የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ለታዳጊዎችና ወጣቶች ጤና እና የህይወት ክህሎት እውቀት መዳበር እገዛ የሚያበረክት 'የኔታብ' ተብሎ የተሰየመ የሞባይል መተግበርያ ሀሙስ ህዳር 23/2014 ዓ.ም. አስመርቆ ይፋ አደረጓል።
የስነ-ተዋልዶ ጤና ጥምረት ማህበር (CORHA) ፣ የተባበሩት መንግስታት የስነ ሕዝብ ፈንድ (UNFPA) እንዲሁም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን አዘጋጅተው ያቀረቡት ይህ መተግበርያ ወጣቶች ስለጤናቸው፣ ስለፆታ እና ስነ-ተዋልዶ ጉዳዮች፣ ስለ ኮቪድ 19፣ ስለ ህይወት ክህሎት፣ ስለ አደንዛዥ ዕፅ ጎጂነት እና በሌሎች ተያያዥ የጤና ጉዳዮች ላይ ተዓማኒነት ያላቸውን ጠቃሚ መረጃዎች የሚያገኙበት መሆኑ ተገልጿል።
አሁን ባለንበት ወቅት ወጣቶች ለመረጃ ምንጭነት ከሚጠቀሙባቸው መሳርያዎች መካከል ተንቀሳቃሽ ስልኮች ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተዘጋጀው የኔታብ በጎግል ፕሌይ ስቶር ላይ የሚገኝ ሲሆን አሁን ላይ በአማርኛ ቋንቋ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል። በቅርብ ጊዜ ውስጥም በአፋርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሶማሊኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተደራሽ እንደሚሆን ተገልጿል።
ይህ ጤና ተኮር መረጀ የሚሰጥ መተግበሪያ በዋናነት ወጣቶች ወደ ጤና ተቋማት መሄድ ሳይጠበቅባቸው መረጃዎችን ማግኘት እንዲችሉ ለማድረግ ታልሞ የቀረበ ሲሆን ነው ተብሏል።
“የወጣትነት እድሜ ለብዙ የጤና ጉድለቶች ተጋላጭ እድሜ መሆኑ ይታወቃል ነገር ግን፣ በእድሜ ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በተቃራኒው የጤናቸውን ሁኔታ በምን መልኩ መከታተል እንዳለባቸው ያላቸው ግንዛቤ በአንጻራዊነት አነስተኛ ነው። በመሆኑም ይህ መተግበርያ በስልካቸው ሲቀርብላቸው ጉዳዩ ላይ እንዲነቁ ከማድረግ ጀምሮ ትክክለኛ የጤና መረጃን ለማድረስ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶበት ነው የተሰራው” ሲሉ የስነ-ተዋልዶ ጤና ጥምረት ማህበር ፕሮጀክት ኦፊሰር የሆኑት ቤተልሔም በዛብህ ለአዲስ ዘይቤ አስረድተዋል።
እንደ ቤተልሄም ማብራሪያ በተለይ ለጾታዊ በሽታዎች ተጋላጭ የሆኑት ወጣቶች በእውቀት ማነስ ምክንያት ብቻ በጊዜ ህክምና ሳያገኙ አስከፊ ደረጃ ላይ የሚደርስቱንም ሆነ ህይወታቸውን የሚያጡትን መገመት አዳጋች አይደለም።
አክለውም አሁን ላይ የመዝናኛ ቦታዎች ከመብዛታቸው ጋር ተያይዞም ሆነ ስለጾታዊ ግንኙነቶች ጤናማነት ግንዛቤ ያለው ከጠቅላላው ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ሲሉ በዚህ ደረጃ ራስን ስለመጠበቅ እና ችግር ከተፈጠረ ደግሞ ስለሚያስፈልገው የህክምና ሂደት የሚያውቁ ዜጎች ጥቂቶች መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት የሚያወጡት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ በግንዛቤ እጦት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን ይህን ለመቀነስ ደግሞ የሕክምና ግንዛቤዎችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ይጠቁማል፡፡
በዚህ ረገድ የስነ-ተዋልዶ ጤና ጥምረት ማህበር በ1995 ዓ.ም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዘርፍም ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ተገልጿል። ይህንንም ተደራሽ ለማድረግ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር የአባላትን እንቅስቃሴ በማስተባበር እየሰራ ይገኛል።