ሰለሞን ሰማዬ እና ልእልት ይልቃል በአዲስ አበባ የግል ድርጅት ተቀጣሪዎች ናቸው። ለአዲስ ዘይቤ እንደሚገልፁት ሰለሞን ተቀጥሮ ስራ ከጀመረ 2 ዓመቱ ሲሆን 6 ሺህ 800 ብር እንዲሁም ልእልት ደግሞ በ3 ዓመታት የስራ ልምድ 7 ሺህ 200 ብር የተጣራ ወርሃዊ ደሞዝ ይከፈላቸዋል።
“አዲስ አበባ ላይ የራሴ ቤት ይኖረኛል ብዬ ማሰብ ራሱ ይከብደኛል። በየቦታው ደላላዎች የሚጠሩትን እና ሰዎች የሚከራዩበትን ገንዘብ ስትሰማ የማይታሰብ ነው። እኔ አሁን የማገኘው ደሞዝ ምንም ሳይቆራረጥ ቤት ለመከራየት ራሱ የሚበቃ አይደለም” ይላል ሰለሞን።
ልእልት ይልቃልም በሰለሞን ሀሳብ የምትስማማ ሲሆን “እኔ ብቻ ሳልሆን አሁን ያለው ወጣት ትውልድ ከወላጆቹ ቤት የሚወጣ አይመስለኝም፤ ስራ ለማግኘት ተለፍቶ ከዛም የተሻለ ደሞዝ ላይ ለመድረስ ተደኮሞ እንዴት ይሆናል? የኑሮ ውድነት መጨመር እንጂ መቀነስ አያውቅም እና እንዴት ሆኖ መኖሪያ ቤት ይገኛል?” ስትል ትጠይቃለች። ወጣት ልእልት አክላም “በደህና ጊዜ ቤት ባገኙት ወላጆቻችን ተጠልለን ካልኖርን አሁን የሚሰማው የቤት መከራያና መሸጫ ዋጋ ያስፈራል” ብላለች።
በመዲናዋ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የከተማዋን ነዋሪ በእጀጉ እየፈተነ ይገኛል። ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍሎች ወደ ከተማዋ የሚፈልሰዉ የሰዉ ቁጥር እየጨመረ መምጣትና የቤት ዋጋ በየጊዜው እየናረ በመሄዱ በመንግስት በኩል ችግሩን ያቃልላሉ ተብሎ የተሞከሩ ጥረቶች የሚጠበቀዉን ያህል ለዉጥ ሲያመጡ አይስተዋልም።
የአዲስ አበባን የቤት ችግርን ለመፍታት ከ1996 ጀምሮ በተለያየ መዋቅር ሲቋቋም አሁን ያለው የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ላይ ደርሷል። ባለፉት 18 ዓመታት 400 ሺህ የማይሞሉ መኖሪያ ቤቶች ናቸው በመንግስት መገንባት የቻሉት። አሁን ደግሞ ለነዋሪዎች ያልተላለፉ ከ139 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች በግንባታ ሂደት ላይ እንደሚገኙ ከአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመልክታል።
የከተማ ፕላን እና የኪነ-ህንፃ ባለሙያና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዮሐንስ መኮንን የአዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ችግር ከአድዋ ጦርነት ጊዜ ጀምሮ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን ይገልፃሉ። የከተማ ፕላንና ኪነ-ህንፃ ባለሙያው እንደሚገልፁት “በአድዋ ጦርነት ወቅት የክተት ጥሪውን ከአዲስ አበባና ዙሪያዋ ተቀብለው የዘመቱ ነዋሪዎች በቁጥር 30 ሺህ ይሆናሉ፤ ከዘመቻው በኋላ ወደ ከተማዋና ዙሪያው የተመለሱት ሰዎች ከሄዱት በ4 እጥፍ ጨምሮ 120 ሺህ ይሆናሉ። እነዚህም በአዲስ አበባና ዙሪያ ሰፍረው ቀርተዋል”
በደርግ እና በኢህአዴግ ዘመንም የአዲስ አበባ መስፋፋትና መልማትን ተከትሎ የፍልሰት ቁጥሩ እየጨመረ መቀጠሉን ባለሙያው ይገልፃሉ። “ሀገር አቀፍ ዓመታዊ አማካይ የህዝብ እድገት ከ2.1 እስከ 2.5 ነው። የአዲስ አበባን ለብቻው ከተመለከትን ደግሞ በዓመት እስከ 5 በመቶ የህዝብ ቁጥር እድገት ይታያል፤ ነገር ግን በከተማዋ የአዲስ ውልደት ምጣኔ 1.7 በመቶ የሚሆን ሲሆን የተቀረው ከ3 በመቶ በላይ በፍልሰት የሚመጣ ነው ማለት ነው” ሲሉ ዮሐንስ መኮንን ይገልፃሉ።
አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደሚሉት አዲስ አበባ ውስጥ አንድ በዲግሪ የተመረቀ ግለሰብ ቤት የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው። “ከተማ ላይ ባለአንድ ክፍል መኖሪያ ቤት (በተለምዶ ስቱዲዮ) የሚባሉት ከ8 እስከ 10 ሺህ ብር ነው የሚከራዩት። በተዐምር ካልሆነ የማይታሰብ ነው በተለይ የመንግስት ሰራተኛ የ10 ሺህ ብር ደሞዝተኛ ራሱ ለመሆን እስከ 10 ዓመት መስራት ያስፈልገዋል” ይላሉ ባለሙያው።
በሌላ በኩል መንግስት የመኖሪያ ቤቶችን ፍላጎት ጋብ ያደርጋሉ ያላቸውን እንደ 10/90፣ 20/80 እና 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክቶችን እየሰራ ቢሆንም፤ በተለይ በእዚህ ወቅት ተግዳሮቶች በዝተዋል። በአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ የቤት ልማት ትግበራ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ኢንጂነር ኪያ ተሬቻ ለአዲስ ዘይቤ እንደሚገልፁት በ2014 ዓ.ም. ይጀመራሉ የተባሉ ከ75 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ቢኖርም በሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ፣ በፋይናንስ እጥረት እንዲሁም ለግንባታ የተዘጋጀ የፀዳ መሬት ማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል።
“35 ሺህ መኖሪያ ቤቶች በተለመዱት የመንግስት አስተባባሪነት የሚሰሩ እንዲሁም ከ40 ሺህ በላይ ደግሞ በአማራጭ የቤቶች ልማት መንገዶች ለመገንባት ቢታቀድም እስካሁን ጅማሮውን ማሳካት የተቻለው የተገጣጣሚ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን ብቻ ነው” ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንደሚሉት ከ15 ዓመታት በላይ ቆይተው የተገነቡት 400 ሺህ የማይሞሉ መኖሪያ ቤቶች ቀርፋፋ፣ ደህንነታቸውና ፅዳታቸው ያልተጠበቀ እንዲሁም ጥራት የሌላቸው፤ ከዚያም ሲያልፍ ለፖለቲካ ጥቅም በፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ተቃዉሞ የሚበዛባቸው የአንዳንድ ሰፈሮችን ነዋሪዎችን በልማት ስም ለመበተን ተብለው የተሰሩ ናቸው።
በጥር ወር 2014 ዓ.ም. መጀመሪያ በከተማ አስተዳደሩ ይፋ የተደረገው 10 ሺህ የተገጣጣሚ መኖሪያ ቤቶች አንዱ ጊዜያዊ መፍትሔ ነው። ፕሮጀክቱ በመጀመሪያ ዙር 5 ሺህ ቤቶችን በ1 ዓመት ለመገንባት በ8 ቢልየን ብር ፕሮጀክቱ ተጀምሯል። የተገጣጣሚ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከተለመደው የግንባታ ሂደት ሲነፃፀር ጊዜ እና ገንዘብ መቆጠብ እንዲሁም ጥራትን ማሳደግ የሚችል መሆኑን የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ይገልፃል፤ ባለሙያዎችም ይስማሙበታል።
