(የአስተያየት ሰጪ አሽከርካሪዎች ስም ለደህንነት ሲባል ተቀይረዋል)
ህዳር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፤ አቤል አማርከኝ አየር ጤና አካባቢ ከጓደኛው ጋር በመኪና ውስጥ ተቀምጠው ሳለ ስልክ ይደወልለታል። በተደወለው ስልክም የታክሲ አገልግሎት ፈላጊዎች እንደሆኑና አቤል እንዲያደርሳቸው እንደሚፈልጉ ይነግሩታል። ተሳፋሪዎቹም ወደ ቡታጂራ መስመር የሚሄዱበት ቦታ መኖሩን ነግረውት ጉዟቸውን ጀምረዋል።
ከቀኑ 8፡00 ገደማ ከአዲስ አበባ ውጪ እንደሚሄዱ ስለነገሩት ለእህቱ በመደወል ሶስት ሰዎችን እንደጫነ እና ወደ ክፍለ ሀገር የሚሄድ ከሆነ እንደሚያሳውቃት ቢነግራትም ከእዛ ሰዓት በኋላ የአቤል ስልክ ዝግ ሆነ። በማህበራዊ ትስስር ገጾች አማካይነት አቤልን የማፋለግ ተግባርም ተጀመረ። በተለያዩ ጥቆማዎች ወደ ቡታጂራ መስመር የሄዱት ቤተሰቦቹ የአቤልን ተሽከርካሪ ሰሌዳዉ ተፈቶ ማግኘት ቢችሉም ልጃቸውን አላገኙትም። በፖሊስ ክትትል መሰረት ከ16 የፍለጋ ቀናት በኋላ የአቤል ህልፈት ለቤተሰቦቹ መርዶ ደረሰ።
ይህ በቅርቡ የተከሰተ ታሪክ ሆነ እንጂ የመጀመሪያ አይደለም። ቀደም ባሉት ጊዜያት በመዲናዋ ተመሳሳይ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ ያነጣጠሩ የግድያና የመኪና ዝርፊያ ወንጀሎች በተደጋጋሚ መከሰታቸዉን የፓሊስ ሪፖርቶች ያመለክታሉ። እንደማሳያ መውሰድ የምንችላቸው በማህበራዊ ትስስር ገጾች በስፋት የተዘዋወሩት ሲሆኑ ሁኔታዎቹን ለመጥቀስ ያህል በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. በተሽከርካሪው ውስጥ ህይወቱ አልፎ የተገኘው ቴዎድሮስ አበባው (ቴዲ ቡናማው)፣ በዛው ዓመት ሰኔ 2 ቀን ለስራ ከቤት የወጣው ሀብቴ ተመስገን የተባለ አሽከርካሪ ከ15 ቀናት በኋላ ሰኔ 16፤ 2013 ዓ.ም ቱሉ ዲምቱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሰዎች እጅ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተለመዱ ከመጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል የሆነዉ የሜትር ታክሲ አገልግሎቶች በተለይም በምሽት ለስራና ለተለያዩ የግል ጉዳዮቻቸው ለሚንቀሳቀሱ ሰዎች የተሻለ መፍትሔ ሆነዋል። ይኸው የትራንስፖርት አገልግሎት ለበርካታ የከተማዉ ነዋሪዎች በተለይም ለወጣቶች ሰፊ የስራ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር ከፍተኛ የትራንስፖርት አገልግሎቶት ችግር ለሚፈትናት አዲስ አበባም አንድ ተጨማሪ አማራጭ ሆኖ ብቅ ካለ ዓመታት ተቆጥረዋል።
እነዚህ በዲጂታል መተግበሪያ የታገዙ የትራንስፖርት አገልግሎቶች መጀመርና አሁን ላይ እየተለመዱ መምጣታቸው ለተሳፋሪዎች፣ ለስራ አጥ ወጣቶች እና ተጨማሪ ገቢ ለሚፈልጉ ሰዎችም እፎይታን ፈጥረዋል። ነገር ግን የሹፌሮችም ሆነ የተሳፋሪዎች ደህንነት የተጠበቃባቸው አለመሆናቸው በአሽከርካሪዉም ሆነ በተጠቃሚዉ ዘንድ ከፍተኛ ሰጋት እየፈጠረ ይገኛል።
ተሳፋሪዎች በአሽከርካሪዎች ስጋት ውስጥ ሲወድቁ በተገላቢጦሽ ደግሞ ሹፌሮች ደንበኛ ብለው በሚያስተናግዷቸው ግለሰቦች የዝርፊያ እና የግድያ ስጋት ውስጥ መግባታቸውን የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ የሆነች ግለሰብ ለአዲስ ዘይቤ ተናገራለች። “በተለይ እንደኔ ላሉ ሴት አሽከርካሪዎች ሁኔታው ሰራዉን እስከማቆም የሚያደረስ ዉሳኔ ላይ ሊያደርስ ይችላል” ትላለች።
