የ41 ወንዞች እና የ77 ምንጮች መገኛ የሆነው የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ በከፍታው ከአፍሪካ 9ኛ ከኢትዮጵያ ደግሞ 3ኛ ነው። ከአዲስ አበባ 666 ኪሎ ሜትር፣ ከባህር ዳር 97 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። እንደ ደብር ታቦር ሁሉ ወረታ፣ ንፋስ መውጫ፣ አዲስ ዘመንና መካነ ኢየሱስ በዞኑ የሚገኙ አንጋፋ ከተሞች ናቸው። ዞኑ ከባህር ወለል በላይ ከ1,8ዐዐ እስከ 4,232 ሜትር ከፍታ ላይ ነው። ከእነዚህ ከፍተኛ ስፍራዎች መካከል አንዱ የጉና ተራራ ነው።
በደቡብ ጎንደር ዞን ሦስት ወረዳዎችን በሚያካልል ስፍራ ላይ ያረፈው የጉና ተራራ በዋናነት ሦስት ወረዳዎች ያዋስኑታል። እስቴ ወረዳ በስተምዕራብና ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ፣ ላይ ጋይንት ወረዳ በስተ ምስራቅና ደቡብ ምስራቅ ያለውን የተራራ ክፍል፣ ፋርጣ ወረዳ በስተሰሜንና ሰሜን ምዕራብ የሚገኘውን የተራራ ክፍል ያዋስናል። ከላይ ጋይንት ወረዳ ደቡባዊ ምዕራብ አቅጣጫ ከንፋስ መውጫ ከተማ 28 ኪሎ ሜትር፤ ከፋርጣ ወረዳ ደግሞ ከደብረ ታቦር በስተምስራቅ አቅጣጫ ከጋሳይና ክምር ድንጋይ በመነሳት ከጋሳይ 17 ኪሎ ሜትር ከክምር ድንጋይ 9 ኪሎ ሜትር እንዲሁም ከደብረ ታቦር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፤ በእስቴ ወረዳ በኩል የሚገኘው የጉና ተራራ ክፍል ጥንታዊ ቤተ ክርስትያኖች ይገኙበታል። ከእነዚህም መካከል ዋሻ ማርያም፣ አጎና ማርያምና አንጋጫት ማርያም ይጠቀሳሉ።
ጉና ተራራ በኢትዮጵያ በርዝመቱ 3ኛ ደረጃ የያዘ ተራራ ነው። ከባህር ወለል በላይ 4,231 ሜትር ከፍታ ያለው ይህ ተራራ በአጠቃላይ 9,192.04 ሄክታር መሬት ይሸፍናል። ጉና ተራራ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ማራኪ የመስህብ ስፍራዎች አንዱ ነው። በርካታ የዱር እንስሳትም መገኛ ነው። ከእነዚህም መካከል ቀይ ቀበሮ፣ ቀበሮ፣ ሚዳቋ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም በርካታ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ሃብቶችን እና ዓይነተ ብዙ እጽዋት መገኛም ነው።
በዚህ ተራራ ውስጥ ከሚገኙት ሰው ሰራሽ የተፈጥሮ ኃብቶች መካከል ከ736 ሄክታር በላይ የሆነ ሽፋን ያላቸው ነጭ ባህር ዛፍ እና የፈረንጅ ጽድ ይገኙበታል። ከ1228 ሄክታር በላይ የሚሆነው የተራራ ክፍል የሀበሻ ጽድ፣ አስታና ጅብራ የመሳሰሉ እጽዋት መገኛ ነው። የተለያዩ የሳር ዓይነቶችና አእዋፍ ይገኛሉ። እነዚህ ሳሮች የተለያየ ቀለም መጠን ዓይነትና ውበት ያላቸው የሳር ዓይነቶች ናቸው። በዋናነትም ጓንጭላ፣ ጭማና ጦስኝ ይጠቀሳሉ።
ከጉና ተራራ ስር ተነስተው ወደ ዝቅተኛ ቦታ ከሚፈሱ በርካታ ወንዞች መካከል አንጋፋዎቹ የጉማራ ወንዝ፣ በፋርጣ ወረዳ የርብ ወንዝ፣ የጉልጊ ወንዝ፣ የወለላ ባህር ወንዝ፣ ፍሻ ወንዝ፣ ሻጋ ወንዝ፣ የጭምጭሚት ወንዝና ዋንቃ ይገኙበታል። ከተራራው ከ40 የሚበልጡ ምንጮች ይፈልቃሉ።
ከፍተኛ የኖራ ድንጋይ /ግሃ ድንጋይ/ ክምችትም ይገኛል። ጉና ለበግ እርባታ የተመቸ ነው። የጉና ተራራ ጫፍ የፕላቶማ መልክአ ምድር ቅርጽ ያለውና ሜዳማ ከመሆኑ በላይ የተራራውን ጫፍ በየአቅጣጫው በእግር ለማቋረጥ ከሦስት ሰዓታት በላይ ይፈጃል። ይህ ተራራ በክረምት ወቅት በጉም የሚሸፈን ሲሆን አልፎ አልፎ የበረዶ ክምር ከአናቱ ላይ ይቆለላል።
