የብቸኛው የድሬዳዋ “ድልጮራ” ሪፈራል ሆስፒታል ተግዳሮቶች

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራውሐምሌ 30 ፣ 2013
City: Dire Dawaጤናማህበራዊ ጉዳዮች
የብቸኛው የድሬዳዋ “ድልጮራ” ሪፈራል ሆስፒታል ተግዳሮቶች

የድሬደዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታልን የአስታማሚና ታማሚ ግፊያንና ያለውን መጨናነቅና ግርገር ለተመለከተ በከተማዋ ሌላ ሆስፒታል ያለ አይመስልም፡፡ በየቀበሌው የተቋቋሙትን ጤና ጣቢያዎችን ሕብረተሰቡ የመጠቀም ባህሉ እምብዛም ጥሩ እንዳልሆነም ያሳያል፡፡ ከግንዛቤ እጥረትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሳ ማኅበረሰቡ ለቀላሉም ለከባዱም እግሩ የሚቀናው ወደ ተለመደው ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ነው፡፡ ሆስፒታሉ ከተቋቋመበት ወቅት ከተማዋ ውሳጥ የነበረው የህዝብ ቁጥር መጠን አሁን ካለው የአስተዳደሩን የህዝብ ቁጥር መጨመር ተከትሎ ባለው ሁኔታ የተነሳ ሆስፒታሉ የመጣውን ሰው ሁሉ ማስተናገድ ዳገት እንደሚሆንበት እሙን ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል 569 ሰራተኞች አሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ወደ 400 የሚጠጉት የመስሪያቤቱ ቋሚ ሰራተኞች እንደሆኑ የድልጮራ ሆስፒታል የሰው ሀብት አስተዳደር ባለሞያ መአዛ መረሳ ገልፃለች፡፡ ሰራተኞቹ በሽፍት እንደሚሰሩና በቀን በአማካኝ ከ1500 የሚደርሱ የታማሚዎችን እንደሚያስተናግዱ ታብራራለች። በታካሚዎችና በጤና ባለሙያዎች መካከል ያለው ምጣኔ ሰፊ ከመሆኑም በተጨማሪ አሁን ላይ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር ጋር በተያያዘም በየሆስፒታሎቹ የታማሚ ቁጥር መጨመሩ የሚጠበቅ ቢሆንም የአቅም ውስንነትን እንዳስከተለ ትናገራለች። እንደሪፈራልነቱ የሚፈቀድለት በጀትና የሚሰራው ስራ የተመጣጠነ አይደለም፡፡ እንደዛም ሆኖ ግን በተቻለ አቅም አገልግሎቶችን በጥራት ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው ስትልም አብራርታለች፡፡

በያንዳንዱ ቀበሌ የጤና ጣቢያዎች እያሉ በዚህ ልክ ነዋሪው ለምን ወደ ድልጮራ ሆስፒታል ያቀናል የሚል ጥያቄ  ያነሳንላት የከተማዋ ነዋሪ የሆነችው  መሰረት ጌታቸው ሃሳቧን አጋርታናለች። “ከተማዋ ውስጥ ያሉት ጤና ጣቢያዎች ጥራት ያለው አገልግሎት አገኛለሁ ብዬ አላስብም ምክንያቱም አገልግሎቱ በነፃ መሆን  አንዲሁም ለመድሃኒት የምንከፍለውም ዋጋ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጥራት ያለው አይመስለኝም። ነገር ግን በግሌ ምንም ያጋጠመኝ ጥሩ ያልሆነ ነገር የለም” ስትል የሚሰማትን ገልፃለች፡፡

ሌላኛው አስተያየቱን ለአዲስ ዘይቤ የሰጠው የድሬደዋ ነዋሪ ሚካኤል ፍፁም ደግሞ ከድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ውጪ በሌሎቹ የመንግስት የጤና ተቋማት ሁሉንም አገልግሎት አገኛለሁ ብሎ እንደማያስብ ይናገራል። “በተለይ መዳኒት የለም የሚባልበት አጋጣሚ ስለሚበዛ እና ድልጮራ መሄድ ስለሚቀናኝ በብዛት ድልጮራ ነው የምመጣው” ሲል ሃሳቡን ገልጿል፡፡

ሆስፒታሉ ሪፈራል እንደመሆኑ በዛ ሆስፒታል መታከም የሚገባው ሪፈር የተባለ ግለሰብ ነው የሚል እምነት ቢኖርም ለነዋሪው የሪፈራልንና የሌላውን ሆስፒታል ልዩነት ለማስረዳት ከባድ እንደሆነና ሌሎች ድንገተኛ በሽታዎች አፋጣኝ እርዳታ የሚሹ ታካሚዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ በድንገተኛ በኩል ለመውለድ በሚመጡበት ወቅት እንደጤና ተቋም ወረቀት ካላመጣችሁ ማለት እንደሚከብዳቸው የገለፀው ነርስ ሰለሞን ማሞ የሆነ ሰአት የሪፈር ወረቀት የያዘ ሰው ብቻ እንዲገባ ተደርጎ እንደነበር ገልፆ በሰአቱ ግን ሰው ካላስገባችሁኝ እያለ መጨቃጨቅና ክርክር በር ላይ ተበራክቶ እንደነበር ምክኒያቱን ደግሞ ሲያስረዳ በየመኖሪያ አካባቢ ታከሙ ስንላቸው ስራውን ጥላቻ ወይም ሽሽት የሚመስለውም እንደሚኖርም ገልፃል፡፡ እንዲሁም የአስታማሚ ባጅ ተዘጋጅቶ ለአንድ ሰው ሁለት አስታማሚ እንዲያስታምመው እንደሚረግ ነገር ግን እየተቀባበሉ እንደሚገብ በዛ ላይ የማይፈቀዱ ነገሮች ልክ እንደ ጫት ይዘው እንደሚገቡ አክሏል፡፡ እነዚህን መሰል ድርጊቶች ግን የሚያደርጉት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀምና ጥበቃዎችን በማታለል ለምሳሌ በአጥር የማስገባት አይነት መንገዶችን ይጠቀማሉ ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን የጥበቃዎች እጥረትም እንዳለ አያይዞ ገልፆልናል፡፡

