ነሐሴ 5 ፣ 2013

“ቴራ” የተሳካው ወንጀልን በባህላዊ መሐላ የመቀነስ መላ

City: Assosaባህል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምትገኘው ወንበራ ወረዳ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወንጀልን ለመከላከል የሚጠቀምበት “ቴራ” የተባለው ባህላዊ ክዋኔ በአካባቢው በሚገኝ ሰፋ ያለ ሜዳ ላይ ሁሉም በተገኘበት እና ስርአት ባለው ሰልፍ የሚደረግ ነው።

 “ቴራ” የተሳካው ወንጀልን በባህላዊ መሐላ የመቀነስ መላ

የወንበራ ወረዳ የተቆረቆረቆረችው ከጥንት የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር እንደሆነ ታሪክ ይናገራል፡፡ እንደ ደብረማርቆስ እና ጎንደር ያሉት ከተሞች እኩዮቿ ናቸው፡፡ ወንበራ ስያሜዋን ያገኘችው በንጉሥ ተክለኃይማኖት ዘመን ነው፡፡ የታሪክ መዛግብት እንደሚያብራሩት ከፍ ያለው የመልከአ ምድሯ አቀማመጥ በዙርያዋ ያሉ አብዛኛዎቹን ቀበሌዎችን ለመመልከት ስለሚያስችል “ይህቺማ ልክ እንደ ወንበር አይደለች እንዴ?” ከሚለው የንጉሡ ንግግር በኋላ ወንበራ የሚለውን ስያሜ አግኝታለች። 

የወንበራ ወርዳ ከባህር ጠለል በላይ ከ1,200 እስከ 1,500 ሜትር ከፍታ ላይ ትገኛለች፡፡ የአየር ንብረቷም ደጋማ ነው። የዛሬው የወንበራ ከተማ ስያሜ “ደብረዘይት” ነው፡፡ ምንም እንኳን እድሜ ጠገብ ከተማ ብትሆንም የቀደምትነቷን ያህል እድገት ያላስመዘገበች ስለመሆኗ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ለዚህም በምክንያትነት ከሚዘረዘሩ ጉዳዮች ውስጥ የመልከአ ምድሯ አለመመቸት በዋነኝነት ይነሳል፡፡

ወንበራ ወረዳ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ ትገኛለች፡፡ ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ የተነሳ ተጓዥ ወንበራ ለመግባት የአንድ ቀን ተኩል ጉዞን ማጠናቀቅ ግድ ያለዋል፡፡ የአዲስ ዘይቤ አሶሳ ሪፖርተር በደብረ ዘይት ከተማ ተገኝቶ የአካባቢው ማኅበረሰብ ወንጀልን ለመከላከል የሚጠቀምበትን “ቴራ” የተባለውን ባህላዊ ክዋኔ ተመልክቶ  ዘገባ አሰናድቷል። 

የስርአቱ ድባብ

ስርአቱ የሚከናወነው በአካባቢው በሚገኝ ሰፋ ያለ ሜዳ ላይ ነው፡፡ አንድ ገበያ የሚሆን ነዋሪ በታዳሚነት በስፍራው ይገኛል፡፡ የሃገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ የእድሜ ባለጸጎች፣ ሴት ወንድ ሳይለይ ነጭ ጋቢያቸውን ደርበው ተሰብስበው ይታደማሉ፡፡ ሁሉም ስርአት ባለው ሰልፍ ተራቸውን ይጠብቃሉ። ከፊትለፊታቸው ሁለት ራቅ ራቅ ብለው የተደኮኑ ዳሶች ይታያሉ። በአንዱ ድንኳን ውስጥ አምስት ሽማግሌዎች በአንዱ ደግሞ አራት ሽማግሌዎች ይገኛሉ። ተራቸውን ጠብቀው ወደ መጀመርያው ዳስ ይገባሉ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች ቆይታ በኋላ ደግሞ ከገቡበት ዳስ ወጥተው ወደሌላኛው ዳስ ይገባሉ፡፡ በዚያም እንዲሁ ከተመሳሳይ ቆያታ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ።

