ኢሬቻ ያነቃቃው የፋሽን ኢንደስትሪ ባህሉን እየጎዳው ይሆን?

Avatar: Tesfalidet Bizuwork
ተስፋልደት ብዙወርቅመስከረም 19 ፣ 2014
City: Adamaባህል ኢኮኖሚቱሪዝም
ኢሬቻ ያነቃቃው የፋሽን ኢንደስትሪ ባህሉን እየጎዳው ይሆን?

“መሬዎ… መሬዎ” በሚል ሕብረ ዜማ ታጅቦ፣ እርጥብ ሳር እና አደይ አበባ ተይዞ በየዓመቱ የሚከበረው ኢሬቻ ሁሉም ሰው በአቅሙ አምሮና ደምቆ የሚታይበት የአደባባይ በዓል ነው። በኦሮሞ ባህል ክረምቱን ያሳለፈ፣ ባህሩን የሞላ፣ ተራራውን ያለመለመ ፈጣሪ የሚወደስበት “የምስጋና ቀን” በትዕይንተ ሕዝብ ይደምቃል። ባሕላዊ እና ስነ-ማኅበረሰባዊ ወጉን ጠብቆ የመስቀል በዓል በዋለ በሳምንቱ በሚኖሩ ቅዳሜ እና እሁዶች የሚከበረው ኢሬቻ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፋሽን አልባሳት ዲዛይነሮችን ቀልብ እየሳበ መጥቷል።

መስከረም 15 እና 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የተዘጋጀው “የኢሬቻ ፋሽን ትርኢት እና የባህል ፌስቲቫል” ለዚህ እንደማሳያ ሊወሰድ ይችላል። በአዳማ ከተማ ኦልያድ ሲኒማ ግቢ ውስጥ በተከናወነው በዚህ ዝግጅት ላይ 10 ዲዛይነሮች እና 40 ሞዴሎች ተሳትፈዋል። አልባሳት፣ ሙዚቃና ውዝዋዜዎች፣ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ለሽያጭ የቀረቡበት ዝግጅት ኢሬቻ ለፋሽን ኢንዱስትሪው እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ እንደሆነ ተነግሮለታል። ከዝግጅቱ ቀን ቀደም ብሎ መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የአዳማ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአሜን ሞዴሊንግ አካዳሚ ጋር በመተባበር ከተማዋን ወክለው ለሚስ ቱሪዝም ኦሮምያ የሚቀርቡ ሦስት እጩዎችን መርጧል። በወቅቱ የአሜን ሞዴሊንግ ት/ቤት መምህር አቶ አማኑዔል ንጉሤ “ይህ ዓይነት ውድርር በዓሉን ማስተዋወቁ ትልቁ ውጤቱ ሲሆን ለሞዴሊንግም ሆነ ለፋሽን ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትም ይፈጥርልናል።” የሚል ንግግር አሰምተዋል።

ቱባው ባህል መነካት የለበትም የሚሉት የባህል ተቆርቋሪዎች ዘንድ ብርቱ ሙግት የገጠበው፤ በአፍላ ወጣቶች እና የፋሽን ኢንዱስትሪው ተዋናዮች በኩል እየተረታታ የሚገኘው የኦሮሞ ባሕላዊ አልባሳትን የማዘመን ሥራ ተመልካቹን ለውይይት እየጋበዘ በዘመን ሐዲድ ላይ እየተጓዘ ይገኛል። የዘመኑት አልባሳት ለአደባባይ ከሚቀርቡባቸው የመታያ በዓላት መካከል ኢሬቻ አንዱ፣ ምናልባትም ዋነኛው ነው።

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር በአዳማ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የአልባሳት እና ጌጣጌጦችን ገበያ ተመልክቷል። ከገበያተኞች እና ከነጋዴዎች እንደተረዳው የዘንድሮው የግዢና ኪራይ ዋጋ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በአዳዲስ አልባሳት በኩል በተለያየ መልክ የተዘጋጀ ከላይ ከሚለበስ እስከ ሙሉ ልብስ ድረስ ከብር 2 ሺህ እስከ 20 ሺህ ድረስ ይገኛል። በኪራይም ከ1 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 3 ሺህ ይገኛል። ለዋጋው መጨመር የፍላጎት መጨመርና የጥሬ እቃ መወደድ በምክንያትነት ቀርበዋል።