የከተማ ፕላንና የኪነ-ህንፃ ባለሙያው ዮሐንስ መኮንን እንደሚገልፀው “ተገጣጣሚ መኖሪያ ቤቶች በፅንሰ ሀሳብ ደረጃ ብክነት ይቀንሳል፣ ጊዜን ይቆጥባል እንዲሁም በጊዜ መራዘም የሚመጣን የዋጋ ንረትን መቋቋም ያስችላል።”
ነገር ግን ይላል አርክቴክት ዮሐንስ “ተገጣጣሚ ቤቶች ይሰራሉ የተባለበት ዋጋ እና ሊሰራ የታሰበው የመኖሪያ ቤት ብዛት ሲነፃፀር በካሬ ሜትር የሚወጣው ዋጋ እና ለአጠቃላይ ግንባታው የሚወጣው ወጪ በፍፁም የሚመጣጠን አይደለም። ስለዚህ ክፍተት አለ ማለት ነው። በእኔ እይታ ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን የአንድ ሰሞን ማሟሟቂያ እንዲሆን ለማድረግ ይመስለኛል”
ኢንጂነር ኪያ ተሬቻ እንደሚገልፁት “በአዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመኖሪያ ቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄዱ እሙን ነው። በመሆኑም ችግሩን ያቃልላሉ ተብሎ የታቀዱ በቅርብ ጊዜ ወደ ትግበራ የሚገቡ 6 አሰራሮች ተዘጋጅተዋል”
የትግበራ መንገዶቹ በመንግስት አስተባባሪነት የሚከናወኑ ግንባታዎችን ማጠናከር፣ በህብረት ስራ ማህበራት የቤት ግንባታ ሲሆን ቤት ፈላጊዎች ተደራጅተው እንዲገነቡ የሚያደርግ ሲሆን ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ለእዚህ አማራጭ ተመዝግበዋል።
ሌሎቹ ደግሞ በመንግስትና በግል ባለሃብት አጋርነት ሲሆን መንግስት መሬትና ግብዓት የሚያቀርብበት፤ ባለሀብቶች ደግሞ እውቀትና ሀብታቸውን የሚያፈሱበት ይሆናል። በሽርክና (joint venture) የቤት ልማት ይተገበራሉ ከተባሉት የቤት ልማት አማራጮች መካከል ሲሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት እንዲሁም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሀብትና ቴክኖሎጂን በጋራ በመጠቀም ጥቅምና ጉዳቶችን የሚጋሩበት ነው።
ሪል ስቴት ደግሞ አላማቸው መካከለኛ እና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ላይ ቢሆንም በቅርብ ጊዜ ከመንግስት ጋር ተባብረው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች ቤት የሚሰሩበት ሁኔታ የሚመቻችበት ሲሆን የግል ቤት አልሚዎች ትግበራ ደግሞ ለራስ መኖሪያም ሆነ ለኪራይ የሚሆኑ መኖሪያዎችን የመገንባትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር የመፍትሔ አካል ይሆናሉ የተባሉት አካሄዶች የቤት ልማት ትግበራ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የኪነ-ህንፃ እና የከተማ ፕላን ባለሙያው ዮሐንስ መኮንን “መንግስት መኖሪያ ቤት እየገነባሁ አዳርሳልሁ ብሎ የያዘው አካሄድ ስሁት ነው ብዬ አምናለሁ” ይላሉ።
“የመኖሪያ ቤት ፍላጎቶችን ለመቅረፍ ተመራጭ መፍትሔ የሚሆኑት ዜጎች ቤት የሚገነቡበትን አቅም መገንባትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ህግና አሰራሮችን ማመቻቸት፣ መሬት የሚገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ መኖሪያ ቤት ማግኘት ለዜጎች ቅንጦና ስጦታ ሳይሆን መብት መሆኑን በአፅንኦት ማመን እንዲሁም በህዝብ ታክስ የሚገነቡ መኖሪያ ቤቶችን በአግባቡ ማዳረስ የግድ ነው”