ነሐሴ 6 ፣ 2013

የጉዳቱን ያህል ትኩረት ያልተሰጠው 'ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች' ጉዳይ

City: Addis Ababaጤና

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቶሎ ምልክት ስለማያሳዩ ውስጥ ውስጡን ብዙዎችን እየቀሙ ሲሆን በዚህ የሚሰቃዩና እስከወዲያኛው የማይመለሱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ሄዷል። እንዲህ ያሉ ታሪኮች በሀገራችን መሰማት እና መታየት ከጀመሩም ቆየት ብለዋል።

የጉዳቱን ያህል ትኩረት ያልተሰጠው 'ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች' ጉዳይ

ሰላማዊት መስፍን ትባላለች፣ በወጣትነት የእድሜ ክልል ላይ ትገኛለች። ከግብ ልታደርሰው የሰነቀችው ብዙ ዕቅድ፤ ልታሳካው ያለመችው ህልም አላት። በዚህ መሀል ግን በአንድ ክፉ ቀን ኩላሊቷ መጎዳቱንና በቶሎ ሕክምና ካላገኘች ለህይወቷ በጣም አስጊ እንደሆነ ሲነገራት ሁሉም ነገር እንደጨለመባት በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆና ትናገራለች::  

"ጎኔ ላይ የውጋት ስሜት ሲደጋገምብኝ ነበር ወደ ሀኪም ቤት የሄድኩት። ቀለል ያለ በማስታገሻ መድሀኒት የሚድን በሽታ እንደሚሆን ጠብቄ ነበር ግን የገጠመኝ ሌላ ሆኖ ተገኘ፣ በየጊዜው እጥበት ማከናወን ደግሞ በኔና በቤተሰቦቼ አቅም የሚሞከር አይደለም" ስትል ሰላማዊት ያለችበትን ሁኔታ ነግራናለች።

" ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም ቢሆን ነገ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ በማድረግ እየሞከርን ነው" ትላለች። ያ ተስፋ ግን ፊቷ ላይ አይታይም።  

ከፍሎ ለማሳከም የገንዘብ አቅም የሌላቸው ቤተሰቦቿ የልጃቸውን ህይወት ለመታደግ በየአቅጣጫው ተፍጨረጨሩ። አማራጭ ጠፋ። ከሚኖሩበት ቀበሌ የኑሮ ደረጃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ አስጽፈው በየጎዳናው በተሽከርካሪ እየዞሩ ለኩላሊት እጥበት የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ ጀመሩ። በተገኘው ገንዘብ እጥበት እንዲደረግላት እያደረጉ ወደፊት የሚሆነውን በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ይጠብቃሉ።

ይህ ታሪክ የሰላማዊት ብቻ አይደለም። ግርማ አሰፉ ነዋሪነቱ በአዋሳ ከተማ የሆነ በመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጥሮ የሚሰራ የ47 ዓመት ጎልማሳ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ የደም ግፊት በሽታ እንዳለበት የተነገረው ከ7 አመት በፊት አዲስ አበባ እያለ እንደነበር ይናገራል። 

በመጀመሪያ ሰሞን ከፍተኛ የራስ ምታት ህመም ይሰማኝ ነበር። ህመሙ እየጨመረ ሲሄድ ወደ ሆስፒታል ሄጀ ምርመራ ሳደርግ የደም ግፊት በሽታ እንዳለብኝ ተነገረኝ የሚለው ግርማ በሰዓቱ በጣም አስደንግጦት እንደነበር ያስታውሳል::  

"በሽታው ካልተመጣጠነ የሰውነት ክብደትና በአመጋገብ ችግር እንደመጣ ስለተረዳሁ እራሴን በማረጋጋት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመስራትና አመጋገቤን በማስተካከል ለመቆጣጠር ሞከርኩ" ይላል።

ይሁን እንጅ ህመሙ እየጠናበት በመሄዱ በተደጋጋሚ ሀኪም ቤት እየተመላለሰ ህክምና በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ይገልፃል።

"ለህክምና ወደ ሆስፒታል ስሄድ በተለያዮ የእድሜ ክልል የሚገኙ በርካታ የስኳር፣ የኩላሊት፣ የደምግፊት ታማሚዎች ጋር እገናኛለሁ። ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቶሎ ምልክት ስለማያሳዩ ውስጥ ውስጡን ብዙዎችን እየቀማን እንደሚገኝ አስተውያለው" ይላል። 