ለተከታታይ አራት ዓመታት በሆራ ሰርገዴ ተጉዞ ኢሬቻን እንዳከበረ የሚናገረው አቶ ደሳለኝ ዓለሙ “የፋሽን እድገቱ አስደናቂ ነው” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል። ባለፈው ዓመት ከአራት ጓደኞቹ ጋር ተመሳሳይ ልብስ በማሰፋት ደምቀው ማሳለፋቸውን ያስታውሳል። “የፋሽኑ መስፋፋት ባህልን ከማስተዋወቅ ባሻገር ወጣቶች ባህላቸውን እንዲወዱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድረጓል” የሚለው ወጣቱ የበዓሉ ሕዝባዊነት ወደሌሎች አካባቢዎችም ተስፋፍቶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያከብረው እንዲሆን ያለውን ሐሳብ አጋርቶናል።

የኬቲ ፋሽን ባለቤት አቶ ዘሩ ዓለማየሁ ኢሬቻ በአልባሳት ሽያጭ እና ዲዛይን ሥራ ላይ የሚታይ ለውጥ ስለማምጣቱ ይናገራል። “በበዓሉ ዕለት ደምቀው ለመታየት የሚሆኗቸውን አልባሳት የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በማሻቀቡ ትዕዛዝ መቀበል አቁመናል” ብሎናል።

ባህላዊ አልባሳት በአዳዲስ ዲዛይኖች በዘፈቀደ እንዲዘምኑና የቀደመ ይዘታቸውን እንዲለውጡ መደረጋቸው ጥንቃቄ የሚጠይቅ ተግባር ስለመሆኑ አብዛኞችን ያስማማል። የዚህ ሐሳብ አራማጆች ከሚያነሷቸው ነጥቦች መካከል የልዩ ልዩ ባህሎችን (አካባቢዎችን) አለባበስ መቀላቀል፣ በሽመና ወቅት የቀለም ድርድሮችን ወይም መስመሮችን ማዛባት፣ የጥራት ደረጃን ማሳነስ ወይም ከባህሉ ውጭ ያሉ ጨርቆችን መጠቀም፣ በአጊያጊያጥ ወይም አለባበስ ላይ ያለውን ባህላዊ ስርአት ማፋለስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በኦሮሞ ባህል ውስጥ የባሌ፣ የአርሲ፣ የቦረና፣ የጉጂ፣ የሐረርጌ፣ የጅማ እና መሰል አካባቢዎች የተለያዩ የአልባሳት ዐይነቶች አሉ። እነኚህ የራሳቸው መገለጫ ያላቸው አለባበሶች ሲዘምኑ የቀደመ ታሪካቸውን ባልለቀቀ መልኩ መሆን አለበት ከሚሉት እና ከአንድ በላይ በሆኑ አካባቢዎች የሚለበሱትን አቀላቅሎ በፋሽን መልክ ማምጣት አደጋ እንዳለው ከሚያስቡ ሰዎች መካከል ሲፈን ንጉሤ አንዷ ነች።

“የተለያዩ አካባቢ አልባሳት በአንድ ተሰርተው ወይም በቲሸርት እና በሱሪ አልያም በቀሚስ እና በጋዋን ሲለበሱ እመለከታሁ።” የምትለው ሲፈን ድርጊቱ ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳትም ሊኖረው እንደሚችል ትናገራለች።  

“በአዲስ ዲዛይን አዲስ ውበት መፍጠሩ ጥሩ ጎኑ ነው። ለየት ማለቱ ውበትም አለው። በወጣቶችም ይወደዳል። የምሰጋው የባህል መዘበራረቅን እንዳያስከትል ነው።" ትላለች። "አልባሳቱ ተዳቅለው ሲዘጋጁ አንዱ የአንዱን እንዳይውጥ እና የቀደመውን ‹ኦርጅናል› ባህል እንዳያጠፋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል" ስትል አስተያየቷን ደምድማለች።