ከፅዳት ጋር በተያያዘ ከድልጮራ ሆስፒታል በቀን የሚወገው ቆሻሻ በጣም ብዙ እንደሆነና ምክንያቱ ደግሞ ለመታከም የሚመጣው፣ ተኝቶ የሚታከመው፣ የሚያስታምመው፣ እንዲሁም ጠይቆ ለመመለስ  የሚመጣው ቁጥር በጣም ብዙ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሆነ በድልጮራ ሆስፒታል ውስጥ የፅዳት አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ አዜብ ገብሬ የገለፁ ሲሆን አያይዘውም ያ ሁሉ ሰው ምግብ ያመጣል፣ ውሀ በሀይላንድ እና አትክልት ያመጣል ሁሉንም ደግሞ እዛው ነው ጥሎት የሚሄደው ያ መሆኑ የፅዳት ሰራተኞቹ  ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝ ገልፃለች፡፡ ግቢውን በተቻል አቅም ለማፅዳት ቢሞክሩም አንዳንድ ግለሰብ ግን እንደሚያማርራቸውና የማይገባ ድርጊት ልክ እንደ ሽንት በሀይላንድ ሞለቶ በየቦታዉ መጣል እና የምግብ እጣቢን በየቦታው የመድፋት ነገር እንዳለ እና በአግባቡ ተጠቀሙ ሲሉ ያልተገባ ምላሽ የሚሰጣቸው ሰው እንደሚያጋጥማቸውም አጫውታናለች፡፡ የቆሻሻው በዚህ መልኩ ያለ አግባብ መጣል የተጠቃሚው ግደለሽነት ብቻ ሊሆን ይችላል የሚለውን ጥያቄ ባስከተልንበት ወቅት በሚገባው መጠን የቁሻሻ መጣያዎች እንደሌሉ፣ ጥራታቸው የተጓደለ እና የተሰበሩ የቆሻሻ መጣያዎችም እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

በድሬደዋ ድልጮራ ሪፈራል ሆስፒታል ለመታከም የሚመጡት የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በዙሪያ ካሉ የገጠር ቀበሌዎችም ጭምር እንደሆነ በድልጮራ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና ስትከታተል ያገኘናት ራሄል ምህረት የተባለች ወጣት የነገረችን ሲሆን አያይዛም ከዛ አካባቢ ሲመጡ አንድ ሰው ሲታመም አስር ሰው ሊያስታምም ሊመጣ ስለሚችል በቦታው ትልቅ መጨናነቅን እንደሚፈጥር አስረድታለች፡፡ ያ መሆኑ ደግሞ ግቢው ላይ ከፅዳትና በሽታን ከመከላከል አንፃር መሰናክል እንደሚሆን በተለይ አሁን ያለንበት ወቅት ኮቪድ ስለሚኖር ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል ስትል ሀሳቧን ገልጻለች፡፡

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ በየቀበሌዎች የጤና ጣቢያዎችን ከፍቶ ሁሉም በየአካባቢው ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰአት የጤና ጣቢያዎቹ ከዚህ በላይ መስራት የሚችሉ ሲሆን  ለቀላል የህመም አይነቶች ወደነዚህ በየቀበሌው ወደሚገኙ የጤና ተቋማት መጠቀም ለራስም ሆነ ለሪፈራል ሆስፒታሉ ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛ የሰው ቁጥር በሚያስተናግበት ወቅት በሚፈጠሩ ክፍተቶች ምክንያት ሰው ለሆስፒታሉ ያለው አመለካከት ጥሩ እንዳይሆን ከማረግ እና የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ከመዳኒት ጭምር እጥረት እንዲገጥም ያደርጋል፡፡ ለራስ ምታቱም ለሆድ ቁርጠቱም  ወደ ድልጮራ ሆስፒታል ከመሮጥ  በየአካባቢው ባሉ ጤና ጣቢያዎች መጠቀም ጉልበትንም ሆነ ገንዘብን መቆጠብ እንደሚቻል እሙን ነው፡፡ እራሳቸው የጤና ጣቢያዎቹ ከአቅማችን በላይ ነው እስካላሉ ድረስ በቅርብ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ጎራ ብሎ የመታከም ተሞኩሮ ማዳበር ተገቢ ነው፡፡  

Author: undefined undefined
ጦማሪዝናሽ ሽፈራው

I graduated from Bahir dar university in the field of journalism and communication, and a reporter at Addis Zeybe in Dire Dawa branch.