ኅዳር 25 ፣ 2014

የድሬዳዋው ፈርጥ ዓሊ ቢራ

City: Dire Dawaማህበራዊ ጉዳዮች

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ አንጋፋ ድምፃዊያን መካከል አንዱ ነው።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

የድሬዳዋው ፈርጥ ዓሊ ቢራ

ግንቦት 18 በ1940 ዓ.ም. በድሬደዋ ከተማ ልዩ ስሙ ቀንደቆሬ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ተወለደ። በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ አንጋፋ ድምፃዊያን መካከል አንዱ ነው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ያቀነቀነ ሲሆን በኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ አረበኛ፣ ሀደርኛ፣ እና ሶማልኛ ቋንቋዎች ይጠቀሳሉ አሊቢራ። በአጠቃላይ 265 ዘፈኖችን ተጫውቷል። ያሳተማቸው የካሴት ቁጥር ግን ስድስት ናቸው። እናት እና አባቱ ያወጡለት ስም አሊ መሐመድ ሙሳ ነው። በ14 ዓመቱ የኦሮሞን ባህል ለማስተዋወቅ የተመሰረተውን “አፍራን ቀሎ” የተባለውን የሙዚቃ ቡድን ተቀላቀለ። የአሊ ቢራ የሙዚቃ ህይወት የተጀመረውም አሊ ቢራ የተሰኘውን ስሙን ያገኘውም ከዚሁ አፍራን ቀሎ ከተባለው የሙዚቃ ቡድን ጋር ተያይዞ በመሆኑ ስለ አሊቢራ ሲያነሱ ስለአፍራን ቀሎ አለማንሳት የማይታሰብ ነው።  

አፈንዲ ሙተቂ “ኡመተ ፈናን ኡመተ ቀሽቲ ዲሬዳዋ” በተሰኘው መጽሐፉ  ስለ አፍራን ቀሎ በዚህ መልኩ አብራርቷል። “አፍራን ቀሎን የመሰረቱት ሦስት ወጣቶች ናቸው። ዘመኑም 1954 ነው። እነዚያ ወጣቶች በጊዜው በኦሮምኛ ቋንቋ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን የሚያቀርብ ቡድን አለመኖሩ ስላንገበገባቸው “ለምን በቋንቋችን ሙዚቃና ቲያትር እድገት ላይ አተኩሮ የሚንቀሳቀስ ቡድን አናቋቁምም? በማለት መነጋገር ጀመሩ። ሃሳቡን ለጥቂት ሳምንታት ካንሸራሸሩ በኋላም ቡድኑን መሰረቱ። ስያሜውንም በአራቱ የምስራቅ ሐረርጌ የኦሮሞ ጎሳዎች ስም “ አፍራን ቀሎ” በማለት ጠሩት። ሦስቱ ወጣቶች በመሰረቱት ቡድን ዙሪያ ችሎታ ያላቸውን መለመሉ። በተበታተነ ሁኔታ የኪነ-ጥበብ ስራዎችን የሚሞካክሩ ወጣቶችን መሳብ ጀመሩ። በሀርሞኒካና በጊታር እየዘፈኑ የጫጉላ ሽርሽር ሲያደምቁ የነበሩትንም አሰባሰቡ። በዚህም መሰረት ዓሊ ሸቦ፣ ማሕሙድ ቦኼ፣ ሸንተም ሹቢሳ እና ሃሚዶ አሕመድ የመሳሰሉትን የዘመኑን ውብ ዜመኞች በአንድነት አጣምረው “አጃዒበኛ” ስራዎችን ወደህዝብ ማድረስ ጀመሩ። ህዝቡም በከፍተኛ ወኔና ሞራል ተቀበላቸው። በተለይ በአረፋና በዒድ አል ፈጥር በዓል የሚያቀርቡት የድራማና የሙዚቃ ትርዒት ከፍተኛ ዝናና ከበሬታ አስገኘላቸው። የድሬደዋ ባለሀብቶችም በልዩ ልዩ መልክ ይደጉሟቸው ጀመር። የሙዚቃ መሳሪያዎችን ከመግዛት ጀምሮ በሐረርጌ ከተሞች ውስጥ እየተዘዋወሩ ትርዒታቸውን የሚያሳዩበትን ሁኔታ እስከማመቻቸት የሚደርስ ድጋፍ አደረጉላቸው” ሲል ስለ አፍራን ቀሎ አመሰራረት ገልጿል።

