በአዳማ ከተማ አራት የትራፊክ መብራቶች አሉ። የትራፊክ መብራቶቹ ወንጂ ማዞርያ፣ መብራት ኃይል፣ ቀበሌ 04 እና ሀኒ ኬክ ቤት አካባቢ ይገኛሉ። አገልግሎቱ በብልሽት፣ በመብራት እጦት እና በሌሎች ምክንያቶች እየተቆራረጠ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት የሰጡት የትራፊክ መብራቶች ቅሬታ ሲሰነዘርባቸው ይስተዋላል። በከተማዋ ነዋሪዎች ዘንድ የትራንስፖርት ፍሰቱን ከማሳለጥ ይልቅ የማጨናነቅ ሚና አላቸው የሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ አስተናግደዋል።
አዳማ መብራት ኃይል አካባቢ ያገኘነው ዮሐንስ ሙሉጌታ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ “ባጃጅ” ሹፌር ነው። የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጥቶ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን እንደሚያስተዳድር ነግሮናል። ዮሐንስ የትራፊክ መብራቶቹ ተጠግነው ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ስላለው ሁኔታ ሲናገር “ከምትጓዝበት የምትቆምበት ጊዜ ይበልጣል” ሲል ያማርራል። “የትራፊክ መብራቱ አስቸጋሪ ነው። መኪኖችን እንዲጓዙ እና እንዲቆሙ የሚያፈራርቅበት ደቂቃ አሞላል ላይ ችግር ያለ ይመስለኛል። ለምሳሌ ቀይ መብራት ላይ ቆይቶ ወደ አረንጓዴ የሚቀየርበት መንገድ ለአደጋ አጋላጭ ነው። ለበርካታ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት ሲሆን ተመልክቻለሁ” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።
“አሰራሩ መጨናነቅን እንጂ ፍጥነትን በተጨባጭ አልጨመረም” የሚለው ቴዎድሮስ ገዛኸኝ ለስራ እንቅስቃሴው የግሉን የቤት ተሽከርካሪ ይጠቀማል። የትራፊክ መብራቶቹ ዳግም ስራ መጀመር እያደገ ከመጣው የተሽከርካሪ ቁጥር አንጻር ጥሩ የሚባል መሆኑን ይናገራል። የመንገድ ጥበት እና የምልክት አለመከበር ለትራፊክ ፍሰቱ መስተጓጎል አንድ መንስዔ እንደሆነ የሚያምነው ቴዎድሮስ “እንደ 04 ቀበሌ ባሉ አካባቢዎች የመጫኛ ምልክቶቹ በጥናት የተቀመጡ አይመስልም። አሁን ከሚገኙበት ቦታ ጥቂት ራቅ ብለው ቢቀመጡ እና ወደ ማዞሪያ የሚጭኑት ታክሲ እና “ባጃጆች” ቦታ ቢቀየርላቸው በአካባቢው የሚስተዋለውን መጨናነቅ የሚቀርፈው ይመስለኛል” ብሏል።
ዋሲሁን አምባዬ ችግሮቹን በሂደት ማስተካከል እንደሚቻል ያምናል። በአሽከርካሪነት ሙያ የሚተዳደረው ዋሲሁን የአገልግሎቱ በተቆራረጠ ሁኔታ መካሄድ አሽከርካሪዎችም ሆነ እግረኞች አሰራሩን እንዳይረዱ እንቅፋት መሆኑ ቀዳሚው ችግር ስለመሆኑ አንስቷል። “የትራፊክ መብራቱ ለተወሰነ ጊዜ ሰርቶ መቋረጡ፣ በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት እየሰራ መበላሸቱ እንደ ቋሚ ልማድ እንዳይወሰድ ያስፈራል” ብሏል።
“አሽከርካሪዎች ተገቢ የሆነ የትራፊክ መብራት አጠቃቀም ልምድ አላዳበሩም። በጥሩ ንቃት የራሳቸውን ጊዜ ጠብቀው ሲያሽከረክሩ ዓይታይም። እግረኛውም በአግባቡ የትራፊክ መብራቱን ትእዛዝ ዕያየ ቢንቀሳቀስ ሁሉም በተሻለ ፍጥነት ይገለገላል” ሲል አስተያየቱን ይደመድማል።
