ሐምሌ 30 ፣ 2014

አምናና ካቻምና የተተከሉት ችግኞችንስ?

City: Dessieማህበራዊ ጉዳዮችወቅታዊ ጉዳዮችምጣኔ ሀብት

ቃልኪዳን ችግኞቹን የተከለችባቸው ቦታዎች ከከተማ የራቁ በመሆናቸው ዳግም ሄዳ ለማየት ባትችልም፤ ችግኞቹን ለመንከባከብ ግን ፍላጎት አላት።

Avatar:  Idris Abdu
እድሪስ አብዱ

እድሪስ አብዱ በደሴ የሚገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነው።

አምናና ካቻምና የተተከሉት ችግኞችንስ?
Camera Icon

ፎቶ፡ ኢድሪስ አብዱ (ከአዲስ ዘይቤ)

የተለያዩ ጥናታዊና ታሪካዊ ፅሁፎች እንደሚያትቱት በሃገራችን ኢትዮጵያ ችግኝን በዘመቻ መትከል የተጀመረው በ14ኛው ክፍለ ዘመን በንጉስ ዘረ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት እንደነበር ያስረዳሉ። በመንግሥት ደረጃ ችግኞችን አፍልቶ መትከል የተጀመረው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት ነበር። ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚቀርበው ንጉሡ አጼ ልብነ ድንግል ከወፍ ዋሻ ዘርና ችግኞችን ወስደው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በሚገኘው መናገሻ ሱባ የሚባል ሥፍራ የሃበሻ ጽድ መትከላቸው ይነገራል።

በዳግማዊ ሚኒልክ ዘመንም ደኖች የህዝብ ኃብት እንደሆኑ በሕብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ተሞልሮ ነበር። በጊዜው የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል ያስችል ዘንድ “ሁሉም በግለሰብ መሬት ላይም ያሉ ዛፎች የመንግሥት ንብረት ናቸው” ሲሉ አዋጅ አስነግረው እንደነበር የለምለም ታጀበ (Status, Challenges and Opportunities of Environmental Management in Ethiopia) በሚለው ጥናታዊ ፅሑፍ ላይ ሰፍሮ ይገኛል።

በንጉሥ ኃይለሥላሴም ይሁን በደርግ ዘመነ መንግስት ችግኝ መትከልና መንከባከብ እንደ አንድ የመንግስት ፓሊሲ ተደርጎ በስፋት ሲሰራበት እንደነበር በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ መስማት የተለመደ ተግባር ነው። 

በኢህአዴግም ጊዜ ቢሆን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በታዳጊ ሃገሮች ላይ እያስከተለ ያለውን ተጽእኖ ለአለም በማስረዳት መንግስታት ትኩረታቸው ተፈጥሮን መንከባከብ ላይ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

በአሁኑ ላይ ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ  'አረንጓዴ አሻራ' በሚል ዘመቻ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ አሊ በአገር አቀፍ ደረጃ ችግኝ እንዲተከል ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን ተከትሎ ዘንድሮም በ2014 ዓ.ም. የክረምት ወቅት በመላ ሃገሪቱ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች እየተተከሉ ይገኛል። 

በደሴ ከተማም ይሄው ዘመቻ ተጠናክሮ በመቀጠል በመንግስት ተቋማት አስተባባሪነት ህብረተሰቡ በርካታ ችግኞችን እየተከለ ይገኛል። ከሰሞኑም በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በደሴ ከተማ ልዩ ስሙ ጦሳ ተብሎ በሚታወቀው ተራራ ላይ ከአምስት ሺህ በላይ ችግኞችን መትከል ችለዋል። ይህም ተግባር አድናቆት የሚቸረውና ይበል የሚያሰኝ ነው።

ይሁን እንጅ አብዛኛውን ጊዜ 'ይህ ያህል ሺህ ችግኝ ተከልን' ከማለት ያለፈ በችግኞቹ እድገት ላይ ምንም አይነት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲደረግ አይታይም። ይህም ሁኔታ “በአንድ ጀምበር 350 ሚሊየን ችግኝ በመትከል በህንድ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ አሻሽያለሁ” የሚለው መንግስትም ከሚሊየኖቹ ምን ያህሉ ጸደቀ ? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ የሚሰጥ ጥናት አጥንቶ ሲያቀርብ አይታይም። ቁጥራዊ መረጃ ከማቅረብም በተጨማሪም በቀጣይ ስህተቶችን በማረም ለትውልድ የሚተርፍ ስራ መስራት ይገባል።

ወጣት አማረ አበበ ከወንዶገነት ዩኒቨርሲቲ በደን ልማት የትምህርት ዘርፍ በ2010 ዓ.ም የተመረቀ ሲሆን፤ ይሰራበት ከነበረው ትግራይ ክልል በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ምክንያት ስራውን ለመልቀቅ መገደዱን ገለጾል። ከዛም ወደ ደሴ ከተማ በመምጣት መኖር ከጀመረ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር በማህበር ተደራጅተው በሙያቸው የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚፈልጉ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ አቀረቡ። ለስራ እድል ፈጠራና ግብርና መምሪያ ቢሮዎች በተደጋጋሚ ቢያመለክቱም ሃሳባቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን ገልጿል።