በጉና እና አካባቢው የሚኖሩ አርሶ አደሮች እንደ ድንች፣ ገብስና ስንዴ የመሳሰለውን ያመርታሉ። ጉና ተራራ በሚገኝበት ቀበሌ የተለያዩ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ መስህቦች ሲኖሩ የሞክሽ እርግብ ዋሻ ተፈጥሮአዊ መስህብ፣ የሞክሽ ኪዳነ ምህረት፣ ሞክሽ መርቆሪዎስና ሞክሽ መድኃኒዓለምና ማርያም ቤተ ክርስቲያን ዋናዎቹ ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የእድሜ ባለጸጋ አባ አረጋ “ጉና ተራራ የታሪክ አውድማ ነው ማለት ይቻላል። የተበደሉ ለነፃነት ትግል የሚመርጡት፣ አቅም አጥተው የሸሹ ህይወት ለማትረፍ ከለላቸው አድርገው የሚቆጥሩትና በተፋፋመ ውጊያ ከጭቁኖች ጎን የሚሰለፍ የተፈጥሮ ፀጋ ነው” ይላሉ።
ታላቁ የጉና ተራራ በዘውዳዊውና በአምባገነናዊው የደርግ መንግስታት ግፍና በደል ሸሽተው የተጠጉት ንፁሃን ዜጎች በፀጋ ተቀብሎ በስሩ አቅፎ በያዛቸው በርግብና በሞግሽ ዋሻዎች በማስተናገድ ሲታደጋቸው እንደኖረ የአካባቢው ነዋሪዎችም ይመሰክራሉ። ጉና ተራራ ኢህአዴግና ደርግ በሙሉ አቅማቸው የተፋለሙበት የውጊያ ቀጠናው ጭምር ነው። የደርግ መንግሥት በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ የሞት የሽረት ትንቅንቅ አካሂዷል። ኢህአዴግ ደግሞ ጉና ላይ ቆሞ አዲስ አበባን በርቀት ለመመልከት በጽናት ተዋድቋል። በጉና ተራራ ጫፍ የተካሄደው ታላቁ ፍልሚያ የማታ ማታ በኢህአዴግ ታጋዮች ድል አድራጊነት ተቋጭቷል ሲሉም አክለውልኛል።
ጉና ተራራ በአካባቢው ነዋሪዎች የውሃ እናት ወይም የውሃ ማማ ተብሎ ይጠራል። ምክንያቱ ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ያለማቋረጥ የሚፈሱና ከተራራው የሚመነጩ ከሰባት በላይ ወንዞች አሉት። በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ለጣና ሀይቅ ህልውና ወሳኝ መሆኑንም ባለሙያዎች ይናገራሉ። ተራራው በተፈጥሮ የታደለ ነው።
አሁን ላይ ይህ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ የሆነው የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ ይላሉ የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መቶ አለቃ ፈንቴ መብራቱ።
እንደ መቶ አለቃ ፈንቴ ገለጻ የጉና ተራራን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳን የተረዳው የአማራ ክልል ምክር ቤት በአዋጅ (ደንብ) ቁጥር 147/2008 የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት እንዲቋቋም አውጇል። በአዋጁ መሰረት የጉና ተራራ ማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ጽሕፈት ቤት በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም. ተቋቁሞ ወደ ስራ ገባ። ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ተቋማት፣ ግብረ-ሰናይ ድርጅቶች፣ ምሁራን፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከአመራሩ ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ 4 ሽህ 615 ሄክታር ለመከለል እና ለመጠበቅ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። በአጠቃላይ ስምምነት ከተደረሰበት የጉና ተራራ ጥብቅ ስፍራ ውስጥ 1ሺህ 540 ሄክታር አካባቢ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ሲጠበቅ እንደቆየ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ይናገራሉ።
