ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ቀውስ እና መፈናቅል ባስከተለው ጦርነት ምክንያት በአማራ ክልል በርካታ ተፈናቃዮች ተጠልለዋል። በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችም የተለያየ ድጋፍ እየተደረጉላቸው ይገኛል። ተፈናቃዮቹ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካትታሉ። ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ አረጋዊያንም የችግሩ ገፈት ቀማሽ ናቸው። በመንግስት፣ በረድኤት ድርጅቶችና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ለህፃናት ለሴቶችና ለአካል ጉዳተኞች የገንዘብ ድጋፍን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች እየተደረገላቸው ይገኛል።
በአንፃሩ እድሜአቸው የገፋ አረጋዊያን ጦርነት ያለባቸውን አካባቢዎች ጥለው መሸሽ ባለመቻላቸው እርዳታ ወደሚያገኙበት መጠለያ ጣቢያ መገኘት አልቻሉም። በሚገኙበት አካባቢ ሥራ ላይ የሚገኝ የመንግሥት መዋቅር በመፍረሱ ይደረጋላቸው የነበረ ድጋፍ ተቋርጧል። በዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በከልሉ የሚገኙ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን ያሉበት ሁኔታ አሳሰቢ መሆኑን አድስ ዘይቤ ያገችው መረጃ ያመላክታል።
ቢሮው ያወጣው መረጃ እንደሚያመላክተው በ2013 ዓ.ም. የክልሉ አረጋዊያን ቁጥር ከአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ይገመታል። እንደ ኮሚሽኑ በቀጣይ አስር ዓመት በክልሉ የሚኖሩ አረጋዊያን ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ በ 1.25 በመቶ እንደሚጨምርና በ2022 ዓ.ም. 1.5 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ነው። በአማራ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ አረጋዊያን ጧሪና ደጋፊ እንደሌላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንደ ክልሉ ሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መረጃ በርካቶችን ካፈናቀለው ጦርነት በፊት ለበርካታ አረጋዊያን የድጋፍና እንክብካቤ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
አቶ መንበሩ የወርቅ ሚዛኑ በቢሮው የአረጋዊያን ጉዳይ ማስተባበሪያና መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንደገለፁት ቀድሞውንም በርካታ አረጋዊያን ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው የነበሩ ሲሆን ከጦርነቱ በፊት በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እና እንክብካቤ ይደረግላቸው ነበር። ከዚሀም መካካል በቤተሰብ ደረጃ ይደረግላቸው የነበረ ድጋፍ እና እንክብካቤ አቅም ያላቸው የቤተሰብ አባላት ጥለዋቸው ወደ አጎራባች ወረዳዎች በመሸሻቸው ያለ ጧሪና ቀባሪ ቀርተዋል።
በአማራ ክልል የአረጋዊያን ቁጥር እና የዕድገት ምጣኔ በተለያዩ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በኢትዮጵያ የሚገነውም የአረጋውያን ማኅበረ-ኢኮኖሚ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችል የተሰበሰበ የቅርብ ጊዜ መረጃ ባይኖርም በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት የአረጋውያን ቁጥር ከሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ነው። ይህም የጠቅላላ ህዝቡን አምስት በመቶ ማለት ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት በገጠር እንደሚኖሩ ሪፖርቱ ያሳያል።
የኢትዮጵያ አረጋውያን ቁጥር በ2037 ዓ.ም. ከዘጠኝ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ እና በወቅቱ ከሚኖረው ጠቅላላ ህዝብ አንጻርም ሰባት በመቶ እንደሚሸፍን ይገመታል። የአማራ ክልል አረጋውያን በተመለከተ ደግሞ በዚሁ ቆየት ባለው በ2007 ሕዝብ እና ቤት ቆጠራ መረጃ መሰረት ከአንድ ሚሊዮን በላይ አረጋውያን በአማራ ክልል የነበሩ ሲሆን የጠቅላላ ህዝቡን አምስት ነጥብ ዘጠኝ በመቶ እንደሚሸፍን እና አብዛኛው አረጋውያን ደግሞ በገጠር እንደሚኖሩ ቆየት ያለው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ ያመላክታል።
አቶ መንበሩ ቀደም ሲል ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋዊያን ይደረግ ስለነበረውና አሁን በግጭቱ ምክንያት ስለተቋረጠው ድጋፍ ሲያብራሩ “አንድም በክልል ደረጃ ከተገነባው የአማራ ክልል አረጋዊያን ገቢ ማስገኛ ህንፃ በሚገኝ ገቢ በክልሉ የሚገኙ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር” ይላሉ።