የኬቲ ፋሽን ባለቤት አቶ ዙሩ ዓለማየሁም በሲፈን ሐሳብ ቢስማማም ችግሩ የ”ዲዛይነሮች ብቻ አይደለም” ይላል። የተለያዩ ባህሎችን የመቀላል፣ የሚታወቁ የቀለም አደራደሮችን ማዛባት እና መቀየር፣ ከደረጃቸው በታች የሆኑ ጥለቶች የመጠቀም (sublimation) ስራ መመልከቱን እና ይህም ዋናውን ባህል በጊዜ ሂደት የማጥፋት አደጋ እንዳለው ያምናል። እንደ አቶ ዘሩ ገለጻ አብዛኛዎቹ አልባሳት በደንበኛው ትእዛዝ እና ፍላጎት ላይ ተመስርተው የሚዘጋጁ በመሆናቸው ሁለቱም ወገን የብልሽቱ ተጠያቂዎች ናቸው።

የሲመን ዲዛይን ባለቤት እና ዲዛይነሯ ሀንጋቱ ሙሳ ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበራት ቆይታ “አብዛኞቹ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት በሞቃት ቀለማት እና በጠንካራ ድግግሞሽ (Pattern) የሚሰሩ ስለሆነ እጅግ ዘምነው መሰራታቸው ባህሉን ለማተዋወቅ እጅግ ከፍተኛ አበርክቶ አለው። ተጠቃሚዎች የአንድ ቀን ልብስ አድረገው ስለሚያስቡ ከጥራቱ በላይ ዋጋው ላይ ያተኩራሉ። ይህን ለማስተካከል በተሻለ ጥራት እና ሁሌም መለበስ የሚችሉ ልብሶችን እያዘጋጀን ነው” የሚል ሐሳብ ሰንዝራለች። በመደምደሚያዋም በተጠቃሚዎች ዘንድ ከተደጋገመ ዲዛይን ይልቅ አዳዲስ ስታይሎችን እና ዲዛይኖችን ከባለሞያው መቀበል መለመድ እንዳለበት ትናገራለች።

“በኦሮሞ ባህል “ሰፉ” አለ” ሚለው ደግሞ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች የኦሮሞ ባህል አልባሳትን ፎቶዎች በማጋራት የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሳምሶን አንተነህ ነው። “ሰፉ ማለት በባህሉ መሆን የሚፈቀድ እና የተከለከለ ተብሎ ባጭሩ መገለጽ ይችላል። ከባህል አልባሳት ጋር ብቻ ሳይሆን በእጅ ከሚያዙ እንደ ቦኩ፣ ሲንቄ፣ ጀምሮ እስከ ጌጣጌጦች ድረስ ሰፉ ሲጣስ ይታያል። ይህንን ለማስተካከል የራሱ መንገድ አለውና ወጣቶችን እና ዲዛይነሮችን ማስተማር ያስፈልጋል። ሰፉ ተጠብቆ ፋሽኑን ማሳደግ ከታሰበበት አይከብድም”

ይህ በባህል ተቆሮቋሪዎች እና አልባሳቱ  እንዳይዘምኑ ባህል ለጉሞ ይዞታል  በሚሉ መሀከል ያለው ክርክር በማህበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ መንገዶች ቀጥሏል። የዘንድሮ ኢሬቻ ቅዳሜ መስከረም 22 በሆራ ፊንፊኔ እሁድ መስከረም 23 በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሊከበር በጉጉት እየተጠበቀ ነው። አዲስ ዘይቤም መልካም በዓል ይሆን ዘንድ ከወዲሁ ተመኘን።

Author: undefined undefined
ጦማሪተስፋልደት ብዙወርቅ

Tesfalidet is Addis Zeybe's correspondent in Adama.