እምብዛም ትኩረት ያላገኙት የወንጀል ተግባራት፤ በርካታ ቤተሰቦችን የሐዘን ማቅ አልብሷል፣ ጥቂት የማይባሉ ለጋ ሕጻናት ለእነሱ የሚለፉት ወላጆቻቸውን ይመጣሉ ብለው እየጠበቁ ወላጆቻቸውን በወጡበት አስቀርቷል።
በተጎጂ ቤተሰቦች ላይ እያሳረፈ የሚገኘው ሌላኛው ጠባሳ ደግሞ ወጥተው የቀሩ ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ አሰራጭተው በተስፋ ሲጠብቁ የልጆቻቸውን ሁኔታ ሳያውቁ እንዲሁም የሟቾች አስክሬን ለቀናትና ለሳምንታት የደረሰበት ሳይታወቅ መቅረት ነው።
መሰል ታሪኮች በሰው በሰው እየተሰሙ እና በማህበራዊ ገጾችም የአፋልጉኝ ጥሪዎች ተበራክተው ለብዙኀን ጆሮ የደረሱ መሆናቸውን ልብ ላለ ሰው ምንም ሳይሰማ ደብዛቸው የጠፉ፤ በቁጥር እንኳን የማይታወቁ ሌሎች አሽከርካሪዎች እንደሚኖሩ መገመት ያስችላል።
የወንጀሎቹ መደጋገም በአሽከርካሪዎች እይታ
ለአዲስ ዘይቤ አስተያየታቸዉን ያካፈሉ አገልግሎቱን የሚሰጡ አሽከርካሪዎችም የደረሱበት የማይታወቁ ብዙዎች እንደሚኖሩና ጉዳዩ እጅግ እያሳሰባቸው እንደቀጠለ ገልጸዋል። በረከት ኢሳያስ የተባለ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ እንደገለጸው መሰል ወንጀሎች እየተደጋገሙ መሆናቸው በእሱና በሌሎች አሽከርካሪ ባልደረባዎቹ ላይ ስጋት ፈጥረዋል። “የእንጀራ ጉዳይ ስለሆነ አለመስራት አይቻልም፤ ግን ደግሞ ማን ሌባ እንደሆነ ማን እንዳልሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ነው።” ሲል የገለጸው በረከት በሹፌሮች ደህንነት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ነግሮናል።
ሌላኛው የሜትር ታክሲ ሹፌር አማንይሁን መልካሙ እንደሚያስረዳው ደግሞ በተደጋጋሚ የሚሰማቸው በአሽከርካሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎችና ዘረፋዎች ከከተማ ግርግር ራቅ ያሉ አካባቢዎች ሲሄዱ እንደሆነ ታዝቧል። “አብዛኛዎቹ ወንጀለኞች ስራዬ ብለው የያዙት ተግባር በመሆኑ ከእኛ አቅም በላይ ነው።” ሲል አማንይሁን የችግሩን አስከፊነት ያስረዳል።
ያለስልክ ጥሪ እና ያለመተግበሪያ ትእዛዝ ተሳፋሪ በመምሰል መንገድ ላይ ጠርተው ወይም አስቁመው የሚሳፈሩ ሰዎች በስፋት ለወንጀል ድርጊቶቹ የሚያጋልጡ መሆናቸውን አሽከርካሪዎቹ በተደጋጋሚ እንደሚሰሙ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
ነገር ግን እስካሁን በራሳቸዉ ላይ ባይገጥማቸውም በስልክ ጥሪና መተግበሪያ የጠሩት አሽከርካሪ በሩቅ ተመልክተው ለዝርፊያ የማያመች ከመሰላቸው ትእዛዙን መሰረዝ፤ ይሳካልናል ካሉ ደግሞ ተሳፍረው ለወንጀላቸው አመቺ ወደሆኑ ራቅ ያሉቦታዎች መሄድ እንደሚፈልጉ የሚገልጹ እንዳሉም በስራው ላይ ከተሰማሩ ባልደረቦቻቸው የሰሟቸው ገጠመኞች መኖራቸውን ያነጋገርናቸው አሽከርካሪዎች ገልጸዋል።
በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ችግር በአሽከርካሪዎች እና በተሳፋሪዎች መካከል አለመተማመን እየፈጠረ እንደሚገኝ የገለጹት አሽከርካሪዎች ከሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች፣ ከጸጥታ ኃይሎች እና ከትራንስፖርት ባለስልጣን የተጠናከረ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
የሜትር ታክሲ አገልግሎት ከሌሎች የትራንስፖርት ዘርፎች ለየት የሚያደርገው እና ለተጠቃሚዎች ዋስትና የሰጠበት ዋነኛው ጉዳይ የደህንነት ደረጃቸው ከፍተኛ መሆኑ እንደሆነ የአገልግሎቱ ሰጪዎች በማስታወቂያቸው ላይ ሲገልጹ ይስተዋላል።
የሜትር ታክሲ አገልግሎት ድርጅቶች ምን ይላሉ?