"ትልቁ ነገር በሽታው ከመባባሱ በፊት ቀድሞ መጠንቀቅ ነው" ሲል ግርማ ይመክራል።

እንዲህ ያሉ ታሪኮችን በሀገራችን መሰማት እና መታየት ከጀመሩ ቆየት ብለዋል። በእንዲህ ባለ ህመም የሚሰቃዩ እና እስከወዲያኛው የማይመለሱ ሰዎች ቁጥርም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሄዷል። 

የዕድሜ ልክ በሽታ ሆኖባቸው በየቀኑ መድኀኒቶችን እየወሰዱ በህይወትና በሞት መካከል ሆነው ለመኖር የተገደዱም ጥቂቶች አይደሉም። ይህ ጉዳት በአንድ ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ላይ ሲከሰት ጫናው ለአገር የሚተርፍ እንደሚሆን አይዘነጋም። 

በጎንደር ዪኒቨርስቲ የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ሕክምና ክፍል ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት መምህርት፣ ሐኪምና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሽታዬ ዓለሙ “ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በንክኪ ወይም በሽታ አምጪ በሆኑ ተህዋሲያን ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፉ አይደሉም ” ሲሉ ይነግሩናል። 

ይሁን እንጂ በሽታዎቹ በዘር ሊተላለፉ የሚችሉበት እድል ሰፊ ነው ይላሉ በኤች አይ ቪ ኤድስ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ በርካታ ጥናቶችን የሠሩት ፕሮፌሰሯ።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እጅግ በርካታ በመሆናቸው በዋና ዋና ክፍሎች ሰብሰብ አድርጎ ለማጥናት፣ ለመመርመርና መፍትሔ ለመፈለግ ይረዳ ዘንድ የዓለም ጤና ድርጅት እነዚህን የጤና እክሎች በአራት ዘርፍ ተከፍለው እንዲታዩ እንዳስቻለም ይገልጻሉ::

 “በዋናነት ከሚጠቀሱት የስኳር በሽታ፣ የልብ እና የደም ሥር በሽታዎች፣ ተከታታይነት ያለው የመተንፈሻ አካል በሽታ እና ካንሰር ጀምሮ በስራቸው በርካታ የበሽታ ዝርያዎች መጥቀስም ይቻላል፤ ሊድኑ ከሚችሉት አንስቶ ፈጽሞ መድኀኒት እስከሌላቸው ድረስ ” በማለት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

በተመሳሳይ በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ “እነዚህ በዋናነት የተቀመጡ አራቱ ተላላፊ ያልሆኑ የበሽታ ዓይነቶች ትኩረት ያገኙት በጠቅላላው ካሉ ተላላፊ በሽታዎች መካከል 71 በመቶ ድርሻ ስለሚይዙ ነው በተጨማሪም በዓለማችን ከሚከሰቱ ሞቶች መካከል 70 ከመቶ የሚጠጉት በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት የሚከሰቱ ሲሆኑ ከዚህም 85 በመቶ የሚደርሰው ሞት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚታይ ነው ” ሲሉ ያስረዳሉ።

ዶክተር ኩኑዝ በዋናነት በሚከታተሉት የካንሰር ሕመምን እንደምሳሌ በማንሳት " በዓመት ውስጥ 67 ሺሕ ሰዎች በአዲስ ካንሰር ሕመም ይያዛሉ  ወደ ሕክምና ዘግይቶ መምጣት፣ የሕክምና ተቋማት ዝግጁ ባለመሆን፣ የሠለጠነ ባለሙያና መሣሪያ እንዲሁም መድኀኒት ባለመኖሩ ሞቱ ከፍ እንዲል ሆኗል። በተመሳሳይ ስኳር፣ ከደም ሥር ጋር የሚገናኙ እንደ ደም ግፊትና እሱን ተከትሎ የሚመጡ በሽታዎች እንዲሁም አስም እና መሰል ከመተንፈሻ ጋር የተገናኙ በሽታዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃም በከፍተኛ ሁኔታ ተንሰራፍተው ይገኛሉ " ሲሉም አብራርተዋል

አንዳንዶቹ የበሽታ ዓይነቶች በጊዜ ከተደረሰባቸው የሚድኑ ቢሆኑም እንደተባለው ወደ ሕክምና ዘግይቶ መሔድ የመዳን ዕድሉን ያጠበዋል። ከግንዛቤ፣ ከቸልታ እንዲሁም ከምርመራ ወጪና መሰል ምክንያቶች የተነሳ ሕመም ካልተሰማው በቀር ወደ ሕክምና የሚሔደው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቂት መሆኑንና አብዛኞቹ በሽታዎች ደግሞ ከፍተኛ ደረጃ ካልደረሱ በቀር ምልክት እንደማያሳዩ የሚያስረዱት ዶክተር ሽታዬ፡ እነዚህን በሽታዎች ማኅበረሰቡ ‘የሀብታም በሽታ’ እያለ መጥራቱ ቀልድ ቢመስልም ከፍተኛ አደጋ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ፈጥሯል ይላሉ።

በተመሳሳይ ዶክተር ኩኑዝ በዚሁ ሐሳብ ላይ ሲያክሉ፤ በሽታው በአብዛኛው ባደጉ አገራት መታየቱ በአዳጊ አገራት ሊኖር የሚገባውን ትኩረት እንዳዘገየውና ይሄ ስያሜ የመጣውም ከዛ መሆኑን አውስተው “አሁን ግን በሽታዎቹ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ እንዲሁም አዳጊ የተባሉ አገራት ሰው እየጨረሱ ነው። በሠለጠኑ አገራት ነገሩ ቶሎ ታውቆ አሁን እየቀነሰ ነው፤ መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ደግሞ ሳይቀንስ ሳይጨምር ተደላድሎ አለ። ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ባሉ አገራት ግን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው፤ ምክንያቱም አጋላጭ ሁኔታው በዝቷል” ሲሉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እነዚህ በሽታዎች ትኩረት ያገኙት በቅርብ ጊዜ ነው። ይህም መሆኑን ዶክተር ኩኑዝ ሲያብራሩ፣ “ትኩረት የተሰጠው ከረጅም ጊዜ ተሞክሮ በኋላ ሲሆን ከዛ ቀደም የጤና ፖሊሲው ተላላፊ በሽታዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውሰዋል። ይሁንና በተለያየ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች በዓለምም ሆነ በአገራችን ደረጃ በሽታዎቹ የሚያደርሱት ጉዳት እየሰፋ መምጣቱን በማመላከታቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ትኩረት ሊስቡ ችለዋል” ብለዋል።

በኢትዮጵያም የኑሮ ዘይቤና አኗኗር መቀየሩ ተጋላጭ ሁኔታዎችን እንደጨመረ ዶክተር ሽታዬ በአንክሮ አንስተዋል። እንደ ዶክተሯ እይታ በተለይም ከተሜነት በተስፋፋባቸው አካባቢዎች ጤናማ ያልሆነ የአኗኗር ዘይቤ ይታያል። ኬክ ቤቶች በየቀኑ መከፈታቸው እና ጣፋጭ ያለገደብ መበላቱ፣ ጥሬ ስጋ የወጣቶች ትልቅ የመዝናኛ ምግብ መሆኑ፣ በየመጠጥ ቤቱ በብዛት የሚታዩት ሰዎች፣ የሲጋራ አጫሽ ዜጎች ቁጥር መብዛት፣ የቅባት ምግቦች ፍላጎትና ተጠቃሚነት መጨመር፣ሞባይል ላይ ዓይናቸውን ተክለው የሚውሉ፣ ፀሐይ ወጥታ እስክትገባ ፊልም በመመልከት የሚያሳልፉ ልጆችና ወጣቶች፣ ከዘመናዊነት ይልቅ አደገኝነቱ እየጨመረ መሆኑን አረጋግጠው “በተጨማሪም ቢሮ ውስጥና በየቤታቸው ቁጭ ብለው የሚውሉ ሰዎች ተጋላጭ ከመሆናቸው በላይ መብዛታቸው ያሳስባል” ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁትን አንድ ጥናት ይፋ አድርጎ ነበር። በዓለም ጤና ድርጅት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ኦፊሰር ዶክተር አስማማው በዛብህ ይህንን እና ሌሎች ተያያዥ ዘገባዎችን መሠረት አድርገው ለአዲስ ዘይቤ እንዳስረዱት፤ በዓለም በዓመት ከሚሞተው 57 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 41 ሚሊዮን ለሚሆነው ሞት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምክንያት ሲሆኑ፤ ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ በአራቱ ዋና ዋና በሽታዎች ይያዛል። 

የጥናቱ አንዱ ዓላማ በሽታዎቹ የሚያስከትሉትን ኪሳራ ማሳየትና በተቋማት መካከል ቅንጅት ተፈጥሮ መከላከል እንዲቻል ማመላከት ነበር። ይህንንም መሠረት አድርገው ዶክተር አስማማው፤ “አጋላጭ የተባሉት ምክንያቶች ከኢኮኖሚ ጋር ይያያዛሉ። አልኮል በራሱ ብዙ ብዙ የሰው ኀይልና ገንዘብ የያዘ ነው፣ ትንባሆም እንደዛው። በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ጫትም እዚህ ጋር ይካተታል። እነዚህ የኢኮኖሚ ፍላጎት አላቸው። ይህንንም የጤናው ዘርፍ ብቻውን ሊከላከል አይችልም። ስለዚህ በእነዚህ በሽታዎች ምክንያት የሚደርሰውን ጥፋትና ኪሳራን በማሳየት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ብንከላከልና ብናክም የምናወጣው ብር እና ሳናክም ብንተዋቸው የምናወጣው ብር ምን ያህል ይሆናል የሚለው በጥናቱ ታይቷል።”

መንግሥት ለሕዝቡ ተጠያቂነት ተሰምቶት ከሚንቀሳቀስባቸው የማኅበራዊ ዘርፎች መከላከል የጤናው መስክ አንደኛው በመሆኑና ኀላፊነት ስላለበትም ሥሙ ሳይጠራ አይቀርም። በዚህም መሠረት በእነዚህ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ መከላከልን መምረጡን ዶክተር ኩሙዛ ይናገራሉ።

“የጤና ፕሮግራሙ መሠረታዊ አካሔድ መከላከል ይህም አዋጭ፣ ተደራሽና ብዙ መዘዞችንም የሚያስቀር ነው” ሲሉ ገልጸውታል። 

አያይዘውም “ኢትዮጵያ በመከላከል ደረጃ የተሻለ አቅም ይኖራታል። የጤና አገልግሎት ዝርጋታውን ስናይ የመጀመሪያ ደረጃ የሚባል ሕክምና የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎች 4 ሺሕ ሲሆኑ በጠቅላላው ያሉ ሆስፒታሎች ከ400 በላይ አይደሉም። በአንጻሩ 16 ሺሕ የጤና ኬላዎች አሉ። ይህም ማለት ማንኛውም ጤና ነክ መልዕክት በእነዚህ መዋቅሮች መድረስ ይችላል ነው። ይህን አጋጣሚ መጠቀም ከቻልን በሽታዎቹን ቀድሞ ለመከላከል እንዲያስችል ኅብረተሰቡ ጋር መድረስ ይቻላል፣ ማሻሻል የሚያስፈልገውና የሚጠበቀው መልዕክቱን ማቀናበርና የማኅበረሰቡን ዕድሜ፣ ጾታ፣ አረዳድ፣ አኗኗር ሁኔታ፣ ባሕልን ያገናዘበ አድርጎ ማዘጋጀት ነው።” ብለዋል

ከእነዚህ በሽታዎች ጋር በተያያዘ የሙያና የበጎ አድራጎት ማኅበራት ድጋፍ ምን ይመስላል ስትል አዲስ ዘይቤ ጥያቄ አንስታለች። የኩላሊት ሕመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ማኅበር የኩላሊት ሕመምተኞች የቀዶ ጥገና ዕድል እስኪያገኙ ድረስ ሕይወታቸውን ለማቆየት የእጥበት አገልግሎትን በነጻ ለመስጠት የሚጥር ማኅበር መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን እስካሁን ባለው ሂደት በምኒልክ የኩላሊት እጥበትን ሙሉ ለሙሉ ነጻ ማድረግ መቻሉም ይታወቃል። 

የማኅበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ፤ ኩላሊትን በተመለከተ መንግሥት ትንሽም ቢሆን ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው “የመንግስትን ትኩረት በሚፈለገው ልክ እስክናገኝ ድረስ የኩላሊት እጥበት በጎ አድራጎት ማኅበርን ጨምሮ በሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የሚሠሩ ማኅበራት መግፋት አለባቸው።” ብለዋል። የኩላሊት እጥበትን መነሻ አድርገው ሲጠቅሱም፤ በፊት አገልግሎቱ አዲስ አበባ ላይ ብቻ እንደነበርና፤ አሁን በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እጥበት እንደሚሰጥ እና ይህም የማህበሩ ስኬት አንድ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።