አሊ ቢራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በድሬደዋ ከተማ በጀዲዳ እና በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ወደ አዲስ አበባ በማቅናት በካቴደራል ት/ቤት ተከታትሏል። አፍራን ቀሎ  የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወተው ሙዚቃ “ቢራጳ በሪኤ” ይሰኛል። አሊ ቢራ የተሰኘውን ስያሜም ያገኘው ከዚሁ ሙዚቃ ጋር ተያይዞ እንደሆነ ይነገራል። የአፍራን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን የቆየው ለስምንት ዓመታት ብቻ ነበር።

አሊ ቢራ ከአፍራን ቀሎ ቆይውታው በኋላ እ.ኤ.አ 1966 ዓ.ም. በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት ተጫውቷል፣ በ1977 ከካይፋ ሪከርድስ ጋር ሰርቷል። ችሎታው እየዳበረ ሲሄድም አይቤክስ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎችን በዲ አፍሪክ አቅርበዋል። አሊ ቢራ አሜሪካ በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት ተከታትሏል። ከመዝፈን ባሻገርም ፒያኖና ጊታር የሙዚቃ መሳሪያዎችን የመጫወት ብቃት አለው።

አሊ ቢራ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ራሱን እንዲገልፅ ተጠይቆ “እኔ ተማሪ ነኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን ምድር ላይ ወደ 7 ቢሊዮን ከምናምን ተማሪዎች አሉ። ከነዛ መሀል አንዱ ነኝ። ራሴን የማየው በዛ ዓይነት መንገድ ነው። ዛሬም እማራለሁ፤ ነገም እማራለሁ፤ ትላንትም ተማርኩኝ። ፈጣሪ በመዘነው ዓይነትና በሰጠኝ ያችን ብቻ ነው የማውቀው። እንጀራ እንጀራ ነው። ዳቦ ዳቦ ነው። እንደዚህ እንደዚህ ብሎ ከዚህ በላይ ከፍ እያለም የማውቀው ነገሮች አሉ። ስለ ትምህርት ከሆነ እድለኛ አይደለሁም። እንደ ብዙኃን የአገራችን ተጨቋኞች እና የደሀ ቤተሰብ ልጅ ስለሆንኩኝ እስከዚህም የመማር እድል አላገኘሁም። ግን በየቀኑ ትምህርት ቤት ሄጄ የምማረው ነገር አለ” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

የአሊ ቢራን የሕይወት ታሪክ የሚያትት "የምስራቁ ዋርካ" የተሰኘ መጽሐፍ በዶክተር ሱራፌል ግልገሎ ተፅፎ ለንባብ በቅቷል። መጽሐፉ የተዘጋጀው በሦስት ቋንቋ ሲሆን በአማርኛ "የምስራቁ ዋርካ" በአፋን ኦሮሞ "Odda Bahaa“ እና በእንግሊዝኛ “Growing Into Ethiopia” በሚሉ ርዕሶች ቀርቧል:: ደ/ር ሱራፌል መፀሀፉን ለመፃፍ አምስት አመታትን እንደፈጀበት መፀሀፉን ባስመረቀበት ወቅት የገለፀ ሲሆን መጽሐፉ  155 ገጾች አሉት።