በእምነት በለጠ ኮሌጅ አካባቢ በሚገኝ ክሊኒክ ውስጥ ትሰራለች። በየእለቱ ከቤት ወደ ሥራ ወይም ከስራ ወደ ቤት ስታመራ 04 እና መብራት ኃይል አካባቢ ያሉትን የትራፊክ መብራቶች እንደምታስተውል ነግራናለች። የትራፊክ መብራቱ አሁን ሥራ ላይ ያሉበትን እና ከዚህ በፊት ያልነበሩበትን ጊዜ በማነጻጸር በሰጠችው አስተያየት
“ምንም የተለወጠ ነገር የለም። እንደውም ተባብሷል ማለት ይቻላል። የትራፊክ መብራቱ በማይሰራበት ጊዜ ከማሳልፈው የበለጠ ጊዜ በትራንስፖርት ውስጥ አሳልፋለሁ። እንደ እግረኛም ለውጥ አላየሁም” ብላለች። የመንገድ መጨናነቁን በመጥላት በመንደው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በሚጓዙ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች አልፎ አልፎ እንደምትጠቀም ገልጻ ይህ ዓይነቱ አማራጭ ለዝርፊያ ስለሚያጋልጥ እንደማይመረጥ ነግራናለች።
04 ኮንዶሚንየም አካባቢ የምትኖረው ሲሳይ መሃመድም ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥታለች። ለተለያዩ ጉዳዮች ፍራንኮ እና ፖስታ ቤት በየቀኑ እመላለሳለሁ። መንገዶቹ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ያለባቸው ናቸው። ለቸኮለ ሰው በፍጹም አይሆኑም። አብዛኛው እግረኛ የመንገድ ደህንነት ሕጎችን አያከብርም። ትእግስት አልባ ነው” ብላናለች። “አሽከርካሪዎች የትራፊክ መብራት ሲያዛቸው በትክክለኛው ቦታ አይቆሙም። ከእግረኛ መሻገሪያ “ዜብራ” ጋር መኖር የሚገባውን ርቀት አይጠብቁም። ዜብራው ላይ ወይም ከዜብራው አልፈው ይቆማሉ። ይህ ሕግ አፍራሽ ልማድ ለአደጋ እና ለመንገድ መጨናነቅ ያጋልጣል” የሚል ሐሳቡን ያጋራን ደግሞ ተስፋዬ ጣሰው ነው። በተጨማሪም በትራፊክ መብራቶች አቅራቢያ የተተከሉ ምልክቶች በጉልህ ዓለመታየት የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ግንዛቤ ማነስን እንደሚያሳይ ያምናል።
በአዳማ ከተማ የሚገኘው ሪፍት ቫሊ የአሽርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም መምህር የሆነው አቶ ሽፈራው ተሾመ መጨናነቁን የፈጠረው የትራፊክ መብራቱ ቀለም እየቀያየረ የሚበራበት እና የሚጠፋበት ደቂቃ አሞላል ላይ በሚገኝ ስህተት ስለመሆኑ ይናገራል። “የሰዓት አሞላሉ ተመጣጣኝ አይደለም። ቀዩ መብራት ላይ 100 ሰከንድ፣ አረጓዴው መብራት ደግሞ 20 ሰከንድ ነው የሚፈጁት ይህ አሰራር ለመጨናነቁ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” የሚል አስተያየቱን ሲሰነዝር የአሽከርካሪዎች አሰልጣኙ ጃዕፈር አደምም በሽፈራው ሐሳብ ይስማማል። “ለምሳሌ ከፖስታ ቤት መብራት ኃይልን አልፎ ወደ ቴሌ የሚወስደው መንገድ ከፍተኛ የትራፊክ ፍሰት የሚታይበት ነው። ከማርያም በመብራት ኃይልን አልፎ ወደ ሳርቤት የሚወስደው መንገድ ግን የትራፊክ ፍሰቱ ዝቅተኛ ነው። ይሁን እንጂ የራፊክ መብራቱ ይህንን የመንገዱን ነባራዊ ሁኔታ ያማከለ የሰዓት ክፍፍል የለውም። የሰዓቱ ሙሌት የፍሰቱን ሁኔታ ያገናዘበ ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል” ይላል።
