ጥቅምት 20 ፣ 2014

ከሰሞኑ በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና የቀጣይ ጊዜ ጥንቃቄዎች

City: Dire Dawaዜናማህበራዊ ጉዳዮች

በድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ አራት ጊዜ  ርዕደ መሬት (የመሬት መንቀጥቀጥ) ተከስቷል። የሰሞኑ የመሬት ንቅናቄ ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወስዱ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።

Avatar: Zinash shiferaw
ዝናሽ ሽፈራው

ዝናሽ ሽፈራው በድሬዳዋ የሚትገኝ የአዲስ ዘይቤ ዘጋቢ ነች።

ከሰሞኑ በድሬዳዋ ከተማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እና የቀጣይ ጊዜ ጥንቃቄዎች
Camera Icon

Photo: Solomon Yimer

በድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ ብቻ አራት ጊዜ  ርዕደ መሬት (የመሬት መንቀጥቀጥ) ተከስቷል። ጥቅምት 6፣ 8፣ 13 እና 18 ያጋጠመው ርዕደ መሬት በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት አላደረሰም። ርዕደ መሬት በመሬት ውስጥ በታመቀ ኃይል ልቀት የተነሳ በseismic waves / ‘ሲሰሚክ’ ሞገዶች አማካኝነት እንደሚከሰት ባለሙያዎች ያብራራሉ። የሰሞኑ የመሬት ንቅናቄ ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል ነዋሪዎች ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወስዱ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።

ወ/ሮ መስታዋት ደይሳ በድሬደዋ ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ስትሆን ባሳለፍነው ሳምንት ካያጋጠሙት የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተቶች መካከል ሁለቱን ስለማስተዋሏ ትናገራለች። ጥቅምት 13፤ ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ የቤቷ በር ላይ ተቀምጣ በነበረችበት ወቅት ርዕደ መሬት መከሰቱን አስተውላለች። ወ/ሮ መስታዋት “በወቅቱ ተርበትብቼ ነበር። የመሬት መንቀጥቀጥ በሚኖርበት ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ዕውቀቱ የለኝም። ከምን መራቅ እንደሚገባም አላውቅም” ስትል በጊዜው የነበረውን ሁኔታ አስረድታለች። ሌላኛው ጥቅምት 8 ሌሊት 8 ሰዓት የተከሰተው ሲሆን “የአንዳች ነገር መውደቅ የሚመስል ድምጽ ብሰማም መሬት መንቀጥቀጥ አልመሰለኝም ነበር” ብላለች።

አቶ ማቲያስ ተፈራ የወ/ሮ መስታወትን ሀሳብ ይጋራል። እንደ አቶ ማቲያስ ገለፃ “የተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች ስለ ርዕደ መሬትና ጥንቃቄዎች ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰራተኛዋ ወ/ሮ ቢፍቱ ሁሴን ጥቅምት 13 ቀን ጠዋት ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ተከስቶ የነበረውን የመሬት መንቀጥቀጥ አስተውላ እንደነበር ትገልፃለች። ስራዋን አቋርጣ ከቢሮ ወጥታ ራሷን አረጋግታ መመለሷንም ተናግራለች።

በወቅቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ ህዋ ሳይንስና አስትሮኖሚ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር፣ የርዕደ መሬት ባለሞያና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ በሰጡት ማብራሪያ ጥቅምት 8 ሌሊት የተከሰተው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 4.1 እንደተመዘገበ ገልፀዋል።

ድሬደዋ በታላቁ የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ ጫፍ የምትገኝ በመሆኗ አነስተኛ ርዕደ መሬቶች በተደጋጋሚ ሊከሰቱባት እንደሚችሉ ተመራማሪው አመልክተዋል። “የስምጥ ሸለቆ ተፈጥሮ አንዱ መገለጫው እንደ መሬት መንቀጥቀጥና የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ሊከሰት መቻሉ ነው። ስለዚህ እዚህ አካባቢ መከሰቱ የሚያስገርም አይደለም” ያሉ ሲሆን ሰሞኑን ያጋጠመውን የርዕደ መሬት ሁኔታ ሲያብራሩ “ክስተቱ ያጋጠመው ድሬዳዋ ውስጥ አይደለም” ይላሉ። “ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ የሚገኘው ወደ አፋር አካባቢ ነው ሌሊት የድሬዳዋ ነዋሪ ሊያስተውለው የቻለው ክስተቱ ያጋጠመው ሌሊት በመሆኑ ነው።” ተመራማሪው ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉ “በደንገጎ ተራራማ አካባቢ የሚገኘው አለት ድንጋያማ አካባቢ ይበዛዋል። ያ ማለት እሳተ ጎሞራ በአንድ ወቅት ያዘወትረው የነበረ ቦታ መሆኑን ያመላክታል። ስለዚህ በተለያየ ጊዜያት ርዕደ መሬት የሚጠበቅ ነው” ብለዋል።

ሀረርና ሰመራ የሚገኙት መሳሪያዎች በርካታ የመሬት መንቀጥቀጦችን እንደሚመዘግቡ እንጠብቃለን ለሕብረተሰቡ ባይሰማም መሬት መንቀጥቀጦቹ እያጋጠሙ ስለመሆኑ አዲስ ዘይቤ ያነጋገረቻቸው ባለሙያዎች ተናግረዋል። ይህ በሬክታል እስኬል ከፍ  ወዳለ መጠን ሊሄድ ወይም ሊጠፋ እንደሚችልም ተጠባቂ ነው። ነገሩ ለባለሙያ ትንበያ አመቺ ባለመሆኑ እንዲህ ይሆናል ብሎ መናገር አስቸጋሪ ስለመሆኑም ሰምተናል። ተመሳሳይ ክስተት ሲያጋጥምም ሕብረተሰቡ ከመደናገጥ ይልቅ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ ለመውሰድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ይመክራሉ።

በርዕደ መሬት ወቅት ሊወሰዱ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

ከቤት ውጭ ከሆነ - ከዛፎች፣ ከሕንፃዎች፣ ከኤሌትሪክ ምሶሶዎች እና ሌሎች ወድቀው ጉዳት ሊያደርሱ ከሚችሉ ነገሮች መራቅ እና ገላጣ ሜዳ አካባቢ መቆየት።

በቤት ውስጥ ከሆነ - በበር መቃኖች፣ በኮርነሮች እና ኮሪደሮች ተጠግቶ ማሳለፍ። ከእሳት ምድጃዎች፣ ከተሰቀሉ ፍሬሞች እና የግድግዳ ጌጦች፣ ከመጽሐፍ መደርደሪያዎች እንዲሁም ከመስኮት አካባቢ መራቅ። የጋዝ ምድጃዎችን በተቻለ ፍጥነት ማጥፋት ካልሆነም ከአካባቢው መራቅ።

በትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥ ከሆነ- ከሕንጻዎቹ ለመውጣት አለመሞከር፣ አሳንሰር (ሊፍት) በፍፁም አለመጠቀም። ከደረጃዎች አካባቢ መራቅ።

መኪና እያሽከረከሩ ከሆነ- የኤሌትሪክ መተላለፊያ ምሶሶዎችን፣ ዛፎችና ሽቦዎች አካባቢ አለመቆም፣ የኤሌትሪክ መስመር ምሶሶዎች እና ሽቦዎች ተሽርካሪው ላይ ከወደቁ ከመኪናው ለመውጣት አለመሞከር፣ በተቻለ ፍጥነት ገላጣ ወደሆነ አካባቢ መኪናን ማቆም።

አስተያየት