በአማርኛ ቋንቋ ከተፃፈው የተወሰነው ይህንን ይመስላል።” እ.ኤ.አ በ1977 መጀመሪያ አካባቢ አሊ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ኮንትራት መፈራረሙን ተከትሎ የዛምቤዚ ክለብንና የዲ አፍሪክ ሆቴልን ለቆ በራስ ሆቴል ስራ ጀመረ። በወቅቱ የደንበኞች ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት የአይቤክስ ባንድ በራስ ሆቴል የሚያቀርበውን ዝግጅት ቅዳሜ ማታ ብቻ ለማድረግ ተገዶ ነበር።

ማህሙድ አህመድንና ሌሎቹ ስመ-ጥር ሙዚቀኞችን ያቀፈው አይቤክስ ባንድ አሊን ማግኘቱ የተቀዛቀዘውን የሆቴሉን ደንበኛ በማነቃቃት ገቢው ከፍ እንደሚያደርግ በማመን ነበር 1,000 ብር የወር ደመወዝ ሊከፍሉት የተስማሙት አሊ የስራ ስምምነቱን ከመቀበል ባለፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ200 ብር የአይቤክስ ሙዚቃ መሳሪያዎችን አክሲዮን መግዛት ቻለ።

እ.ኤ.አ በ1979 የአሊና የአይቤክስ ባንድ ወዳጅነት ጠንክሮ “አማሌሌ” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ለእርሱ አራተኛ ከባንዱ ጋር የመጀመሪያ የሆነውን አልበም ለገበያ በቃ። የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “አማሌሌ” ዘፈን አሊ ባደገበት በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚዘወተር ባህላዊ ዘፈን ሲሆን፤ አሊና ማህሙድ አህመድ በኦሮምኛና በአማርኛ እየተቀባበሉ በዘመናዊ መልኩ ሊጫወቱት ችለዋል። አይቤክስ ሙዚቃ ቤት የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ ሲሆን በወቅቱ ኦሮሞዎች ስራውን የተቀበሉበት የደስታ ስሜት ዛሬ ድረስ በህይወት ያሉ እማኞች በመገረም ያስታውሳሉ። “የሰዉ አቀባበልና ከአልበሙ ሽያጭ የተገኘው ትርፍ ከጠበቅነው በላይ ነበር” ይላል የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት አቶ ጣሃ አህመድ (የመሀሙድ አህመድ ወንድም) ስለአልበሙ ሲያስታውስ። የአልበሙ ሽያጭ አስጨንቆት የነበረው ሙዚቃ ቤት የካሴቱን ዋጋ ከተለመደው 15 ብር ወደ 12 ብር ያወረደው ሲሆን ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ህዝብ አልበሙን በእጁ ለማስገባት በመፈለጉ ማዳረስ እንኳን አልተቻለም። የመግዛት አቅምና አጋጣሚውን ያገኘ አልበሙን ተረባርቦ ገዛ። ያልቻለው ደግሞ አንዱ ከአንዱ እየተዋዋሰ አልበሙን ይኮመኩም ያዘ። “አማሌሌ” አልበም በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ከፍቅርና ከባህል ጋር ደባልቆ እያላቆጠ ለአደባባይ ቢያቀርበው የብዙዎችን ጆሮ አጠመደ፤ ከብዙዎች አንደበት አልጠፋ አለ።”

አሊቢራ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጭንቅላት እጢ ምክንያት የግራ ዓይኑ ማየት እንዳቆመና የቀኙም እየተዳከመ እንደሆነ በተለያዩ ሚዲያዎች ተነግሯል። እግሩም በካንሰር ተጠቅቶ በቀዶ ጥገና ህክምና እንደናነም ታውቋል። ከሁለት ዓመታት በፊት የውስጥ ደዌ ህክምና እየተደረገለት የነበር ሲሆን ከዚህ ቀደምም የልብ እና የስኳር በሽታዎች ታማሚ ነበር።

አሊ ቢራ ባለፉት 60 ዓመታት ለኦሮመኛ ቋንቋ የሙዚቃ እድገት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽፆ ከድሬደዋና የጅማ ዩንቨርሲቲዎች የክብር ዶክትሬት ተቀብሏል።

አስተያየት