መሐላ

ባህላዊ ክዋኔውን ከዳር ቆመን ዕየተመለከትን ነው፡፡ ከአፍታ ጥበቃ በኋላ ከሁለተኛው ዳስ አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ 80 ዓመት የሚገመቱ አዛወንት በቀኝ እጃቸው ጦር እና ሌሎች የስርዓቱ ማስፈፀምያ ቁሳቁሶች ማለትም ገመድ፣ የከፈን ጨርቅ፣ ቃሬዛ፣ አፈር፣… የመሳሰሉትን እንደያዙ ወደ ተጠለልንበት መጡ። የተቀላቀሉን ስነ-ስርአቱ በመጠናቀቁ የሆነውን ነገር እንዲያብራሩልኝ ባቀረብኩት ጥያቄ መሰረት ነው፡፡ ቀዳሚ ጥያቄዬ “በሁለቱ ድንኳኖች ውስጥ ምን ተከናወነ?” የሚል ነበር፡፡ በአጭሩ “መሐላ” የሚል ምላሽ ሰጡኝ፡፡

አግራሞቴን ተመልክተው ድሮን ከዘንድሮ በማነጻጸር እንዲህ አሉ፡፡ “በእኛ በአባቶቻችሁ ዘመን አርብቶ አደሩ ከብቶቹን፣ ፍየሎቹን፣ በጎቹን እንዲሁም ያለውን ከብት እና ንብረት ያለምንም ስጋት በየሜዳው ያለ ጠባቂ ነበር የሚያሳደረው፡፡ በየግጦሹም እንስሳቶቹን የሚያሰማራው ያለ እረኛ ነበር። ነጋዴውም እንዲሁ ሱቄ በሌባ ይዘረፋል ብሎ አይሰጋም። ከሰው ጋር ቂም ያለውም ሳይሰጋና እና ሳይፈራ የዕለት ተዕለት ስራውን እንደማንኛውም ጊዜ ያከናወናል። በአጠቃላይ ሰው መገደል፣ ስርቆት እና ሌላም ወንጀል አለ ለማለት አያስደፍርም። በአሁኑ በእናንተ ዘመን ላይ ስንደርስ ደግሞ ያ የድሮው ነገር ተለወጠ። ተቃራኒ ሆኖ አገኘነው፡፡ የነጋዴው ሱቅ ቀን በቀን ይዘርፋል። በግ፣ ፍየል እና ከብት ከበረት ይወሰዳል፡፡ ዘራፊው እንደራሱ ንብረት አርዶ ይበላል፣ ገበያ ወስዶ ይሸጠዋል፡፡ በየቀኑ፣ በየመንገዱ ሰው ይገደላል። አንዱ የሌላውን ሃብትና ንብረት ይመኛል። ሴቶች ይደፈራሉ። ባህላዊ መድሀኒት በመጠቀም ወንጀል ይፈፀማል፡፡”

የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ካብራሩበት ሰፋ ያለ ንግግራቸው በኋላ ድሮ ሲሉ በሰየሙት የጉብዝናቸው ዘመን ያልነበረውን በእርጅናቸው ወቅት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት የሄዱትን ርቀት አብራሩልኝ።

“እንግዲህ እንዲህ እየተደራረጉ እነዚህ የምትመለከተው ህዝብ በሙሉ እስከመቼ ይኖራል? አንዱ የሌላውን ሃብት እየቀማ እስከመቼ መኖር አለበት? እንግዲህ አንተም መመስከር ትችላለህ፡፡ እነዚህ ወንጀሎች በሀይማኖትም ይሁን በሕግ አይፈቀዱም፡፡ ታዲያ እኛም በወረዳዋ ያለን የሃገር ሽማግሌዎች ይህንን አብሮን ያልኖረውን የወንጀል ድርጊት ለማስቀረት ከመሞታችን በፊት ተከላከለን ህዝቡ ያለ ስጋት መኖር አለበት ብለን በመመካከር ይህንን የምታየውን ሁሉንም ብሄረሰቦች የሚወክል፣ የአባቶቻችንን ባህላዊ የመሀላ ስርዓት ዳግም በማምጣት ይህንን ዛሬ የምታየውን ማከናወን ጀመርን። ተግባራችን በክልሉ መንግሥት እውቅና አግኝቷል፡፡”

አተገባበር

“ከሦስት ብሔር ብሔሰቦች የሐገር ሽማግሌዎች መርጠን ሁሉንም ብሄሮች እንዲወክሉ ተደርገ። ሽማግሌዎቹ የተመረጡት ከአማራ ከኦሮሞ እና ከሺናሻ ብሔረሰቦች ነው። ሦስቱም ብሔረሰቦች የየራሳቸው የመሀላ ስነ-ስርአት ቢኖራቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች አበዛኛዎቹ የሺናሻ ብሔረሰቦች ስለሆኑ እና የወንጀል ድርጎቱ በብዛት እየተስተዋለ ያለው በዚህ ማኅበረሰብ ውስጥ በመሆኑ የሺናሻ ብሔረሰብ ውስጥ “ቴራ” በመባል የሚታወቀውን የመሃላ ስነ-ስረዓት ህዝቡ እንዲሚል ወሰንን።