የፈረስ ኮሚሽን ስራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ፈረስ ትራንስፖርት) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አበበ ሙሉ ለአዲስ ዘይቤ እንደገለጹት ፈረስ ስራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አሽከርካሪዎች በፈረስ ኦፕሬሽን (ስራ ላይ ሆነው) እስከ አሁን ሪፖርት የተደረገ ክስተት ባይኖርም በዘርፉ ላይ የወንጀል ድርጊት መኖሩን ተመልክተናል ብለዋል።
በጥሪ ማእከል፣ ለአሽከርካሪዎችና ለተጠቃሚዎች በተዘጋጁ መተግበሪያዎች እንዲሁም ለተቋማት በቀረበው ፖርታል አማካይነት የትራንስፖርት አገልግሎት እያቀረበ የሚገኘዉ የፈረስ ትራንስፖርት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደገለጹት አሽከርካሪዎች ችግርና አጠራጣሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው በአቅራቢያቸው ላሉ ለሌሎች 5 አሽከርካሪዎች መልዕክት ማስተላለፍ የሚያስችል አሰራር በአሽከርካሪ መተግበሪያ ላይ መኖሩን ገልጸዋል።
“በተጨማሪም ለጥሪ ማዕከል ሰራተኞች መረጃው እንዲደርሳቸው በማድረግ የአሽከርካሪዎችን ደህንነት በመደወል እንዲከታተሉ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነዉ” ሲሉም ጠቅሰዋል።
ዘላቂ መፍትሔ የሚሆነው ምንድን ነው?
የችግሩን አሳሳቢነት ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመቅረፍ ከጸጥታ አካላት ጋር አጠራጣሪ ጉዳዮችን መከታተል፣ የደህንነት ማረጋገጫ አሰራሮችን በተቋም ደረጃ በየጊዜው ማሳደግ፣ ግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች በፈረስ በኩል ይቀጥላሉ ብለዋል አቶ አበበ ሙሉ።ከላይ በአሽከርካሪዎች እንደተጠቀሰው በርካታ ወንጀሎች የሚፈጸሙት ከስርዓቱ ውጪ ማለትም በመተግበሪያ እና በጥሪ ማእከሉ ያልተመዘገቡ ተሳፋሪዎች አማካይነት መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ አበበ ሙሉ ገለጻ አሽከርካሪዎች ተጠቃሚዎችን በሚያሳፍሩበት ወቅት በጥሪ ማእከል እና በፈረስ መተግበሪያ የመጡ ትእዛዞችን ብቻ መቀበል ይገባቸዋል። በመንገድ ላይ አስቁመው የሚሳፈሩ ደንበኞችንም በመመዝገብ በተቋሙ ስርዓት ስር እንዲታዩ ማድረግ እና የስልክ ቁጥሮችን በመደዉል ትክክለኛነታቸውን በማረጋገጥ ተቋሙ እንዲያውቃቸው ማድረግ ይገባል ሲሉ አበበ ሙሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አሽከርካሪዎች በተመዘገቡበት ተቋም የቀረቡ የደህንነት መጠበቂያ አሰራሮችን መገንዘብና ጥቅማ ላይ ማዋል አስፈላጊ መሆኑን አዲስ ዘይቤ ያናገረቻቸው አሽከርካሪዎችና አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ገልጸዋል።
የራይድ ሜትር ታክሲ የተሽከርካሪ ዝርፊያን የሚከታተል እና በአቅራቢያው የሚገኙ ሌሎች የድርጅቱ አሽከርካሪዎች እና የጸጥታ አካላት አደጋ ለደርሰበት ሰው የሚደርሱበትን 'ዱካ ሁሉ' የተባለ አሰራር በ2012 ዓ.ም. ስራ ማስጀመሩ ቢታወቅም አፈጻጸሙን ለመረዳት እንዲሁም በአሽከርካሪዎች ደህንነት ዙሪያ የተቋሙን ሀይብሪድ ዲዛይንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርን ሀሳብ ለማካታት ያደረነው ሙከራ አልተሳካም።
አዲስ ዘይቤ የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ሳምራዊት ፍቅሩ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡን በእጅ ስልካቸዉ ላይ በተደጋጋሚ መልእክት ብትልክና ብትደዉልም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደሉም።