የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር ማሻቀብ በቀደመው ጊዜ በአነስተኛነት ይፈረጁ የነበሩ የሥራ ዓይነቶች በተደራጁ ወጣቶች እንዲሰሩ አስገድዷል። የአንድ አካባቢ ወጣቶች አንድ ዐይነት ስራ ለመስራት በቀበሌ ተደራጅተው እንጀራ ከሚበሉባቸው ዘርፎች መካከል የመኪና እጥበት፣ ጫኝና አውራጅ፣ የታክሲ ተራ ማስከበር ይኙበታል። በአዳማ ከተማ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መታየት የጀመሩት “ሸራ ማኅበራት” ደግሞ በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ካልተለመዱት መካከል ይገኙበታል። የሸራ ማኅበራት ለአገልግሎታቸው የሚጠይቁት ክፍያ መጋነን፣ አገልግሎቱ ለተገልጋዮች ይህ ነው የሚባል ጥቅም አለመስጠቱ የማኅበራቱን ተገቢነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ጉዳዮች ሆነዋል።
ሸራ ማኅበር ምንድነው?
የገዳ ጫኝ እና አውራጅ ማኅበር አባል ወጣት ሰሎሞን ባዩ “ሸራ ማኅበራት አገልግሎት የሚሰጡት ለእቃ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ነው” ሲል ከአዲስ ዘይቤ ጋር በነበረው ቆይታ ተናግሯል። “በሸራ ጥቅል የታሸገውን የተሽከርካሪውን ጭነት መፍታት ዋነኛ ሥራቸው ነው። ሸራውን ገልጠው፣ የታሸገበትን ቁልፍ መሳይ ብረት ቆርጠው መልሰው ወደ መኪናው ይጭናሉ። ይህንን የሚያደርጉት ከአስጫኙ፣ አሽርካሪውና ረዳቱ ጋር በመሆን ነው። ከባለቤቱ ጋር መተማመን ላይ ከደረሱ በኋላ የእኛ ስራ ይጀምራል። እኛ ስራችን እቃዎችን ማውረድ እና መጫን ነው” ካለ በኋላ ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ከአሰሪያቸው ጋር የዋጋ ድርድር እንደሚያካሂዱ እና ለተቀበሉት ክፍያ ሕጋዊ ደረሰኝ እንደሚሰጡ ነግሮናል።
በአጭር አገላለጽ የሸራ ማኅበራቱ ሥራ የታሸገውን ሸራ ፈትተው ለጫኝና አውራጆች ሥራ ማመቻቸት ይመስላል። የማኅበራቱ ሥራ አግባብነት የለውም የሚሉ ወገኖች ክርክርም እዚህ ላይ ያተኮረ ነው። የሸራ ማኅበራቱን ድርጊት የሚቃወሙት ሰዎች ሀሳብ “ሥራው በእቃው አስጫኝ ወይም በረዳት እና አሽከርካሪው ሊሰራ የሚችል ነው። ጉልበተኞቹ ወጣቶች ከፍተኛውን ገንዘብ የሚወስዱት ይህ ነው የሚባል ሥራ ሳያከናውኑ ነው።” የሚል እንደሆነ የአዳማው ሪፖርተራችን ካነጋገራቸው ግለሰቦች ተረድቷል። ወጣቶቹ በአካባቢው በማይኖሩበት ጊዜ በስልክ ተጠርተው ሸራውን እንዲፈቱ መደረጉ፣ ያለ እነርሱ ፈቃድ ጭነቱን ከመኪና የሚያወርድ ባለቤት ለድብደባ መዳረጉ፣ ክፍያው በድርድር ሳይሆን በቁርጥ ክፍያ መከናወኑ ጉዳዩን ሕገ-ወጥ ያስባለ ድርጊት ስለመሆኑ ከአስተያየት ሰጪዎች ነግረውናል።
እየቀረበባቸው በሚገኘው ቅሬታ ዙርያ የሸራ ማኅበራትን ሐሳብ በዚህ ዘገባ ላይ ለማካተት ያደረግነው ጥረት ማኅበራቱ ሐሳብ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም።
የአሽከርካሪዎች ሮሮ
የከባድ መኪና አሽከርካሪው አቶ ኦቾ የሸራ ማኅበራቱ ክፍያ እስከ ብር 1ሺህ 8መቶ እንደሚደርስ እና የተጋነነ እንደሆነ ይናገራል። “ከጭቅጭቅ እና ከጸቡ ብለን እንከፍላለን። ክፍያው እንዲቀንስ መደራደር አደጋው ቀላል ላይሆን ይችላል። ሁሉም ይፈራል” የሚው አቶ ኦቾ ከፍተኛ ክፍያ ጠያቂዎቹ የሸራ ማኅበራት የመንግሥት መጋዘኖች አካባቢ እንደማይኖሩ ታዝቧል።
በአካባቢዎቹ አለመግባባት ሲፈጠር የሕግ አስከባሪዎች ማግኘት አዳጋች መሆኑን የነገረን ደግሞ አብዲ ወንድሙ ነው። የተሳቢ አሽከርካሪ መሆኑን የነገረን አብዲ “ክፍያን በተመለከተ የተቀመጠ ታሪፍ አለ” ይላል። “የዋጋ ተመኑ ረዳት ላለው ተሳቢ መኪና አንድ ሺህ ብር፣ ረዳት ለሌለው ስምንት መቶ ብር ነበር። በአሁኑ ሰዓት ማኅበራቱ እያስከፈሉ የሚገኙት ግን ረዳት ላለው አንድ ሺህ ስድስት መቶ ለሌለው ደግሞ አንድ ሺህ ስምንት መቶ ነው። ጉዳዩን በተመለከተ ለመግሥት አካላት ቅሬታ ብናቀርብም መፍትሔ አላገኘንም” ሲል አብራርቶልናል። ጉዳዩ የመንግሥትን ትኩረት ቢያገኝ ለበርካቶች እፎይታ እንደሚሆን በማሳሰብ አስተያየቱን ቋጭቷል።
የነዋሪዎች ትዝብት
ሌሊሴ ሰለሞንን ያገኘናት አዳማ ቦሌ አካባቢ ነው። የእንጨት ስራ ውጤቶች አቅራቢ ሱቅ ውስጥ ትሰራለች። በስራ አካባቢዋ የታዘበችውን ነግራናለች። "በሸራ ማጠፍ የተደራጁ ወጣቶች አሉ። የጭነት መኪና ሲመጣ ይደወልላቸዋል። ካሉበት ቦታ በ“ባጃጅ” ተሳፍረው ይመጣሉ። እነርሱ ካልደረሱ ማንም የመኪናውን ሸራ ፈትቶ እቃ አያወርድም።” ያለች ሲሆን ከዚህ ቀደም ሲቆዩባቸው ሸራ ፈተው ባወረዱ አሽከርካሪዎች ላይ የደረሰውን ድብደባ ታስታውሳለች። ይህንን ፍራቻ ሹፌሮችም ሆነ ረዳቶቻቸው መስራት የሚችሉትን ስራ ወጣቶቹን ጠብቀው፣ ከፍተኛ ክፍያ ፈጽመው ሲከውኑ መታዘቧ እንደሚያስገርማት አጫውታናለች።
በአዳማ ትልቁ የገበያ ማዕከል ወደ ሆነው አራዳ ጎራ ያለው ሪፖርተራችን በሸራ ማኅበራቱ ጉዳይ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል። ሽኩር ጀማልን አራዳ ገበያ ውስጥ እቃ በማድረስ ስራ ተሰማርቶ ይገኛል። ስለሸራ ማኅበራቱ ያየውን አካፍሎናል። "ሸራ መፍታት እና መጠቅለል የመኪናው ረዳት ሊሰራው የሚችል ቀላል ስራ ቢሆንም የሚከፈልበት ክፍያ በጣም ውድ ነው።" ብሎናል። ሌላው ሐሳብ ሰጪአችን አቶ ሽኩር በበኩሉ
“የሞገደኞቹን ወጣቶች ድርጊት ለሕግ አካላት መናገር መፍትሄ አያመጣም። ፖሊሶች ራሱ ወደዚህ ጉዳይ መግባት አይፈልጉም። ተነጋገሩ፣ ተስማሙ የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡት” ሲል ገጠመኙን አጋርቶናል።
የአስተዳደሩ ምላሽ
የቢሮውን ኃላፊነት ከተረከቡ ሁለት ቀናት ብቻ ያስቆጠሩት በአዳማ ከተማ አስተዳደር የኢንተርፕራይዞች እና ኢንድስትሪ ልማት ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ዲሮ ጉዳዩን እንደሚያውቁት ነግረውናል። “ብዙዎችን እንዳማረረ የታወቀለት የሸራ ማኅበራት እንቅስቃሴ ጉዳይ ወደፊት ከምንሰራባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይሆናል” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።