በዚህ ዙሪያ ላይ ህዝቡን አሰባሰበን ከተውያየን በኃላ ሁሉም ተሰማማ። እኛም የሀገር ሽማግሌዎቹም በህዝቡ ስምምነት መሰረት ቅስቀሳ በማድረግ የሰማው ላልሰማው እንዲያደርስ በማድረግ ስራችንን ጀመርን፡፡ ቀጥሎ ያደረግነው ታች ያለው ሕብርተሰብ ማለትም በቀበሌው እና በመንደር ወስጥ ያሉትን ነዋሪዎች ቅደሚያ ሰጥተን የሃገር ሽማግሌዎች ቡድን ወደ እሱ በመውረድ ሁሉም ሰው ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ሲት እና ወንድ፣ አዲስ የመጣም ይሁን ነባሩ ሰው ሳይቀር በስነ-ስርዓቱ መሰረት መሃላውን አስፈጸምን። ከዚያም በመቀጠል ወደ ወረዳዋ ዋና ከተማ በመምጣት በተመሳሳይ ሁኔታ አንደም ሰው ሳይቀር ተመዝግቦ የመሃላ ስረዓቱን በመከተል መሃላ ፈፀምን። በወቅቱ እያወቀ የቀረ እና ቀርቦ ያልማለ ሰው ቢገኝ ተጠርጣሪ እንደሚሆን እና ከፍተኝ ቅጣት ከዚያም አልፎ በሽማገሌዎቹም እንደሚረገም እና ከሕብረተስቡ ውስጥ የተገለለ እንደሚሆን የሚያስረዱ ሕጎችን አውጥተን በመናገር ቀጣዩን የመሀላ ስርአታችንን በወረዳዋ ዋና ከተማ አደርግን።”

አስፈላጊ ቁሳቁሶች

እንግዲሀ በዚህ የመሀላ ወቅት የሚያስፈልጉን በርካታ ባህላዊ ክዋኔዎችና ባህላዊ ቁሳቁሶች አሉን። እነርሱም ባህላዊ የሺናሻ ብሄረሰብ ጦር፤ “ከርዊየሚባል በአንገት የሚደርግ ገመድ፣ አፈር፣ ሁለት የሬሳ መሸካሚ ቃሪዛ፣ የሬሳ መከፈኛ አቡጀዲ ጨርቅ እና ሌሎች ተጨማሪ ነገሮችን በመያዝ ህዝቡን ወደዚህ ሰፊ ሜዳ ጠራን።

ከዚያም ለመሃላ የሚመጣው ሰው ራቅ ብላ ወደ ምትገኘው የመጀመሪያ ዳስ ውስጥ ተራውን እየጠበቀ ይገባል። ይህ የመጀመርያው ክፍል የራሱ ደርሻ አለው። ተረኛው ሰው በመጀመርያ የሚጠየቀው ጥያቂ በዚህ ክፍል ውስጥ ነው። የተንኮል የሌብነት ስራ እና ሌሎችንም ወንጀሎች ሰርቶ የሚያውቅ ከሆነ በታማኝነት እራሱን እንዲያጋልጥ ይደርጋል። ከዚህም የሰራቸውን ከፋቶችንና ወንጀሎችን ሰርቶ የሚያውቅ ከሆነ ወንጀሎቹ መቼ? የት? በማን? ለምን? የሚሉ ጥያቂዎች ተጠይቆ ምላሽ ሲሰጥ ይመዘገባሉ።

የነበሩትን ነግሮች አምኖ ከተናገረ እና ተንኮል በሰው ላይ ሰርቶ የሚያውቅ ከሆነ ወደ ፊት እነዚህን ነገሮች እንደማይሰራ እና ሌላም ሰው ሲሰራ ካየ እንደሚያጋልጥ ቃል ለመግባት ለመሀላው ወደ ሁለተኛው ክፍል ይላካል።

