የድል ጀንበር የጠለቀችበት ወታደራዊው መንግሥት ሲፈረካክስ፣ 17 ዓመታትን በትግል ያሳለፉት 4 ኪሎን ሲቆጣጠሩ፣ ስለ ጦርነት መስማት ያንገሸገሸው የሀገሬው ህዝብ እፎይ እንዳለ፣ የሽግግር ቻርተሩ ጸድቆ አዲስ የክልል አወቃቀር ይፋ ሲሆን፣ ያኔ ኢትዮጵያ በ14 ክልሎች ተደራጀች። ከትግራይ 1 ብሎ የሚጀምረው አደረጃጀቱ አዲስ አበባን 14ኛ አድርጎ ይጠናቀቃል። አዲስ አበባ እና ድሬዳዋም እንደ ክልል እውቅና ነበራቸው። የቁጥር ክለላውን ተከትሎ በመጣው ክልላዊ አደረጃጀት “የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ውስጥ የሚገኙ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች አምስት የተለያዩ ክልሎች ነበሩ። ይህንን መሰሉ አደረጃጀት የቆየው ለሁለት ዓመታት ብቻ ነው። የወቅቱ የሽግግር መንግሥት አባል ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት በመጣ ደብዳቤ ክልላዊ አወቃቀሩ በሌላ አዲስ አወቃቀር እንደተተካ ያስረዳሉ። እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ “ማዕከላዊው መንግሥት ክልሎች የተዋቀሩበትን አዋጅ 7/1984ን ጥሶ አምስቱን ክልሎች ጨፍልቆ አዋህዷቸዋል። 110ሺ ካሬ ኪ.ሜ. የሚሸፍነውና 55 ብሔር ብሄረሰቦችን ያቀፈው የአሁኑ “የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል” ከሌሎቹ 9 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች መካከል እንደ አንዱ ሆኖ ቀጠለ።
ወንድማማቾቹ የስማቸው ልጆች ሀብታሙ እና ተሰማም በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሐሳብ ይስማማሉ። “The Procedure for the Creation of New Regional State under FDRE Constitution” በተሰኘው የጋራ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ሕግ ተጥሶ የተመሰረተው ክልል ለአስተዳደር ምቹ ሆኖ አልዘለቀም። ከፍ ሲል ግጭቶች እና አለመግባባቶች ዝቅ ሲል ጥያቄዎችና ክርክሮች ሲያስተናግድ ቆይቷል።
ቋንቋን መሰረት ያደረገው አከላለል ፊቱን ወደ ደቡብ ሲያዞር መልክአ ምድራዊ እና የአስተዳደር ምቹነትን በመተግበሩ የሰላ ትችት ከማስተናገድ አላመለጠም። ከፍ ያለ የሕዝብ ቁጥር ያላቸው እንደ ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ እና ያሉ ብሔረሰቦች ደግሞ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄአቸውን ሲያቀርቡ ሁለት አስርት ዓመታት አልፈዋል።
“ጥያቄአችን ሕገ-መንግሥታዊ ድጋፍ አለው” ሚሉት እነኚህ አካላት፣ የታሪክ፣ የባህልና የአካባቢ ዝምድና ከሌላቸው ሌሎች ብሄሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር መቀላቀላቸው በመሰረተ ልማት እና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ ኋላ እንዲቀሩ ቀዳሚ ምክንያት እንደሆነ ያስቀምጣሉ። የሕዝብ ብዛታቸው አነስተኛ የሆነ ብሔረሰቦች ደግሞ የውክልና ጥያቄ ያነሳሉ። ለዚህም እንደማስረጃ እስካሁን የክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩ ግለሰቦች የመጡበትን ብሔር ይጠቅሳሉ። ከክልሉ ምስረታ ጀምሮ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ያገለገሉት አመራሮች ከሲዳማ እና ከወላይታ ብሔረሰቦች የተገኙ ናቸው።
ሀገሪቱ እየተከተለች የሚገኘውን ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም የሚተቹ አካላት በበኩላቸው የዞኖቹ የክልልነት ጥያቄ ማንሳታቸውን አይቀበሉም። የዚህ ሐሳብ አራማጆች የደቡብ ክልል የገባበት ውጥረት ሕገ-መንግሥታዊ ድጋፍ ያለው ብሔርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ኢትዮጵያን እስከ መበተን የማድረስ አቅም እንዳለው በማሳያነት ያቀርቡታል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አህመድ ወደሥልጣን ሲመጡ ጠረጴዛቸው ላይ ከጠበቋቸው ሲንከባለሉ የመጡ መልስ ፈላጊ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የክልልነት ጥያቄ ነው። በየክልል ምክርቤቶቻቸው ጸድቀው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚላኩት “በክልል እንደራጅ” ይያቄዎች በርክተው፤ የሁሉም ችግሮች መፍቻ ቁልፍ ክልል መሆን እስከመሆን ደርሶ ነበር። ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጀመሪያዎቹ 100 ቀናት የሥራ ዘመናቸው በተዘዋወሩባቸው ክልሎች ተደጋግመው የተነሱላቸው ጥያቄዎችም ከክልልነት ጋር የተያያዙ ነበሩ። የወሰን መካለል፣ የግዛት ይገባኛል ጥያቄዎችም በተከታይነት ይቀመጣሉ።
ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌና ሌሎች ዞኖች የክልልነት ጥያቄውን አጥብቀው ገፉበት። በተለይ በመንግሥት የተለሳለሰ ምላሽ የተቆጡት የሲዳማ ወጣቶች ለ11/11/2011 ቀን ቆጥረው አደባባዩን በማጥለቅለቅ ቁጣቸውን ገለፁ።
የሪፈረንደም ጥያቄን የሚያስተናግደው የምርጫ ቦርድ በአዲሱ አመራር ስር ነቀል ለውጥ ላይ ነበር። የመጀመርያ ፈተናውም የሲዳማን ሪፈረንደም ማስተናገድ ሆነ። ከፊት ለፊቱ ሀገራዊ ምርጫን አስቀምጦ የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ህዝበ ውሳኔ አከናወነ። ከረዥም ዓመታት መጓተት በኋላ 10ኛው ክልል ተወለደ። ሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ይፋ ሆነ።
ኢህአዴግን ከመሰረቱ ከአራት አውራ ፓርቲዎች ሦስቱ ራሳቸውን ወደ ብልፅግና ፓርቲነት ሲያዋህዱ፤ ደኢህዴንም ብልጽግና ተብሎ መጠራት ሲጀምር በክልሉ የሚገኙ ዞኖች የሚቀነቀኑ የክልልነት ጥያቄዎች ለመመለስ ያቀረበው ሦስት ምክረ-ሀሳብ ወደጎን ተወረወረ። በምትኩ “የሰላም አምባሳደር” የሚል መጠሪያ የያዘ አንድ ቡድን የመፍትሄ ሀሳብ ለማቅረብ ላይ ታች ሲል ሰነበተና ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ቡድኑ ደረስኩት ያለውን መደምደሚያ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀረበ።
80 አባላትን የያዘው “የሰላም አምባሳደር” የሚሰኝ ቡድን በጥናቱ ማጠቃለያ ደቡብ ክልለን ወደ አራት ክልሎች መበተንና አንድ ልዩ ዞን መመስረት መፍትሄ ነው ሲል ገለፀ።
- ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ እና ኮንሶ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል ማለትም ኦሞቲክ ክልል ተብለው እንዲደራጀጁ
- ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ የም፣ እና ሀላባ አንድ ላይ ሁለተኛ ክልል ሲሆን ሲዳማን ለብቻው ሦስተኛ ክልል ያደርጋል።
- አራተኛው ክልል ደግሞ ከፋ፣ ቤንች፣ ሸካ እና ዳውሮን አንድ ላይ ይሰበስባል። ጌዲኦን ልዩ ወረዳነት እንድትደራጅ ሐሳብ የሚያቀርበው ጥናቱ የወላይታን ጉዳይ በዝምታ አልፎታል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት 1 ዓመት የተራዘመው 6ኛው ሐገራዊ ምርጫ ያልተከናወነባቸው አካባቢዎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ተወካዮቻቸውን መርጠዋል። ከምርጫው ጎን ለጎን አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ የህዝብ በውሳኔ ያካሂዳሉ። ዞኖቹ በደቡብ ክልል ስር መቀጠላቸውን ወይም ራሳቸውን ችለው መደራጀታቸውን የሚወስነው ሕዝበ ውሳኔ ቀጣዩን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚወስን ወሳኝ ጥያቄ ይልሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እጣ የ”ሰላም አምባሳደሮቹ” ባቀረቡት የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት እየተጓዘ እንደሆነ ያሳያል። እጣ ፈንታው ያልታወቀው የወላይታ ዞን እና በአምባሰደሮቹ ሀሳብ በአንድ እንዲሰባሰቡ የተወሰነላቸው ዞኖች ቀጣይ እርምጃ ደቡብ ክልልን ታሪክ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ያደርገዋል። አሁን የቀረው ጥያቄ ተረኛው ማነው? የሚለው ብቻ ይሆናል።