ በገበያው መገኘታቸውን፣ የአገልግሎታቸውን ዐይነት፣ የዋጋ አማራጮቻቸውን እና መሰል ጉዳዮች በተገቢው ሁኔታ አለማስተዋወቃቸው መኖራቸው ራሱ እንዳይታወቅ አድርጓቸዋል። እነኚህን በማስተካከል የተሻለ ጥቅም እና አገልግሎት ሊያገኙ ይችላሉ” በማለት ሀሳቡን ይቋጫል።
መሀመድ አደም በታክሲ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ወጣት ነው። "የራይድ አገልግሎት አዳማ ውስጥ አያዋጣም" የሚል እምነት አለው።
“ሁሉም ከተሞች ለሜትር ታክሲ አገልግሎት ምቹ ናቸው ማለት አይደለም። የከተሞቹ ነባራዊ ሁኔታ ይወስነዋል። አዲስ አበባ ላይ ስላዋጣ አዳማም ያዋጣል ማለት የዋህነት ነው” ብሏል። የሚያሽከረክራትን አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ (ዶልፊን) አገልግሎቱን በስልክ ጥሪ እና በሞባይል መተግበሪያ በሚያቀርብ ድርጅት ውስጥ አስመዝግቦ አብሮ የመስራት ፍላጎት ያላደረበት በዚህ ምክንያት መሆኑንም አጫውቶናል።
"ገበያውን የተቀላቀልነው በቂ ጥናት እና የቴክኒክ ዝግጅት አድርገን ነው” የሚሉት የ”ሄይ ራይድ” ስራ አስኪያጅ አቶ ሁሴን አሊ በሌሎች ተመሳሳይ አግልግሎት በሚሰጡ ድርጅቶች ባልተለመደ መልኩ በባለ ሦሰት እግር ተሽከርካሪዎችን እና እስከ 11 ሰው የሚጭኑ ሚኒባሶችን ወደገበያው ቀላቅለዋል። በሰዓት የተከፋፈለ ሦስት ዓይነት ታሪፍ እንዳላቸውም ነግረውናል። እስከ ምሽት 2 ሰዓት ያለው መደበኛ የመጓጓዣ ታሪፍ ሲኖረው ከምሽት 2 ሰዓት እስከ 4 ሰዓት ያለው ከመደበኛው ከፍ ባለ ታሪፍ ይስተናገዳል። ከምሽት 4 ሰዓት በኋላ ለሚመጣ ተስተናጋጅም የሰዓቱን መግፋት ያገናዘበ ታሪፍ ተዘጋጅቷል። ድርጅቱ ከተጠቃሚው ክፍያ ላይ 13 በመቶ ኮሚሽን ለአገልግሎቱ ያስባል።
የአዳማ ከተማ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ታዬ ተሊላ "የማስ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት እየተደራጁ ያሉ ሦስት ማኅበራትን ሥራ ለማስጀመር እየሰራን ነው" ብለዋል።