“እንደኛ ያሉ ማኅበራት ከመንግሥት የሚፈልጉት አንዱና ቀዳሚው ነገር ግብዓት ነውና ይህን መንግሥት ማሟላት አለበት” ይላሉ ሰለሞን። አክለውም “ለስኳር በሽታ እንደሚደረገው ሁሉ ለኩላሊት ሕመምተኞችም በተለይም አቅም ለሌላቸው በየሆስፒታሉ ነጻ ማድረግ፤ መድኀኒቶቹ ውድ በመሆናቸው አቅም ለሌላቸውና መግዛት ለማይችሉት ነጻ መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል። 

በሌላ በኩል ማህበር ተመስርቶ በአቅም ማጣት የቆመ እንዳለም መመልከት ይቻላል ለዚህም ማሳያ ሚሆነው በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ውስጥ በዶክተር በላይ አበጋዝ ማነሳሳት ተቋቁሞ በአቅም ማጣት ቆሞ የነበረው እና አሁን ላይ በህዝብ ድጋፍ እየተንገዳገደ የሚገኘው የህፃናት የልብ ህሙማን ማህበር ነው። “ሰዉ ያለውን በማዋጣት ሕክምና ማዕከሉ ዳግም እንዲቆም ጥረት ቢደረግም ዘላቂ ገቢ ማስፈለጉ ግን ግልጽ ነው። አለበለዛ እነዚህን ተስፈኛ ህፃናት ዳግም የሚሰብር ክስተት መከሰቱ አይቀርም” ያሉት ዶክተር በላይ አበጋዝ ናቸው። 

“ታድያ እነዚህን ህመሞች ለመቆጣጠር ምን መፍትሄ ይደረግ?” ስትል አዲስ ዘይቤ ጠይቃ ዶክተር ኩኑዝ  “እነዚህን በሽታዎች መንግሥት በጤና ሚኒስቴር በኩል ብቻ መፍትሔ ሊሰጣቸው የሚችለው አይደለም። ይልቁንም የሲቪል ማኅበራት፣ ኅብረተሰቡ፣ የተለያዩ አጋር ድርጅቶችና እያንዳንዱ ቤተሰብም ራሱ መሳተፍ መቻል አለባቸው። ጉዳዩ ፈርጀ ብዙ ምላሽ ይፈልጋል ስለዚህ አጋላጭ የተባሉት መንስዔዎች ከጤናው ዓውድ በላይና ውጪ በመሆናቸው የሚመለከተው ሁሉ መሳተፍ ይኖርበታል” ሲሉ መልሰዋል። 

እንደማሳያም የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በተመለከተ ከስፖርት ጋር በተገናኘ የሚንቀሳቀሱ ባለድርሻ ተቋማት፣ ትምህርት መስጠት ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ታች ድረስ በሚወርድ መዋቅሩ፣ በአመጋገብ ዙሪያ ግብርና እና ምግብ ላይ የሚሠሩ የሚመለከታው በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ተቋማት ወዘተ ቅንጅታቸው አስፈላጊ ነው በማለት በጤና ሚኒስቴር በኩል ደግሞ ምላሹን ለመስጠትና መከላከል ላይ እንዲያተኩር ለማስቻል ሁሉም የየራሱን ሚና የሚወስድበት የትብብር እቅድና ስልት እየተዘጋጀ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

ፕሮፌሰር ሽታዬም በበኩላቸው፤ ስለ በሽታዎቹ መነሻና አጋላጭ ሁኔታዎች ከታችኛው የዕድሜ ክልልና ትምህርት ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ግንዛቤ እንዲኖር በየደረጃው ማስተማር ያስፈልጋል ብለዋል። መልዕክቶቹም እንቅስቃሴ አድርጉ፣ ጣፋጭ አታብዙ፣ ኮምፕዩተር ላይ ብዙ አትቀመጡ ከማለት ጀምሮ ሳይንሳዊ መንገድን በማሳየትና በማስተማር ጭምር መሆን ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል።

 “የሚያስፈልገው ማስተማር ነው። ማስፈራራትና  ማባበል ጊዜ አልፎበታል” ይላሉ።

አስተያየት