አክለውም ጉና ተራራ በአግባቡ ከተያዘ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጽቶ እንዲለማ ከተደረገ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል። አቅፎ የያዛቸው የተፈጥሮ ሀብቶች ይበራከታሉ። በመጥፋት ላይ ያሉት ያንሰራራሉ። የተሰደዱት እንስሳትም ወደ ቋሚ ቦታቸው ይመለሳሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ወንዞቻችንና ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ ይታደጋቸዋል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም እየጎላ ይሄዳል። አሁን ላይ ሆነን ስንመለከተው ግን የተቀናጀ ስራ ካልተካሄደበት በስተቀር ተራራው አደጋ ላይ ነው ይላሉ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው።
“ላለፉት ሁለት ዓመታት ተከልሎ በተጠበቀው የጉና ተራራ አካባቢ በስነ-ምህዳሩ ላይ ከፍተኛ መሻሻል እና አበረታች ውጤቶች እንደተገኙ ምሁራን እና የአካባቢው ማኅበረሰብ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር” የሚሉት መቶ አለቃ ፈንቴ “ቀሪውን የጉና ተራራ ክልል ለማስፋት እና ለማጠቃለል ግን አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ ሆኗል” ይላሉ።
የግንዛቤ ፈጠራው በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱን፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ዝቅተኛ መሆኑን እና ቃል የተገባላቸው የመሰረተ-ልማት ግንባታ በጊዜው አለመፈፀሙን እንደ ችግር ያነሱት መቶ አለቃ ፈንቴ “የአካባቢው አርሶ አደሮች የግጦሽ ሳር ፍለጋ ከብቶቻቸውን ያሰማሩበታል። የእርሻ መሬት ለማስፋፋት የሚደረገው የደን ምንጠራም ተራራውን አራቁቶታል። ይህንኑ ተከትሎ ደግሞ የአፈር መሸርሸሩ ተጨማሪ ጉዳት ይዞ እየመጣ ነው” ብለዋል።
ጉና ተራራ ስር ተወልደው ያደጉት አቶ አረጋ “የተራራው መራቆት እኛው የፈጠርነው ችግር ነው። የማዳኑ ኃላፊነቱም የኛው መሆን አለበት” በማለት ካለፈው በመፀፀት በቁጭት ተነሳስተው አካባቢያቸውን መልሶ ለማልማት ዝግጁ መሆናችው ይገልፃሉ። “ነዋሪው ህዝብ በአንድነት ከተረባረበ ተራራው መልሶ ማዳን ይቻላል። በመሆኑን መንግሥትና ህዝብ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለጥፋት ሳይሆን ለልማት ጉና ተራራን ልንወጣለትና ልንደርስለት ይገባል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሌላኛው ወጣት አያሌው ጉና ተራራ ስር አዳራ በሚባል ስፍራ ኗሪ ነው፡፡ “መንግስት ለአየር ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚያካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለጉና ተራራም ቀን የሚያወጣለት ይመስላል። ሀገር በቀልና የተለያዩ ችግኞች እየተተከሉ ነው። ግን ቀዳሚው ነገር የግንዛቤ ማበልፀግ ስራ መሆን አለበት። የአካባቢው ነዋሪዎች የተራራው ልማት ልማታችን ነው ብለው በእምነት ሊቀበሉት ይገባል። በባለቤትነት መንፈስም ሊጠብቁት፣ ሊንከባከቡትና መልሰው ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ማስተማር ግድ ይላል ሲል አስተያየቱን አስቀምጧል።
በመጨረሻም የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ እንደገለፀው ተራራው በልዩ ትኩረት እንዲለማ፣ በውስጡ ያሉት ሀብቶች እንዲጠበቁና እንዲጎለብቱ በማድረግ ለቱሪዝም መስህብነት አገልግሎት እንዲውል እየተሰራ ነው። ተራራው በማልማት የንብ ማንባት ስራ በስፋት ማካሄድ ይቻላል፣ ከጥብቅ ደኑ የሚገኘው ሳር ለከብት ማድለብ ተግባር ይጠቅማል። የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ምርትና ምርታማነትት ለማሳደግ ይረዳል። ወደ ወንዞቻችንና ግድቦቻችን የሚሄደውን ደለል በመከላከል የኃይል አቅርቦታችን አስተማማኝ በማድረግ ሀገራዊ የልማት ውጥኖቻችንን በማፋጠን ተጠቃሚነታችንን እናረጋግጣለን ብለዋል።