የአዲስ ዘይቤ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ለመቃኘት እንደቻለው በደሴ ከተማ እና አካባቢው ላይ በተከታታይ አመታት የተተከሉ አብዛኞቹ ችግኞች ከቦታቸው ላይ እንደሌሉ ማረጋገጥ ትችሏል። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት ለተከላ የሚመረጡ ቦታዎች አብዛኞቹ ቅድመ ዝግጅት የማይደረግባቸው ሆነው ተግኘተዋል። ስለሆነም ችግኞቹ በከብቶች መበላት፣ በሰዎችና በከብቶች መረጋገጥ፣ ተነቅሎ መውደቅ፣ ክትትል እና እንክብካቤ በማጣት መድረቅ እና በሌሎችም ምክንያቶች ለውጤት ሳይበቁ ቀርተዋል።

ዳንኤል ጋሻው ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በ 2008 ዓ.ም. በአፈርና ውሃከል የትምህርት ዘርፍ(Soil and Watershed Management) ቢመረቅም በሙያው ስራ ማግኘት ባለመቻሉ በሹፍርና የሙያ ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል። ወጣት ዳንኤል ጋሻው “በግብርናው ዘርፍ ተፈጥሮን መንከባከብና በእጸዋት ሳይንስ በርካቶች ተምረው ስራ ያላገኙ ወጣቶች አሉ። እንደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ አይነት ተቋሞች ደግሞ በተለያየ ስፍራ የሚተክሏቸው እጸዋት በአግባቡ እንዲያድጉ ሙያው የሚጠይቀውን ማንኛውም አይነት ግብአት አሟልተው ችግኞችን ቢንከባከቡ ለወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ቢችሉ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው” ሲል ሃሳቡን ይገልጻል።

እንደነ ዳንኤል ሁሉ ቃልኪዳን ጌታሁንም ከወሎ ዩኒቨርሲቲ በ2012 ዓ.ም በማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቃለች። እንደ ቃልኪዳን ሃሳብ ከሆን አደረጃጀት ተፈጥሮላቸው ገቢ ማግኘት እስከቻሉ ድረስ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን ችግኝ በመንከባከብና ለውጤት ለማብቃት ፈቃደኛ ፍቃደኝነቷን ገልጻልች። 

ለአዲስ ዘይቤ ቃልኪዳንም ከአመት በፊት ችግኝ በዘመቻ የተከለች ቢሆንም ከዚያን ቀን በኋላ ችግኙ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሄዳ አይታው እንደማታውቅ አልደበቀችም። “አብዛኞቹ ችግኞች የተተከለባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ባሉ ስፍራዎች ላይ ስለሚሆን ዳግም ሄዶ ለማየት ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ ከፍላጎት ያለፈ ነገር ሊኖርህ አይችልም” ስትል ለአዲስ ዘይቤ ገልጻልች።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ስለ ችግኝ ተከላው አላማ ሲገልጹ “በአማራ ክልል የሚገኙ ዩንቨርስቲዎች የክልሉን ህዝብ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ለመጥቀም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በዚህ ክረምትም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ችግኝ ተከላ የሚያከናውኑ ሲሆን ወሎ ዩኒቨርሲቲም ከ60 ሺህ በላይ የደንና የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የአፈር መሸርሸርንና የደን መራቆትን ለመከላከል እየሰራ ነው። በደሴ ከተማ ጦሳ ተራራ ላይም በዘንድሮው መርሃ ግብር ከ3 ሺህ 200 በላይ የተለያዩ ችግኞች ተተክሏል” ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲ ፎረሙ አማካኝነት በአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ ጦሳ ተራራን ጨምሮ ጮቄ ተራራን፣ ጉና ተራራንና ሌሎች በአማራ ክልል የሚገኙ ቦታዎችን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በየዓመቱ ችግኝ በመትከል ላይ ናቸው። በማሳያነት የዘንድሮውን መርሃ ግብር አንስተው የተተከሉት ችግኞች እንዲጸድቁ ከሌላው ጊዜ በተሻለ እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ዶ/ር መንገሻ ጨምረው ገልጸዋል።

የደሴ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ “ደሴ ከተማ በተራራ የተከበበች ከተማ እንደመሆኗ ለጎርፍ ተጋላጭ ናት። ነዋሪው ሕብረተሰብ አረንጓዴ አሻራውን በማስቀመጥ የሚደርሰውን ጎርፍ ለመከላከል መረባረብ አለበት” ብለው ለዚህም ተግባር “ከዩኒቨርሲቲዎች የሚገኘውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የጦሳ ተራራን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም አቅደን እየሰራን ነው” ብለዋል።

በከተማቻው ውስጥና በዙሪያው የተተከሉ ችግኞች ውጤታማ እንዲሆኑ በቋሚነት ችግኞቹን የሚንከባከቡ አካላትን በማሰማራት ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት እንደሚሰሩ ከንቲባው ጨምረው ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ስራ እና ስልጠና ቢሮ በ2015 ዓ.ም በጀት አመት ለ 1 ሚሊዬን 203ሺህ 18ዐ ወጣቶች የስራ እድል ሊፈጥርላቸው አቅዷል። ከነዚህ ወጣቶች መካከል 54 ከመቶ ለሚሆኑት የስራ እድል የሚፈጠረው በግብርና ዘርፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር  እንደሆነ የቢሮው ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ ገልፀዋል።

ችግኞች ከመትከል ባለፈ እንክብካቤና ክትትል የሚያደርጉ በኢንተርኘራይዝ ለተደራጁ የክልሉ ወጣቶች በቋሚነት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቢሮው ኃላፊ ተናግረዋል።

አስተያየት