የአዳማ ከተማ ፖሊስ የትራፊክ ቁጥጥር እና ደህንነት ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ዓለማየሁ በቀለ ከአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ አሽርካሪዎች የትራፊክ መብራቱን ትእዛዝ የማክበር ፈቃደኝነት እንደሚጎድላቸው ነግረውናል። “እግረኛው የመንገድ አጠቃቀም ከፍተኛ ችግር አለበት። አሽከርካሪው ከመብራቱ ይልቅ ትራፊክ ፖሊስን ነው የሚፈልገው፤ የእነዚህ ድምር መጨናነቅ ይፈጥራል” የሚሉት ኃላፊው
"በሌሎች አቻ ስፋት ባላቸው ከተሞች ውስጥ ከመብራት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ችግሮች የሚመደቡት ሞተረኛ ትራፊክ ፖሊሶች ናቸው። እኛ ደግሞ ያሉን ሞተረኞች ሁለት ብቻ ናቸው። ይህ በተገቢው ሁኔታ እንዳንሰራ እንቅፉት ሆኖብናል። ይህን ጉድለት ለመሸፈን በትራፊክ መብራቶች ላይ ቋሚ ባለሞያ ተመድቦ እየተሰራ ነው” ብለዋል።
ባጃጅ እና ታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ደርቦ መጫን፣ ያለቦታ መጫን፣ ምልክቶች አለማክበር እኚህን በተመለከተ በእግረኞች እና በባለሞያዎች ለቀረበው ችግር ምላሽ የሰጡት ኮማንደር ዓለማየሁ ማስተማርን መሠረት አድርገን ብንሰራም እስከ አሁን ከተመዘገቡ 30 ሺህ ቅጣቶች ውስጥ 19 ሺው በታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰዱ መሆኑን ነግረውናል።
የአዳማ መንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን የትራፊክ ቁጥጥር ባለሞያው አቶ ዓለሙ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሰዓት አሞላል ላይ ከአዲስ ዘይቤ ለተነሳው ጥያቄ "እኛ ፍሰቱን መከታተል እንጂ የትራፊክ መብራቶቹ ገጠማ፣ አሰራር እና ቁጥጥርን የሚያሰራው የአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ነው" የሚል ምላሽ አግኝተናል።
የትራፊክ መብራቱ በሰው ኃይል ይደረግ የነበረውን ችግር በከፍተኛ ደረጃ አቅልሎታል። አሁን ካለው ውጤት አንጻር በቀጣይ እንደ ባለሥልጣን ጽ/ቤቱ ሌሎችም ቦታዎች ላይ ተጨማሪ የትራፊክ መብራቶች እንዲገጠሙ ጥቆማ ለመስጠት እያጠናን ነው።" ያሉት አቶ ዓለሙ በየትኞቹ ቦታዎች ላይ እንደሆነ በሒደት እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
በአዳማ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የመስረተ ልማት ክፍል ከትራፊክ መብራቱ ጋር በተገናኘ የሚሰሩ ኃላፊዎችን በአካል ለማግኘት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በስልክ ያነጋገርናቸው የክፍሉ ባልደረባ አቶ መገርሳ ቢሪና "እኛ የገጠማ ስራውን ካጠናቀቅን በኋላ የትራፊክ መብራቶቹን አስተላልፈናል። ስለዚህ ምላሽ መስጠት የሚችሉት እነርሱ ናቸው” ብለዋል።