ወደ ሁለተኛው ክፍል ከገባ በኋላ በተዘጋጀለት መቀመጫ ይቀመጣል፡፡ ከብዙ ምክር እና ተግሳጽ በኋላ የተዘጋጁትን ቁሳቁሶች ተጠቅሞ መሐላውን ይፈጽማል፡፡ ገመድ በአንገቱ አድርጎ፣ የሬሳ መከፈኛውን ለብሶ፣ የሬሳ መሸከሚያ ቃሬዛው ላይ ተቀምጦ፣ አፈሩን በእጁ ይዞ ከሸማግሊዎቹ የሚነገሩትን ነገሮች ደግሞ እንዲናግር ይደርጋል።

“ሌላው ሰው ሲሰርቅ ዕያየሁ ዝም አልልም፤ ከሌላ ሰው ጋር ተባባሪ በመሆን ሌባውን አልደብቅም፤ እኔም አልሰርቅም፤ አልገደልም፤በአቋራጭ ለመበልፀግ ባሀላዊ መድሀኒትን አልጠቀምም፤ ሴትን አልደፍርም፤ ካለ በኋላ እስከ ዕለተ ሞቴ ድረስ በሰው ልጅ ላይ ተንኮል አልሰራም” በሎ በስረዓቱ መሰረት ምሎ ይወጣል። ይህንን ወንጀል መፈጸሙን እያወቀ እራሱን የደበቀ ሰው ደግሞ ይረገማል።

ይህ ባህላዊ ክዋኔ ለማኅበረሰባችን ትልቅ እፎይታን ሰጥቶ  ይገኛል በማለት አብረውን ቆይታ ያደረጉት አባት አብራርተውልናልእንግዲሀ የሃገር ሽማግላቹ በእንደዚህ ዓይነት መልኩ የወረዳዋን ነዋሪዎችን ከመንደር እስክ ከተማ ድረስ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለይ አንድም ሰው ሳይቀር ያስምላሉ።

እኛም አጋጣሚውን በመጠቀም ምለው ሲወጡ ያገኘናቸውን ሰዎች ሰለ ስነ-ስርዓቱ  እንዲነግሩን ጠየቅናቸው።

እነሱም የመሃላ ሰነ-ስርዓቱ ለማኅብረሰቡ በጣም ጥሩ መፍትሄ የሆነ እና በአሁኑ ሰዓት በወረዳዋ እየተበራከተ የመጣውን አዳዲስ የወንጀል ዓይነቶነትበተለይም ደግሞ ባህላዊ መድሀኒቶችን በመጠቀም  የሚፈጸሙትን ወንጀሎች ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለውናል።

አንድ የወረዳዋ ነዋሪ ችግር ቢደርስበት ማለትም የስርቆት፣ የዘርፋ እና ሌላም ወንጀል ቢፈፀምበት ቀጥታ ወደ ሽማግሌዎቹ በመሃድ የሚጠርጥረውን ሰው አስምሉልኝ ብሎ መክሰስ ይችላል። እነሱም የሰውየውን ቅሬታ በመቀበል የሚጠርጠረውን ሰው በማስጠራት ወደ ማስማያ ቦታ በመውሰድ እውነቱን እንዲናገር አለበለዚያ ደግሞ እንዲሚል ያደርጉታል።

ይህ የመሃላ ሰነ-ስርአት በዚህ የሚያበቃ ሳይሆን በየአመቱ የሚከናወን ቋሚነት ያለው ስርአት መሆኑንም ከሃገር ሽማግሌዎች ለመረዳት ችለናል።     

በርግጥ ይህ ወንጀልን በባሀላዊ መንገድ የመከላከሉ ተግባር በተለይም ባህላዊ መድሀኒት በመጠቀም ወንጀል ለሚሰራባቸው ግለሰቦች መፍትሔ እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡

የዚህ ወረዳ ነዋሪዎች የራሳቸው የሆነ ሌላም ባህላዊ መተዳደርያ ሕጎችና ደንቦች አሏቸው፡፡ በክልሉ ላይ ጫትና ተያያዥ ሱሶች የማይፈፀሙባት ብቸኛ ወረዳም ናት፡፡ ስርቆትና ዘረፋ የማይዘወተርባት ወረዳም ናት፡፡ በዚህም ምክንያት በወረዳዋ ያሉ ወጣቶች በመልካም ስነምግባር የሚታወቁ ሁነው ይታያሉ፡፡ ወንጀል የፈፀመ ሰውም በከተማዋ ላይ የሚነቀሳቀሰው አንገቱን ደፍቶ ብቻ ነው፡፡ የወረዳው ወንጀልን በመሀላ የመከላከል ተግባር ለሌሎች አከባቢዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው።

አስተያየት