በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በርካታ ሰዎች የመኖርያ ቀያቸውን ለቀው በአጎራባች አካባቢዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል። በህወሓት ጦር ቁጥጥር ስር የነበሩት የአማራ ክልል አካባቢዎች በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ተከትሎ ባህርዳር ከተማ የተጠለሉ ተፈናቃዮች ወደ መኖርያቸው እየተሸኙ እንደሚገኝ ዘገባዎች አመላክተዋል። የተወሰኑት የመኖርያ አካባቢዎች በጦርነቱ ምክንያት በመውደማቸው፣ ማሳዎች እና መንደሮች በመቃጠላቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች ወደ መደበኛው የኑሮ መስመር ለማስገባት ተጨማሪ እገዛዎች ማስፈለጋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የመመለሳቸው ዜና አስደሳችና የመጀመሪያው ጥሩ እርምጃ ስለመሆኑ በብዙዎች ታምኖበታል።
በደቡብ ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ውስጥ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ቡድን መሪ አቶ ሥዩም አስማረ እንደሚያብራሩት በደቡብ ጎንደር ዞን ብቻ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከ68ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኛሉ። በ13 የገጠር ወረዳዎች ተጠልለው የሚገኙት ተፈናቃዮቹ ከኦሮምያ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የተፈናቀሉ ናቸው።
በእዳቤት፣ እስቴ፣ ሊቦከምከም፣ ሰዴ ሙጃ ወረዳዎች ተፈናቃዮቹ ከሚገኙባቸው መጠለያዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ከደብረ ታቦር ከተማ ውጭ ከሚገኙት መካከል ደግሞ ፋርጣ፣ ፎገራ፣ ደራ፣ ስማዳ፣ ጋይንት፣ መቀጠዋ ወረዳዎች ይገኙበታል። ነፋስ መውጫ ከተማም ተፈናቃዮቹ ከሚገኙባቸው ከተሞች መካከል ይካተታል።
አቶ ጀንበሬ ደሳለኝ ደብረታቦር መጠለያ ካምፕ የገቡት ከወለጋ አካባቢ ተፈናቅለው መሆኑን ይናገራሉ። ዕድሜ አቸው 55 ነው። የመኖሪያ አካባቢያቸውን የለቀቁት ከ6 ቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን ነው።
“የመጣነው መጋቢት 2013 ዓ.ም. ነው። ደብረታቦር ከተማ ከገባን አንስቶ ለተከታታይ ሰባት ቀናት አስፓልት ዳር ቴዎድሮስ አደባባይ ባዶ መሬት ላይ ተኝተን አሳልፈናል። በተደጋጋሚ በጠየቅነው የመጠለያ ጥያቄ በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እገዛ አሳምነው ጽጌ ባሰራው የመጠለያ ካምፕ እየተገለገልን እንገኛለን። በበጎ አድራጎት ማኅበራት እና በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ትብብር ፍራሽ፣ አልባሳት፣ ምግብ፣ የውሃ ጀሪካን እና የመሳሰሉ ድጋፎች እየተደረጉልን ይገኛል” ብለዋል። ነጻ የህክምና አገልግሎትን ጨምሮ በሰው የ15 ኪ.ግ. ስንዴ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ነግረውናል። ከመጪው ጥቅምት ወር አንስቶም ልጆቻቸው የትምህርት ዕድል ማግኘታቸውን ሰምተናል። “ነገር ግን” ይላሉ አቶ ጀምበሬ “ነገር ግን የምንተኛበት አልጋ እና ኩሽና ስለሌለን በክረምት ወቅት መሬቱ ውሃ እያፈለቀብን ለመተኛት ተቸግረናል። በዝናብ ወቅት የማብሰያ እና የማገዶ ችግር ነበረብን” ብለዋል።
የ39 ዓመቷ ሃዋ መሀመድ የምስራቅ ወለጋ ነዋሪ ነበረች። በደብረታቦር ካምፕ የመኖርያ እገዛ እየተደረገላት ይገኛል። የአልባሳት ቁሳቁስ፣ አልፎ አልፎም ቢሆን ለሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ እንደሚሰጣቸው ነግራናለች። “የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሁሉም በተሻለ ችግራችንን ይረዳል። ሦስት ቤተሰብ ሁኜ ወደዚህ ካምፕ መጥቻለሁ። ባለቤቴን በሞት ወለጋ ላይ አጥቻለሁ። ልጆቼን የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደልጁ በማየት እየተንከባከበልኝ ነው። ለደብረታቦር ህዝብ ምስጋና ይገባቸዋል” ብላለች።
“በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን በሁሉም ወረዳዎች ደብረታቦር ከተማን ጨምሮ 68,061 ተፈናቃዮች ተጠልለዋል” የሚሉት አቶ ሥዩም ተፈናቃዮቹ የቀድሞ መኖርያቸውን ጥለው አሁን ያሉበት መጠለያ ጣቢያ እንዲመጡ ያስገደዳቸው ቀዳሚ ምክንያት ድርቅ እና ጦርነት መሆኑን አንስተዋል። ከኦሮምያ፣ ከቤኒሻንጉል ክልሎች፤ ከዳውንት፣ ከታች ጋይንት፣ ከጉና በጌምድር፣ ከእብናት ወረዳዎች፤ ከዋግህምራ ዞን የመጡ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አቶ ስዩም ለአዲስ ዘይቤ ዲጅታል ሚድያ አብራርተዋል።
እርዳታ ከሚሹት ተፈናቃዮች መካከል በእብናት ወረዳ ብቻ ከ6ሺህ 3መቶ በላይ የሚሆኑት አረጋውያን እና ህጻናት ናቸው ብለዋል ኃላፊው።
ተገደው አካባቢያቸውን የለቀቁት እነኚህ ተፈናቃዮች ከመንግሥት የተለያየ ድጋፍ እንደሚያገኙ ኃላፊው ጠቅሰዋል። የእለት ደራሽ እገዛው በመከናወን ላይ የሚገኘው በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ በግል በተደራጁ ወጣቶች፣ በዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ነው። አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ፣ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ፣ ኬር ኢትዮጵያ የሚሰኙት ተቋማት የፍጆታ እቃዎች፣ አልሚ ምግቦች፣ የንጽሕና መጠበቂያዎች እና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን እያቀረቡ ከሚገኙት ተቋማት መካከል ይጠቀሳሉ። በተጨማሪም መንግሥት እና ግብረ-ሰናይ ተቋማቱ ከምግብ አገልግሎት በተጨማሪ ሙሉ የጤና አገልግሎት እየተሰጡ ይገኛል።
“የመኖሪያ አካባቢያቸውን ለቀው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙት ተጎጂዎች ከጣቢያው ውጭ መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ እንዲጠቀሙ እናበረታታለን” የሚሉት የምግብ ዋስተና ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ ሥዩም አስማረ “ተፈናቃዮቹ ሊያስጠጋቸው የሚችል ዘመድ ወይም ወዳጅ ካገኙ መንግሥት ይደግፋቸዋል። መጠጊያ የሌላቸው በተዘጋጀው መጠለያ ይኖራሉ። አሰራሩ የመጠለያ ጣቢያዎቹ እንዳይጨናነቁ ያደርጋል፣ የሥራ ጫና ይቀንሳል፣ ለተረጂዎቹም የተሻለ ምቾት እና ነጻነት ይኖረዋል” ብለዋል። በእብናት ወረዳ ከዋግህምራ ዞን የተፈናቀሉ ከ18ሺህ በላይ ሰዎችም ወደቀያቸው መመለሳቸው ተሰምቷል።
የፋርጣ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት የቅድሚያ ማስተንቀቂያ ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አድለው ተሻገርን ያገኘናቸው ለተፈናቃዮች የምግብ እህል እያከፋፈሉ ነው። አቶ አድለው “በፋርጣ ወረዳ ከተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ከተማችን ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች የምግብ እህል እያከፋፈልን እንገኛለን። በፋርጣ ወረዳ ብቻ 6,972 ተረጂዎች አሉን። ለአንድ ሰው 15 ኪ.ግ. ዱቄት ይሰጣል” ብለውናል።
በተጨማሪም አቶ አድለው “ወደፊትም መንግሥት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል” ያሉ ሲሆን፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለተፈናቃዮች እጁን መዘርጋት እንደሚገባው ሐሳብ አቅርበዋል።