"በጦርነት ቀጠና በሚገኙ አምስት ዞኖች ለተውጣጡ ከሁለት መቶ ሰባ ስድስት በላይ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን በየወሩ የገንዝብ ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር በአሁኑ ወቅት ግን በአካባቢው የመንግሥት መዋቅር ባለመኖሩ እና የባንክ አገልግሎት በመቋረጡ ይደረግ የነበረው ድጋፍ ተቋርጧል" በማለት ያስረዳሉ።
በተመሳሳይ ፌድራል መንግስት በዘረጋው የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም Productive Safety Net Program (PSNP) መስራት ለማይችሉ አቅመ ደካማ አረጋዊያን የቋሚ ቀጥታ የገንዝብ ድጋፍ መርሃ-ግበር ተጠቃሚ የነበሩ 138,101 በላይ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩ አረጋዊን በተመሳሳይ የባንክ አገልግሎት ባለመኖሩ የገንዘብ ድጋፉ እየደረሳቸው አደለም የሚሉት ኃላፊው በተጨማሪም በጦርነቱ ቀጠናው በየቀበሌው በተቋቋሙ የማኅበረሰብ ድጋፍ እና እንክብካቤ ጥምረቶች በጦርነቱ ቀጠና ወስጥ በነበሩ ከሰባት ሽህ በላይ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው አረጋዊያን ይደረግ የነበሩ የተለያዩ ድጋፎችን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ማድረግ አልተቻለም በማለት ይገልፃሉ፡፡
"በጦርነቱ ቀጠና በተለያ ከተሞች በበጎ እድራጎት ማኅበራት የተቋቋሙ ከ8 በላይ ተቋማዊ የአረጋዊን ድጋፍ እና እንክብካቤ ማዕከላት አገልግሎታቸውን በማቋረጣቸው አረጋዊያን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም" ይላሉ።
ከዚህም በተጨማሪ በእድሜ ምክንያት በሚከሰቱ የጤና እክሎች የተዳረጉ አረጋዊያን በቋሚነት ይወስዷቸው የነበሩ መድኃኒቶች የጤና ተቋማት አገልግሎት በመቋረጡ እና አረጋዊያን ወደ ጊዚያዊ የተፈናቃይ ማቆያ መምጣት ባለመቻላችው ለከፋ የህይወት አድን መድኃኒቶች እጥረት ስለመዳረጋቸዉም ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አቶ ነፃነት ደስታ የአማራ ከልል አረጋዊያን ማኅበር ፕሬዘዳንት ናቸው። በከልል ደረጃ የሚገኘው ማኅበር በርካታ አባላት ያሉት ከሦስት መቶ አርባ አምስት በላይ ሌሎች በዞን እና በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ማኅበራትን አቅፎ እንደያዘ ይናገራሉ። አረጋዊያን በጉብዝና ዘመናቸው በተለያዩ የሙያ መስኮች እና ህዝባቸውን አገልግለዋል ሀገራቸውን ከውጭ ወራሪ ተጠብቃ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ማድረግ እንደቻሉ አስተውሰው ከጦርነቱ በፊት በመንግሰት እና በሕብረተሰብ ተሳትፎ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን ድጋፍ ይደረግላቸው እንደነበር ገልፀዋል።በአሁኑ ውቅት በጦርነቱ ምክንያት በርካታ ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያን ለከፋ ችግር ከመጋለጣቸው በተጨማሪ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች መምጣት ባለመቻላቸው ድጋፍ እየተደረገላቸው አለመሆኑን ለአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ አጫውተዋል። በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የሚሰጡ ድርጅቶች እንደ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች ለአረጋዊያን ትኩረት እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአጠቃላይ በሀገራችን በአለው የኑሮ ውድነት፣ ድህነት እና ከከተሜነትና ዘመናዊነት መስፋፋት እንዲሁም ከቤተሰብ መደጋገፍ ስርዓት መላላት ጋር ተያይዞ የሕብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ በእጅጉ እየተቀየረ ይገኛል። በዚህም አብሮ የመኖርና የመደጋገፍ እሴቶቻችን ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሸርሸራቸው ወትሮውንም የአረጋውያንን ተጋላጭነት አሳድጎታል። ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ ጦርነት ወቅት ደግሞ ተንቀሳቅሰው ማምለጥ የማይችሉ የአረጋዊያን ለከፋ ችግር መጋለጣቸው ለሁሉም ግልፅ ነው።
በመሆኑም ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ ተቋማት የሚደረገውን የአረጋውያን ድጋፍና እንክብካቤ ስራዎች እንደ አስፈላጊነቱ በማስተባበርና በማቀናጀት ለችግር የተጋለጡ አረጋውያንን መታደግ ለነገ የማይባል የሁሉም ባለድርሻ አካላት የቤት ስራ ነው።